ክልሉ ከዚህ ቀደም የነበረውን 4 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወደ 8 መቶ ሚለዮን ማውረድ መቻሉን – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገለጸ

ክልሉ ከዚህ ቀደም የነበረውን 4 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወደ 8 መቶ ሚለዮን ማውረድ መቻሉን – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 23/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ክልሉ ከዚህ ቀደም የነበረውን 4 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወደ 8 መቶ ሚለዮን ማውረድ መቻሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገልጿል፡፡

ከነባሩ ክልልም ሆነ ከአሰራር ጉድለቶች ጋር ተያይዞ የመጣውን 4 ቢሊዮን ብር ዕዳ በትጋት በመሠራቱ ወደ 8 መቶ ሚለዮን ማውረድ መቻሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሴክቶሪያል ጉባኤ ላይ ተሳታፊ በመሆን አስተያየታቸውን የሰጡት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ም/ቤት የበጀት፣ ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ የኋላሸት በላይነህ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ ተቋሙን ከዓመት ወደ ዓመት በአሠራር ሂደትም ሆነ በአፈጻጸም የተሻለ ቁመና ላይ ይገኛል ብለዋል።

በሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተው በዞኖችና በወረዳዎች ላይ ያሉት ዕዳዎች በግልጽ መቅረባቸው ተቋሙ የአሠራር ግልጸኝነትንና ተጠያቅነትን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ያመለክታል ያሉት ወ/ሮ የኋላሸት ዕዳዎችን ለማስመለስ ከዞን እስከ ወረዳ የብድር አስመላሽ ግብረ ሃይል አቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተለይ የግብዓትና የጡረታ ዕዳዎች ከአሰራር ክፍተትና ከቅንጅት ጉድለት የመጡ በመሆናቸው የአሠራር ዝንፈትን በማረም ተቋማቱ ወደ ተሻለ ምዕራፍ መሸጋገር እንዲችሉ በየደረጃው የሚገኙ የም/ቤቶች የበጀት፣ ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች የክትትል ድጋፍ ተልዕኮአቸውን መወጣት አለባቸው በማለት አሳስበዋል።

የኦዲት ሥራዎች እየተጠናከሩ መምጣታቸው ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከብልሹ አሰራር በመውጣት የፋይናንስ ደምብ፣ መመሪያዎችንና አሰራሮችን በመተግበር በአሰራር ዝንፈት ከሚመጣው ተጠያቂነት ነጻ መውጣት እንዲችሉ የማንቂያ ደወል መሆኑን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።

የተቋቋመው የዕዳ አስመላሽ ግብረ ሃይል የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ መወጣት እንዲችል የድጋፍና የክትትል ሥራዎች ሊጠናከሩ ይገባል ያሉት ወ/ሮ የኋላሸት ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመሻገር የሚደረገውን የልማት ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ሚናውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

ክልሉ በርካታ የዕዳ ጫናዎችን ተቋቁሞ የፋይናንስ አሰራርና ደምቦችን ተግባራዊ በማድረግ የልማትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ መንግስት ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ ናቸው።

ከነባሩ ክልልም ሆነ ከአሰራር ጉድለቶች ጋር ተያይዞ የመጣውን 4 ቢሊዮን ብር ዕዳ በትጋትና በቅንጅት በመሠራቱ ወደ 8 መቶ ሚለዮን ማውረድ መቻሉን የተናገሩት ወ/ሮ ወሰነች ሙሉ በሙሉ ክልሉን ከዕዳ ነጻ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ዕዳዎቻቸውን በወቅቱ ከፍለው ነጻ የሆኑ ዞኖችና ወረዳዎች ሊመሰገኑ ይገባል ያሉት ኃላፊዋ ያሉንን ጸጋዎች ተጠቅመን ሐብት በማካበት የክልሉ ሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ በቁርጠኝነት መስራት የሁላችን ድርሻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የግብርናን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የማዳበሪያ ግብዓት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ አርሶአደሩ ከዕዳ ነጻ እንዲሆን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የማዳበሪያ ሽያጭ እጅ በእጅ ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት የኮንታ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አግደው አሰፋ ናቸው፡፡

ዞኑ ከዚህ ቀደም ተያይዞ ከመጣው ዕዳ ነጻ መውጣት እንዲችል ከ2014 ዓ.ም በጀት ከፍለው ነጻ መውጣታቸውን የገለጹት አቶ አግደው ዕዳዎቹ በክልሉ ውስን ሐብትና ልማት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መኖሩን ጠቁመው ተቀናጅቶ መከወን እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን