በእንስሳት እርባታ ለተሰማሩ የከተማ ነዋሪዎች ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት በሳይንሳዊ መንገድ በማርባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ጥር 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በእንስሳት እርባታ ለተሰማሩ የከተማ ነዋሪዎች ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት በሳይንሳዊ መንገድ በማርባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ የግብርና ዩኒት አስታወቀ።
በቡርጂ ዞን ሶያማ ከተማ አስተዳደር በኢኮኖምያዊ ክላስተር የግብርና ዩኒት መሪ አቶ ማልጀ ሞሌ በከተማ አሰተዳደሩ ዝሪያቸው የተሻሻሉ እንስሳትን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በማርባት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎችን በሙያተኞች ተጠናክሮ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በከተማው በአሁኑ ወቅት በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ወተት፣ እንቁላል እና ሌሎች የእንስሳት ተዋፅዖዎችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ምሳሌ የሚሆኑ ግለሰቦች እንዳሉ ጠቅሰው፥ ተሞክሯቸውን ወደ ሌሎች በማስፋት ለበለጠ ውጤት እንሠራለን ብለዋል።
በከተማ ግብርና ዩኒት የእስሳት እርባታ ባለሙያ አቶ ቦጋለ ጎሳ በከተማው ከዚህ ቀደም ስለ ዘርፉ እምብዛም ግንዛቤ እንዳልነበረና በተሰጠው ትምህርት ግን በርካታ ሥራ ያልነበራቸው ወጣቶች ጥቅሙን ተረድተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በግብርና ሞያ ለረጅም ዓመት በመንግስት መሥሪያቤት ሲያገለግሉ የቆዩ እና በአሁኑ ወቅት በጡረታ ጊዜያቸው የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ ይስጠኝ ደርባ፥ ቀደም ሲል የጀመሩት የወተት ላም፣ በእንቁላል ዶሮ እርባታ እና በንብ ማነብ ሥራ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡
ለጡረታ ዘመናቸው በማሰብ የጀመሩት የወተት ላም እርባታ፣ እንቁላል ዶሮ እና ንብ ማነብ ሥራ በትንሹ በቀን ከ10 ሊትር ወተት፣ ከ70 በላይ እንቁላል እና በዓመት ከ2 እስከ 3 ጊዜ ከ60 ኪሎ ግራም በላይ ማር በመቁረጥ በጡረታቸው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
ሌላኛው “እምነፅዮን” የአንድ ቀን ጫጩት የዶሮ እርባታ ከመነሻው በትንሹ የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጫጩቶችን በ45 ቀናት ውስጥ አሳድገው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ወጣት በላይነሽ አስማረ ትናገራለች።
ዘጋቢ: አብዶ አያላ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ