በታክስ ህግ ተገዥነት ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ከተማዉ የሚያመነጨዉን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ተገለፀ
በታክስ ህግ ተገዥነት ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የከተማዉ የሚያመነጨዉን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ተገልጿል::
ይህ የተገለፀዉ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በታክስ ተገዥነት ላይ ከደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የንቅናቄ መድረክ በተካሄደበት ወቅት ነዉ::
በንቅናቄ መድረኩ ላይ በእንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትልና የታክስ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተስፋዬ አሰፋ የክልሉ መንግስት ካቀዳቸዉ የመቶ ቀናት ዕቅድ ዉስጥ የመጀመሪያ ዙር ግምገማ ካደረገባቸዉ ዝርዝር ተግባራት መካከል አንዱ የታክስ ህግ ተገዥነት ችግር ነዉ ብለዋል::
በመሆኑም የታክስ ስርዓትን ከማዘመን አኳያ ቴክኖሎጂን መጠቀም ወሳኝ ተግባር ነዉ ያሉት አቶ ተስፋዬ ይህም የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በመግዛት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግብይቱን እንዲፈፅም ማድረግ እንደሚገባ አብራርተዋል::
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት አመታት በዞኑ በተደረገዉ ጥናት መሰረት 95 ከመቶ የሚሆነው የንግዱ ማህበረሰብ ደረሰኝ እየሰጠ እንዳልሆነ ገልፀዋል::
የገቢ አቅምን ለማሳደግ የአካባቢዉን ሰላም ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጥ ተግባር ነዉ ያሉት አቶ ላጫ ይህም ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለንግድ መስፋፋት ሚናዉ የጎላ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም አካላት የህገ ወጥ ንግድን በመከላከል ከመንግስት ጎን መቆም እንደሚገባ አሳስበዋል::
የህዝቡ የልማት ጥያቄ ሊመለስ የሚችለዉ የንግዱ ማህበረሰብ ገቢዉን በማሳወቅ የሚጠበቅበትን ግብር መክፈል ሲችል እንደሆነ የገለፁት ደግሞ የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታዉ ናቸዉ::
በታክስ ህግ ተገዥነት ሂደት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመፍታት የከተማዉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨዉን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ነዉ ከንቲባዉ የገለፁት::
በከተማዉ አገልግሎት ተጠቃሚዉ ህብረተሰብ ደረሰኝ በመጠየቅ የድርሻዉን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል::
በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት ባለድርሻ አካላትና የንግዱ ማህበረሰብ በሰጡት አስተያየት በታክስ ተገዥነት ስርዓት ላይ በቂ ግንዛቤ መፈጠር አለበት ነዉ ያሉት::
በተለይም የመብራትና የዉሀ መቆራረጥ ችግሮች ላይ ትኩረት መደረግ እንዳበት የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ ግብር መሰወር የትዉልድ ተስፋ መስረቅ በመሆኑ የሚጠበቅብንን ግብር በአግባቡ በመክፈል ሀገራዊ ግዴታችንን እንወጣለን ሲሊ ገልፀዋል::
ዘጋቢ፡ ብርሀኑ ማሞ – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ