የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል እንዲሆን የባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ወንድሙ ኩርታ ገለጹ
በክልሉ ተርጫ ከተማ በገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ አስረጂና የባለድርሻ አካላት የጋራ ውይይት አካሂደዋል።
ነባሩ አዋጅ ለ19 ዓመታት ያህል ሥራ ላይ የዋለ ሲሆን ሰፊ ጉድለቶች ያሉበት፣ አሳሪ ሕግና የሁሉንም ተጠቃሚነት ያረጋገጠ አዋጅ ባለመሆኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር በአዋጁ ጉድለት ቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉትን ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል እና ለወደፊቱ የተሻለውን ዕድል ለመፍጠር አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል።
በመሆኑም የሚሻሻለው አዋጅ 4 ክፍሎችና 66 አንቀጾች ያሉት ነው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ አቶ አሰፋ ሻረው ለተሳታፊዎች እንዳብራሩት በሚሻሻለው አዋጅ አንድ አርሶአደር የያዘውን ይዞታ ለዓመታዊ ሰብሎች እስከ 10 ዓመት እንዲሁም ለቋሚ ሰብሎች እስከ 30 ዓመት ድረስ የሚያከራይ ሲሆን የኮንትራት የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ ይዞታው የአከራዩ ይሆናል።
መሬትን መሸጥና መለወጥ የማይቻል ሲሆን የያዘውን ይዞታ አግባብ ባለው ሁኔታ አስይዞ ከባንክ ለምርትና ምርታማነት እገዛ የሚያግዙ ነገሮችን ለማሟላት ከባንክ ገንዘብ መበደር እንደሚችለው ያትታልም ብለዋል።
በሚሻሻለው አዋጅ ከተካተቱት ውስጥ ሴቶችና ድጋፍ ለሚሹ አካላት መብታቸውን በብቃት እንዲጠቀሙ የሚያግዝ ሲሆን ምናልባት በአባወራው በኩል ድርብ ጋብቻ የሚፈጸም ከሆነ ሴቷ ከይዞታው 50 እጅ የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ እንድትወስድ ያግዛታል።
ከሃይማኖት ተቋማት እና ከወል ይዞታ ጋር የነበሩ ችግሮችን በመለየት እንዲሁም በኩታ ገጠም እርሻን በማስፋፋት በጋራ ለማምረት ዕድል እንዲሰጥ ተደርጎ አዋጁ መረቀቁም ተብራርቷል።
ከገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚታየውን ሕገወጥነትን ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ተጠቅሷል።
በሕገወጥነት ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን የፍትሕ ተቋማት ውግንና ለዜጎች ተጠቃሚነት እንዲሆን ያስችላልም ተብሏል።
የመሬት ባለቤትነት የሕዝብና የመንግሥት በመሆኑ የገጠር መሬት የይዞታ ባለቤትነት የአርሶና የአርብቶ አደሮች ይሆናል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ መለሰ መና በበኩላቸው የሚሻሻለው አዋጅ ዓላማ አሁን ላይ የሚታየውን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በመቅረፍ አርሶ አደሩን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግና የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠቀም የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ወንድሙ ኩርታ ለተሳታፊዎች እንደገለጹት የሚሻሻለው አዋጅ ለማከራየት፣ አስይዞ ከባንክ ለመበደር፣ የመሬት ይዞታ ባለቤትነትን ለማረጋገጥ፣ በጋራ አልምቶ ለመጠቀምና የሴቶችን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ ጸድቆ ሲቀርብ የክልሉ ምክር ቤት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ለተግባራዊነቱ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል።
ውይይቱም ለሚሻሻለው አዋጅ ግብአት ለመሰብሰብ የሚያግዝ መሆኑንና ስኬታማ እንደሆነም ገልጸዋል።
ከተሳታፊዎች መካከል ከዳዉሮ ዞን የተገኙ ሼክ ማቴዎስ ማሞና ከከፋ ዞን የመጡ አርሶ አደር ወልደየስ ወልደማርያም ከውይይት መድረኩ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠሪያ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይ ጸድቆ ሲቀርብ የዜጎችን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም ያላቸውን እምነት አስረድተዋል።
በውይይቱም አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሲቪክና ማህበራትና ኢንቨስተሮች፣ የሕግና የመሬት አስተዳደር ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የዞንና የወረዳ ምክር ቤት አባላት ተሳታፊ የሆኑበት የውይይት መድረክ መሆኑን ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።
ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ