ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ እናቶች በጤና ተቋማት ከወሊድ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን አግኝተዋል

 ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ እናቶች በጤና ተቋማት ከወሊድ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን አግኝተዋል

በ2016 ዓ.ም ስድስት ወራት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ እናቶች የቅድመወሊድ፣ የወሊድና ድህረወሊድ አገልግሎቶችን በጤና ተቋማት ማግኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ጤናማ የእናትነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ18ኛ ጊዜ «ፍትሐዊ ተደራሽነትና ጥራት ያለው የቅድመወሊድ ክትትል በወቅቱ በማስጀመር ጤናማ እናትነትን እናረጋግጥ» በሚል መሪ ቃል ከጥር 1 እስከ ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች፣ ሕፃናት እና አፍላ ወጣቶች ጤና መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር መሠረት ዘላለም  እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ የእናቶችን፣ ጨቅላ ሕፃናትንና ሕፃናትን ሞት መቀነስ በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡

በስድስት ወራትም 4 ሚሊዮን 212 ሺህ 019 እናቶች በጤና ተቋማት አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ ከዚህም ከ1ነጥብ 3 በላይ የሚሆኑት የቅድመ ወሊድ፣ ከ1ነጥብ 2 በላይ የሚሆኑት የወሊድ እንዲሁም ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት እናቶች የድህረ ወሊድ አገልግሎት በሠለጠነ ባለሙያ በመታገዝ ያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጥር ወር የሚከበረው ጤናማ የእናትነት ወር ዋነኛ ዓላማው የእናቶችን ሕመም እና ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ዶክተር መሠረት ገለጻ፤ በሀገሪቱ ለእናቶች ሞት ሦስት መዘግየቶች መንስኤ ናቸው፤ የመጀመሪያው እናቶች የጤና ባለሙያ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ለማወቅ በመዘግየት የሚመጣ ሲሆን ለዚህም የመረጃ ክፍተትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ሁለተኛው እናቶች ወደ ጤና ተቋም ለመድረስ በሚገጥማቸው መዘግየት የሚከሰት ሞት ሲሆን የትራንስፖርትና የመንገድ አለመኖር እና የጤና ተቋማት ተደራሽነት ተጠቃሽ መንስኤዎች ናቸው፡፡ ሦስተኛው መዘግየት እናቶች ጤና ተቋም ከደረሱ በኋላ አገልግሎት ለማግኘት በሚገጥማቸው መዘግየት የሚከሰት ሞት ነው፡፡ የሕክምና ግብዓት እጥረት፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎት በጤና ተቋማት አለመኖርና የአገልግሎት ጥራት እንደችግር የሚነሱ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት በወሊድ ጊዜ እና ከወሊድ በኋላ የደም መፍሰስ፣ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰት ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ንጽህናውን ያልጠበቀ ፅንስ-ማቋረጥ፣ ኢንፌክሽን እና የደም ማነስ፣ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ከፍተኛ የደም መፍሰስና የደም አቅርቦት እጥረት ለእናቶች ሞት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አብራርተዋል፡፡

ዶክተር መሠረት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ በላይ የመንግሥት ጤና ተቋማት የወሊድ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ከ18 ሺህ በላይ ጤና ኬላዎች በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ የጤና ሥርዓቱን ለማዘመንና ተደራሽ ለማድረግም ብቁ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በመሆኑም ከቅድመ ወሊድ የሥነ ተዋልዶ ጤናንና መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ ከወሊድ በኋላ ለእናት እና ለተወለደው ልጅ የጤናና የምክረሃሳብ አገልግሎትን በሠለጠነ ባለሙያ ማግኘት ወሳኝ ነው ብለዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡

እ.ኤ.አ በ2020 የሀገሪቱ የእናቶች ሞት መረጃ መሠረት በሕይወት ከሚወለዱ ከ100 ሺህ ጨቅላ ሕፃናት መካከል 267 እናቶች ሕፃናት ይሞታሉ፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ይህንን ቁጥር ከ140 በታች ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሠራም ዶክተር መሠረት አስታውቀዋል፡፡ የእናቶችን፣ ጨቅላ ሕፃናትንና ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ በጥር ወር በሚከበረው የጤነኛ እናቶች ወር ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡