የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በማሳለጡ በኩል የሚስተዋሉ የማሽን እጥረቶችን ለመቅረፍ እየሰራ ነው – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት
ሀዋሳ፡ ጥር 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በማሳለጡ በኩል የሚስተዋሉ የማሽን እጥረቶችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡
ክልሉ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ ግሬደር ማሽኖችን በክልሉ ለሚገኙ የመንገዶች ባለስልጣን ዲስትሪክት ጽ/ቤቶች አስረክቧል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በክልሉ በሚገኙ ዲስትሪክቶች የሚገኙ ማሽኖች ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ከመሆናቸዉ የተነሳ በክልሉ ያለዉን የመንገድ ፍላጎት ለማሟላት አዳጋች ሆነው ቆይተዋል ብለዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም ተገዝተዉ በነባሩ በክልሉ የነበሩ 3 የግሬደር ማሽኖች ሳይከፈሉ የቆዩ ዕዳዎችን ጨምሮ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ወጪ በማዉጣት በካፋ፣ ዳዉሮና ሚዛን ለሚገኙ የመንገዶች ባለስልጣን ዲስትሪክት መስሪያ ቤቶች ማስረከብ ተችሏል ብለዋል።
ለዲስትሪክቶቹ የተሰጡ ማሽኖችም በክልሉ የሚስተዋለዉን የመንገዶች ጥግግት ክፍተትን በአጭር ጊዜ ለማስተካከል አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዉ ጽ/ቤቶቹ ማሽኖቹ ላልተገባ ብልሽት እንዳይዳረጉ በጥንቃቄ ሊይዙ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ መንግሥትም ተጨማሪ ማሽነሪዎችን በመግዛት የዲስትሪክቶችን አቅም በማሳደግ በክልሉ የሚነሳዉን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የክልሉ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብዲዩ መኮንን በበኩላቸው አሁን የተገኘዉ ዕድል ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ በርካታ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ለማጠናቀቅ አቅም የሚፈጥር ነዉ ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም ካለው ውስን ሀብት ቀንሶ የማሽን ድጋፍ ማድረጉ ለመንገድ ስራዎች የተሰጠዉን ትኩረት የሚያሳይ በመሆኑ ለተደረገዉ ድጋፍም ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።
የማሽን ድጋፉን ካገኙ ዲስትሪክቶች መካከል የቦንጋ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸዉ ጊጅ በዲስትሪክቱ የሚገኙ ማሽኖች ከ15 ዓመታት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸዉ ህብረተሰቡን በማስተባበርና መንግስት በሚሰጠዉ ድጎማ የጥገና ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸዉን ጠቁመዋል።
ይህም ስራዎችን በተቀመጠላቸዉ ጊዜ ለማከናወን ችግር ሆኖ መቆየቱን ገልጸዉ አሁን የተገኘዉ ድጋፍ በዲስትሪክቱ የሚታየዉን የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ በአጭር ጊዜ መፍታት ያስችላል ብለዋል።
የሚዛን ዲስትሪክት ስራ አስኪያጂ አቶ አሸናፊ ወልዴ በበኩላቸዉ የተደረገዉ ድጋፍ በአጭር ጊዜ ብዙ ኪሎ ሜትር መንገዶችን ለመስራት የሚያግዛቸዉ መሆኑን ተናግረዋል።
ስራ አስኪያጆቹ የተሰጣቸዉ ማሽን አዲስ እንደመሆኑ ለብልሽት ሳይዳረግ በአግባቡ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የሚያስተዳድሩ መሆናቸዉን ተናግረዉ ለተደረገላቸዉ ድጋፍም ለክልሉ መንግስት ምስጋናቸዉን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ በአሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ