የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የመሬት ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የመሬት ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የመሬት ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል።

በዳውሮ ዞን የ2016 ምርት ዘመን የተፋሰስ ልማት ስራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በማረቃ ወረዳ ጎቦ ሻመና ቀበሌ በዋሼ ንዑስ ተፋሰስ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የዳውሮ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ሀላፊ ረዳት ፕሮፌሰር በተላ በየነ፤ የተፋሰስ ልማት ስራ ለም አፈር በጎርፍ፣ በንፋስ እና በዝናብ ታጦቦ እንዳይወሰድ ለመከላከልና የአፈር ለምነት ተጠብቆ እንድቆይ ከማድረግ ረገድ ያለው ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የተራቆቱ አከባቢዎች መልሰው ለማልት የተፋሰስ ልማት ስራ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

በዞኑ በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ ከ 26 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት እንደሚለማ ሀላፊው ጠቁመዋል።

ለዚህ ስራ ከ 2መቶ 71ሺህ በላይ የህረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።

ለተከታታይ 30 ቀናት በሚቆየው በዚህ የተፋሰስ ልማት ስራ የአከባቢው ህብረተሰብ ክፍሎች በነቂስ በመሳተፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ረዳት ፕሮፌሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት የብልፅግና ፓርቲ የሰው ሀብት መምሪያ ሀላፊ አቶ አክሊሉ ሀይሉ በበኩላቸው የተፋሰስ ስራ ወጤታማ እንዲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ የታየው ተነሳሽነት የሚደነቅ እንደሆነ አንስተው ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ አካባቢን ለማውረስ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የዳውሮ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታሪኩ አካሉ በበኩላቸው፤ የተፋሰስ ስራ ዋና ዓላማ የእርሻ መሬት ለምነት ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግና የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚያበረክተው አስተዋዕኦ ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል።

የማረቃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ዶ/ር ሀብታሙ ደምሴ በበኩላቸው፤ ለሀገራችን የግብና ስራ  ጀርባ አጥንት ስለሆነ ስራው ውጤታማ እንዲሆን የተፋሰስ ልማት ስራ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል። 

አስተያየታቸውን ያጋሩ ተሳታፊዎች ከዚህ በፊት በተሰሩ ስራዎች ላይ የበኩላቸውን አስተዋዕኦ ማበርከታቸውን አስታውሰው ለሚቀጥሉት 30 ቀናት በሚቆየው የዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አማኑኤል ተገኝ – ከዋካ ቅርንጫፍ