የአፈር ጤንነት በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሀገር ህልውና ሊረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ገለፀ
የአፈር ጤንነት ለሀገር ህልውና በሚል መሪ ቃል የክልሉ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በኮንታ ዞን በይፋ ተጀምሯል፡፡
በመርሃ-ግባሩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፀጋዩ ማሞ፤ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አካባቢ ላይ ነው ያለነው፡፡ ነገር ግን በሰዎች ጫና እየደረሱ ያሉ ችግሮችን ለመቋቋም የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ተግባር የዘወትር ሥር መሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ተወካይና የተፈጥሮ ሀብት ልማት መሪ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን ለዘንድሮው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቆ ከ20 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በማሳተፍ የማልማትና የጥበቃ ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
አክለውም በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ለማስጠበቅ በነቂስ መስራት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በክልሉ ከ200 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ ለማልማት በ41 ወረዳዎች 1,188 ንዑስ ተፋሰሶችን ለይተው ወደ ስራ መግባታቸውን አብራርተዋል።
ባለፈው ዓመት በ1,134 ንዑስ ተፋሰሶች 229 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማታቸውን ያወሱት የቢሮ ኃላፊው ከዘንድሮ መሪ ቃል መነሻ የአፈር ለምነት ማስጠበቅ ስራዎች ትኩረት ይደረጋሉ ብለዋል።
ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አበራ በበኩላቸው የኮንታ ዞን አብዛኛው የመሬት አቀማመጥ ተራራማና ተዳፋታማ በመሆኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሰጠ ገልፀው ይህንን ለማቀስጠል በተያዘው ዓመት በዞኑ በሥነ-ህይወታዊና ሥነ-አካላዊ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ከ56 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በማሳተፍ 22 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱን አስረድተዋል።
የዘንድሮው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ “የአፈር ጤንነት ለሀገር ህልውና” በሚል መሪ ቃል ሲሰራ ሁለገብ ጠቀሜታ የሚሰጡ ችግኞች ጭምር የሚተከሉበት እንደሆነም አንስተዋል።
በሀገራችን የተፋሰስ ልማት ከጀመረበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደሆነም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ አብዮት እሸቱ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ