በዘንድሮው የበጋ ወቅት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ 78ሺህ 6መቶ ሄ/ር በላይ መሬት በስነ አካላዊና ስነህይወታዊ ስራዎች ለማልማት ታቅዷል – የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ
ሀዋሳ፡ ጥር 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮው የበጋ ወቅት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ 78ሺህ 6መቶ ሄ/ር በላይ መሬት በስነ አካላዊና ስነህይወታዊ ስራዎች ለማልማት መታቀዱን የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በአፈርና በውሃ ጥበቃ ስራ ከ5መቶ 15ሺህ በላይ የህበረተሰብ ክፍሎችና አደረጃጀቶች እንደሚሳተፉና ስራውም የሚከወንበት 3መቶ 11 ንዑስ ተፋሰሶች ልየታ መደረጋቸው ተመላክቷል።
የሀዲያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ተረፈ የ2016 ዓ.ም የበጋ ወቅት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በሀገሪቱ ብሎም በዞኑ ለረጅም ዓመታት ሲተገበር የቆየ መሆኑን አንስተው ለዓመታት ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ውስንነቶች ይታያሉ ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት አዳዲስ ስትራቴጂዎችን በመንደፍና አሰራሮችን በማሻሻል ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ፀጋዬ በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር እንዲሁም የምንጮችን መጠን ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች በተገቢው ባለመከወናቸው የአየር ንብረት መዛባት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት፣ ምርትና ምርታመነት መቀነስ፣ የአከባቢ መራቆትና መሰል ችግሮች ዓለማችንና ሀገራችንን እየተፈታተነ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት።
በመሆኑም በዞኑ በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ78ሺህ 6መቶ በላይ ሄ/ር መሬት የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚሰራና ለትግበራውም 3መቶ 11 ንዑስ ተፋሰሶች በጥናት ልየታ መደረጋቸውን አውስተዋል አቶ ፀጋዬ።
ለትግበራው የተለያዩ ንቅናቄዎች ተከሂደው የእርሻ መሳሪያ ዝግጅት መደረጉንና በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ ለአረንጓዴ አሻራ ልዩ ትኩረት መስጠት የሚጠበቅ ነው ብለዋል።
በተፋሰሱ ስራ በአጠቃላይ 5መቶ 15 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉ ሲሆን በዚህም ዕድሜያቸው የደረሱ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶአደሮች፣ ምሁራን እና ሌሎች አደረጃጀቶችም በንቃት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀምን በማስፈን ለግብርና ልማት ምቹ የአከባቢ ሁኔታ ለመፍጠርና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ ሁሉም ለትግበራው ውጤታማነት የበኩሉን ድርሻ እንዲያበረክት ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ