ቢ ኤች 140 የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በ50 ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ለመሸፈን አቅዶ እየሰራ መሆኑ ተጠቆመ

ቢ ኤች 140 የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በ50 ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ለመሸፈን አቅዶ እየሰራ መሆኑ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ጥር 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሳውዝ አግሮ ኢንዱስትሪ ቢ ኤች 140 የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በ50 ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ለመሸፈን አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ እንቨስትመንቶች ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል መመዝገቡን የጋሞ ዞን እንቨስትመንት መምሪያ አመላክቷል።

ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ 2 መቶ ሄክታር መሬት ለእንቨስትመንት ተረክቦ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን በማልማትና በማምረት ለአካባቢና ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረበ መሆኑን የሳውዝ አግሮ ኢንዱስትሪ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ገቢሳ ተናግረዋል፡፡

ቢ ኤች 140 የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት በ50 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለመሸፈን አቅደው 30 ሄክታር መሸፈናቸውን አቶ ከበደ ተናግረው ቀሪውን 20 ሄክታር ለመሸፈን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት አርሶ አደሩ የምርጥ ዘር እጥረት ገጥሞት ከሌሎች ክልሎች እየመጣ መቆየቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደ ሀገር የምርጥ ዘር ብዜት ማዕከል ሆነው ለመስራት ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

ሁለት ወር ተኩል ዕድሜ ያስቆጠረውን የበቆሎ ሰብል ከተባይ ነፃ የማድረግ፣ ውሃን ተከታትሎ የመስጠትና ምርጥ ዘር ብዜቱን የማድረስ ስራ እየሰሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ከበደ፥ ግብርናውን አዘምኖ 40 እና 50 ኩንታል በሚመረትበት መሬት ላይ 150 ኩንታል በሄክታር ማምረት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በ25 ቋሚና ኮንትራት እንዲሁም ለ200 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ እድል መፈጠሩን የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ ለአርሶ አደሩ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተደርጓል ብለዋል፡፡

በመንግስት በኩል ይሁን በግል የአካባቢውን ህብረተሰብ በመሰረተ ልማት ዝርጋታና በሌሎች ደራሽ ስራዎች መደገፋቸውን የተናገሩት አቶ ከበደ፥ በሙሉ አቅማቸው ተጠቅመው አስፍተው ለመስራት የመንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡

የሥራ እድል የተፈጠረለት ወጣት አብነት ኢዮብ እንደተናገረው በፊት ከነበረው ህይወት ትልቅ ለውጥ በማሳየቱ ቤተሰቡንም እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጾ ሳውዝ አግሮ ኢንዱስትሪ ስራውን አስፍቶ እየሰራ ይገኛል ብሏል፡፡

የኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ከሚያለሙ ሁለት ኢንቨስትመንት ማሳዎች ሃምሳ ሃምሳ ሄክታር እንዲቀንስ እንዲሁም ከአንድ ኢንቨስትመንት ሙሉ በሙሉ እንዲወርስ መደረጉን የገለጹት የብርብር ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባና የኢኮኖሚክ ክላስተር ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ወ/ዮሐንስ በመስኖ ወይም በኤሌክትሪክ ሳይሆን በነዳጅ ወጪ በከባድ ውሃ ፖምፕ ለሚሰሩ ግብርና እንቨስትመንቶች በጋራ በመመካከር የመብራት ዝርጋታ መከናወን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ እንቨስትመንቶች መኖራቸውን የተናገሩት የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ም/ኃላፊና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻምበል ቦኩ ሳውዝ አግሮ ኢንዱስትሪ የምርጥ ዘር ብዜት ማዕከል ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ እንቨስትመንቶች 5 ቢሊየን 791 ሚሊየን 344 ሺህ 267 ብር ካፒታል መመዝገቡን የገለጹት የጋሞ ዞን እንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ግርማ ከዚህ ውስጥ 2 ቢሊየን 581 ሚሊየን 585 ሺህ 37 ብር በስራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ሰሎሞን አላሶ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን