የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የውይይት መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው

ሀዋሳ: ጥር 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምሥራቅ ጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው::

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የምሥራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን፤ የቡታጅራ ከተማ ከአስር አመት በፊት ከአንድ ያልበለጠ የኮብልስቶን መንገድ እንደነበራት አስታውሰው አሁን ላይ ግን በርካታ የውስጥ ለውስጥ የአስፋልት እና የኮብልስቶን መንገዶች መሠራታቸውን ገልፀዋል::

አሁን ከተማዋ የዞን መቀመጫ እና የክልሉ አንዷ የማእከል ከተማ መሆኗ መልካም እድሎች መሆናቸውን ተናግረዋል::

በከተማዋ የሚገኙ አብዛኞቹ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን የሚወጡ ቢሆንም አሁንም የግንዛቤ ክፍተቶች እንዳሉ ነው የገለፁት::

የውይይት መድረኩ ዋና ዓላማም ግብር በአግባቡ የሚከፍሉትን ለማበረታታት እና የሞዴል ግብር ከፋዮችን አርአያነት ለማስፋትና ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብለዋል::

ግብር ከፋዩ ከግንዛቤ እና ከደረሰኝ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት ከቻለ በመንግስትና ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጫና መቀነስ የሚቻል መሆኑን አስገንዝበዋል::

መንግስት ውሃ፣ መብራ፣ መንገድና ሌሎችንም ልማቶችን የሚሰራው በግብር ከሚገኘው ገንዘብ በመሆኑ ግብር ከፋዮች ይህን ተገንዝበው ሀገራዊ እና የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል::

ለግብር ከፋይነት አለመመዝገብ፣ ተመዝጋቢ የሆኑትም ያለደረሰኝ ግብይት የመፈፀም፣ ታክስ በወቅቱ አስታውቆ አለመክፈል እና የሐሰት ሰነድ ማዘጋጀት በግብር ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች መሆናቸውን በጥናት መለየቱም ተገልጿል::

በውይይት መድረኩ የከተማ አስተዳደር፣ የዞንና የክልሉ መንግስት የሥራ ኃላፊዎች እና የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች ተገኝተዋል::

ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ