የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ጥር 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቆላማ አከባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከደቡብ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ በምርምርና በተለያዩ የግብርና አመራረት ፓኬጅ ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በደቡብ ኦሞ ዞን ቀይአፈር ከተማ አካሂዷል፡፡
የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ከምርምር ማዕከላትና ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እንደሚሠሩ የገለፁት በፌዴራል የቆላማ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ወንድማገኘሁ ሺብሩ፥ የጂንካ ምርምር ማዕከል ሥራዎችን ወደ ሌሎች ማዕከላት ለማስፋት መሰራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
የግብርና ምርምር ማዕከላት ለአርብቶ አደሩ አከባቢ ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር መሪሁን ፍቅሩ ገልፀዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢዎች ልማት ቢሮ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ አይደ ሎመዶ በበኩላቸው፥ የግብርና ኤክስቴንሽን ዘርፍን በዘላቂነት ለመደገፍ አሳታፊ የምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ተክሌ ዮሴፍ እና የክልሉ ቆላማ አከባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ዳይሬክተር አቶ ሚሊዮን ተክሌ በጋራ እንደገለፁት አዳዲስና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማላመድ የአርሶና የከፊል አርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ አሰረድተዋል ፡፡
ማህበረሰቡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት በእጥፍ ለማሳደግ እንዲችሉ የሚያግዙ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች በፓከጅ መቅረቡን ተመራማሪ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመቅረፍና የ2017 እቅድ ለማሳካት ያለመ ውይይት እየተካሔደ ነው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በህገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩና ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ
በጀት ዓመቱ ከ3 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ