የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ለሥራው ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ጥር 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለሁሉ አቀፍ ለውጥ የሚያበረክተው አስተዋእጾ ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ለሥራው ትኩረት መስጠት እንዳለበት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ ገለጹ።
የ2016 ዓ.ም ዞናዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባር “በተደራጀ የህዝብ ንቅናቄ የሚፈፀም የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በበናፀማይ ወረዳ ጎልዲያ ቀበሌ ላይ በይፋ ተጀምሯል።
ከ2003 ዓ.ም በ31 ሄክታር የአፈርና ውሃ ጥበቃ የተጀመረው ዛሬ ላይ ከ988 ሄክታር በላይ መሬት የተፋሰስ ስራ መሰራት መቻሉን የገለፁት የበናፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ጋያ ሲሆኑ፥ በለሙ አካባቢዎች ምንጮችን ጨምሮ ለዱር እንስሳት መኖሪያነት የሚያገለግሉ ከባቢ መፍጠር መቻሉን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ግብርና መመሪያ ሀላፊ አቶ ባንኬ ሱሜ በበኩላቸው በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ጉዳትና መራቆት ለማስቀረት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማካሔድ መልሶ ማልማት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሁሉ አቀፍ ልማት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ለተግባሩ ያለ ቀስቃሽ ወጥቶ በሥራው ላይ መሳተፍ እንዳለበት አቶ ባንኬ ገልፀዋል።
የሰው ቁጥር በጨመረ መጠን ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ አካባቢን በአግባቡ መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ፥ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር፣ በለሙ አካባቢዎች ንብ ማነብን ጨምሮ ሌሎች ለኢኮኖሚ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን በስፋት መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
የለሙ አካባቢዎችን ለታለመ ዓላማ ብቻ እንዲውሉ በማድረግ ከእንስሳት እና ከሰው ንኪኪ ውጭ ሆኖ መጠበቅ እንዳለበት ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
በወረዳ ደረጃ 3 ሺህ 334 ሄ/ር መሬት በ14 ተፋሰሶች እንደሚለማ የበናፀማይ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ መንግስቱ በርቂ ጠቁመው፥ ከዚህ በፊት በለሙ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ማስገኘቱን ተናግረዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ
የክልሉ ህዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ለማድረግ አልሚ ባለሀብቶች እያበረከቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ