ህብረተሰቡ ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የየም ዞን የሳጃ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቅርጫፍ ጽ/ቤት አሳሰበ

ሀዋሳ፡ ጥር 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ህብረተሰቡ ግብርን በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ለሀገር ዕድገት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባው የየም ዞን የሳጃ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቅርጫፍ ጽ/ቤት አሳስቧል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በዛሬዉ ዕለት “ደረሰኝ በመቀበል ለሀገሬ ዕድገት የድርሻዬን እወጣለሁ” በሚል መሪ ቃል በታክስ ተገዢነት ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ በሳጃ ከተማ አካሂዷል።

የንቅናቄ መድረኩን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ገ/ሚካኤል እንደገለፁት፤ ሀገራችን የጀመረችዉን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ገቢን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ይጠበቃል።

በየም ዞን የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ ለዞኑ ዕድገት እያበረከቱ ያለዉን አበረታች ተግባርም አመስግነዋል።

ህዝቡ እየጠየቀ ያለዉን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችኖ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የገቢ አሰባሰብ ሥራ የህልዉና ጉዳይ ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አቶ ሳሙኤል አሳስበዋል።

የየም ዞን ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሃም ዝናብ እንደተናገሩት፤ እንደ ዞን፣ክልልና ሀገር የተጀመረዉ የብልጽግና ጉዞ እዉን እንዲሆን የጀርባ አጥንት የሆነዉን ግብርን አሰባሰብ ዙሪያ ተግባቦት በመፍጠር እና በታማኝነትና በወቅቱ እንዲከፈል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል።

የሳጃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጌታሁን ካሳሁን በበኩላቸዉ በሳጃ ከተማ አስተዳደር መንግስት ላቀዳቸዉ የልማትና መልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ እራሱን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ግብርን በወቅቱና በታማኝነት እንዲከፍል በማድረግ የተሻለ ሥራ እየተሰራ ያለዉን ተግባር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የዞኑን ገቢ ዕድገትና አሰባሰብ ለመደገፍ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አሰፋ እንደገለፁት፤ የየም ዞን ገቢን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ያለዉ አበረታች ተግባር ይበልጥ በዘመነ መንገድ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ሁሉም በየደረጃዉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግብርን በታማኝነት ለመንግስት በመክፈል ከመንግስት ጎን መቆም እንዳለባቸዉ መልዕክታቸዉን አሰተላልፈዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ በየም ዞን ገቢዎች ባለሥልጣን መምሪያ የደንበኞች አገልግሎት ታክስ አወሳሰን፣ አሰባሰብና ዕዳ ክትትል ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ ጌታቸዉ ወልደ የገቢ አዋጅ ሰነድ አቀርበዉ ዉይይት ተደርጓል።

በቀረበዉ አዋጅ ላይ ሰፊ ዉይይት በማድረግ፣ አስተያየት በመስጠት፣ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት የጋራ ተግባቦት ተፈጥሯል።

በቀጣይ ጊዜያት በህገወጥ ንግድ ቁጥጥር፣በግብር ስወራ፣በደረሰኝ ግብይት አተግባበር ፣ በምርት ስወራ፣በመሰረተ ልማት አቅርቦት እና ሌሎች ተግባራት ዙሪያ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የንቅናቄ ተሳታፊዎች መጠቆማቸውን ከየም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልል ገቢዎች ቢሮ ተወካይና ምክትል ኃላፊ ጨምሮ የየም ዞን እና ሳጃ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የ3ቱም ሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣የሳጃ ከተማ አስተዳደር ደረጃ “ሀ” እና ደረጃ “ለ”” ግብር ከፋይ ነጋዴዎች፣ የሳጃ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀት ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።