በአገሪቱ የሚገኘውን የገጠር መሬት ምዝገባና ቅየሳ ሥራ አንድ ወጥ ሆኖ በክልሎች እንዲፈጸም የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

በአገሪቱ የሚገኘውን የገጠር መሬት ምዝገባና ቅየሳ ሥራ አንድ ወጥ ሆኖ በክልሎች እንዲፈጸም የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የሕግ አውጪው መቀመጫ በሆነችው ተርጫ ከተማ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 456/1997 ታውጆ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ 19 ዓመታትን አስቆጠሯል።

በመሆኑም አገሪቱ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ እንዲሁም የአርሶና አርብቶ አደሩ ገቢ እያደገ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በመሬት ላይ ያላቸው የመጠቀም መብትን ማሻሻያ እንዲደረግ አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሯል ተብሏል።

የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃን በማደራጀት የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለመቅረፍ፣ ለተጠቃሚዎች የባለቤትነትን ስሜት በመፍጠር መሬቱን በአግባቡ እንዲያለሙ ለማስቻል፣ የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት በማልማትና በመጠቀም ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲያግዝ ለማስቻል አዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አስፈልጓል የሚል ሀሳብ ተነስቷል።

በተለይም ለሴቶችና ድጋፍ ለሚሹ አካላት መብታቸውን በብቃት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ዕድል እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ ለአዋጁ ማሻሻያ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ መለሰ መና ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው የገጠር መሬት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማስቻል የባለ ድርሻ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

በክልሉ የሚገኘው የገጠር መሬትና የተፈጥሮ ሃብትን ጠብቆ ለማቆየት ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገው የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ወሳኝ በመሆኑ አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የሲቪክና ማህበራትና ኢንቨስተሮች፣ የሕግና የመሬት አስተዳደር ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና የየዞንና የየወረዳ ምክር ቤት አባላት ተሳታፊ የሆኑበት የውይይት መድረክ መሆኑን ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

ዘጋቢ፡ መሣይ መሠለ – ከዋካ ጣቢያችን