በግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የታክስ ህግ ተገዥነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተገለፀ

በግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የታክስ ህግ ተገዥነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ተገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት በታክሲ ህግ ተገዥነት ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የመንግስትን ግብር መሰወርና ማጭበርበር ለታክስ ህጉ ተገዥ ካለመሆን የሚመነጭ ህገወጥ ተግባር ነው።

በታክስ ህጉ ተገዥነት ዙሪያ ከዚህ ቀደም የተስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት ግንዛቤ በመስጠት ግብርን በተገቢው ለመሰብሰብና ግብር ከፋዩንም ከተጠያቂነት ማዳንን ዓላማ በማድረግ የተዘጋጀ መድረክ ሰለመሆኑ የሆሳዕና ከተማ አስተዳዳር ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፀጋነሽ ዮሐንስ በወወያያ ጽሑፉ ገልፀዋል።

ለታክስ ህጉ ተገዥ ካለመሆን የተነሳ ግብርን መሰወርና ማጭበርበር ግብይትን ያለደረሰኝ በማካሄድ፣ ሀሰተኛ ደረሰኝ መጠቀም፣ የገቢ ተቋም ባለሙያዎችን በጥቅም በመደለል፣ ህገወጥ ንግድ በመስፋፋቱና ሌሎችም የታክስ ስርዓቱን የሚፈታተኑ ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቀጣይ ብርቱ ክትትል በማድረግ የታክስ ህጉን በሚጥሱ አካላት ጠንካራ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን በመጠቆም።

መድረኩን የመሩት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ የመንግስትን ግብር በታማኝነት መክፈል በህግም በሃይማኖት አስተምሮ ዘንድም መልካም ተግባር አንደሆነ አስገንዝበዋል።

ሁሉም ግብር ከፋይ ለታክስ ህጉ ተገዥ የመሆን ግዴታ አለበት ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በግብር አሰባሰብ ሂደቱ ህገወጥነትን ህጋዊ ስርዓት ለማስያዝ ከፍትህ ተቋማት ጋር በሚደረግ እንቅስቃሴ የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ ሁሉም ባለድርሻ መተባበር እንዳለበትም አሳስበዋል።

በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የገቢዎች ቢሮ የደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደግፍ መለሰ በበኩላቸው ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ በተገቢው ለመሰብሰብ እንዲቻል ከታክስ ህግ ተገዥነት አንፃር የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሸፈን የንቅናቄ መድረኩ አጋዥ ነው ብለዋል።

ለንግድ ስርዓቱ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት በየደረጃው እንደሚሰራም ገልፀዋል።

ግብርን መሰወርና ማጭበርበር ሌብነት ነው፤ ሌብነት ደግሞ ክብርን መጣል፣ ህግን መናቅና ህገወጥነትን ማስፈን በመሆኑ ሀሉም ግብር ከፋይ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ያሉት ደግሞ የሆሳዕና ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አቶ ሊሬ ጀማል ናቸው።

በመድረኩ የተሳተፉ ግብር ከፋዮችም በተለይ በአዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች የሚገኙ አንዳንድ የጅምላ ዕቃ አቅራቢ ነጋዴዎች ላይ የሚታይ የደረሰኝ አቆራረጥ ችግርና በመግቢያና መውጫ መንገዶች ላይ አልፎ አልፎ የሚታይ የፀጥታ ችግር መፍትሄ አንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ግብር ከራስ ለራስ የሚከፈል ገቢ በመሆኑ ለታክስ ህጉ ተገዥ በመሆን ግብርን በታማኝነት እንደሚከፍሉ ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ግብር ከፋዮች፣ የፍትህ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የገቢ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን