በዞኑ በመንገድ መሠረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

በዞኑ በመንገድ መሠረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ጥር 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዞኑ በመንገድ መሠረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የካፋ ዞን መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ አስታውቋል።

መምሪያዉ የ2016 በጀት ግማሽ ዓመት አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ  አካሂዷል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የመምሪያው ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ መንገድ በሁሉም ዘርፍ የሚከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማሳለጥ የመንገድ መሰረተ ልማት ፋይዳዉ የጎላ ነዉ ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዞኑ ባሉ መዋቅሮች ባለፉት 6 ወራት የትራንስፖርት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በተደረገዉ ጥረት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በተለይም በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ከታሪፍ በላይ ማስከፈልና ትርፍ መጫን ጋር ተያይዞ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት የዲጂታል ትራንስፖርት አገልግሎት ከማስጀመር ጀምሮ ለዉጥ መታየት ጀምሯል ብለዋል።

የመንገድ መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አንጻርም ህብረተሰቡን በማስተባበር በሁሉም ወረዳዎች የተሻለ አፈጻጸም መጀመሩን ተናግረዉ ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠል ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ልሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመደረኩ የተገኙት የካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ጽዮን ታዬ፥ ከመንገድ አገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የዞኑ አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዞኑ በርካታ የቱርዝም መዳረሻዎች ያሉበት ቢሆንም በመንገድ ተደራሽነት ችግር አገልግሎት አለመስጠቱን ገልጸዉ ይህንን ማረም እንዲቻል ዳድበንና የተፈጥሮ ድልድይ መሄጃ መንገዶችን በመገንባት ላይ ናቸዉ ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በዞኑ የገጠር ተደራሽ መንገድ ችግሮችን መፍታት እንዲቻል በተደረገ ጥረት ከታዩ ዉጤቶች በጨና ወረዳ የዋንጃልና አካባቢ ነዋሪዎች በአካባቢው የሚታየዉን የመንገድ ችግር ለመፍታት በአጭር ጊዜ ከ11 ሚሊዮን ብር ማዉጣታቸዉ ለአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል አቶ አብዮት መላኩ እና አቶ በልቶ አባሮ የመንገድ ደህንነት ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችል በየደረጃው ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተሰሩ ስራዎች ዉጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ የትራንስፖርት ማህበራት፣ የመምህራን ማህበር ተወካዮች፣ የሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን