የእንሰት ምርት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለው ድርሻ የጎላ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ማልማት እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ጥር 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የእንሰት ምርት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለው ድርሻ የጎላ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ማልማት እንደሚገባ ተጠቁሟል።
“እንሰትን መትከል የኑሮ መድህን ዋስትና ነዉ” በሚል መሪ ቃል የ2016/17 ምርት ዘመን የእንሰት ልማት ንቅናቄ መድረክ በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ ተካሄዷል።
በሸካ ዞን የማሻ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተገኙት የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር በእዉቀቱ ኃይሌ እንሰትን የሚመለከት ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በጥናታቸውም ሰብሉ የተለያየ አየር ፀባይን መቋቋም የሚችል ከመሆኑ በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ በመቆየት የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ከማስጠበቅ አንጻር ጉልህ ሚናን እንደሚጫወት አንስተዋል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ ቀድሞ በስፋት በሚታወቅበት በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ ላይ በአጭር ወራት መድረስ ለሚችሉ አትክልቶች ትኩረት በመሰጠቱ የማምረት አዝማሚያው እየቀነሰ መምጣቱን ነዉ የተገለጸዉ።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከ25 ሚልዮን በላይ ህዝቦች ለምግብነት እንደሚጠቀሙ የሚነገርለት እንሰት ሀገር በቀል ሰብልነቱ የሚታወቅ ሲሆን በዘርፉ በርካታ ጥናቶችን በማካሄድ የተለያዩ የአለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ማስመዝገብ መቻሉን ዶክተር በእውቀቱ ጠቅሰው ምርቱ ከዚህን ቀደም ትኩረት ሰይሰጠው የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ በአገር አቀፍ ምርምር ተቋማት ጥናቶች ተደርገዉ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነዉ ብለዋል።
በተለያዩ ተቋማት የሚደረጉት ጥናቶች የአርሶ አደሩን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ እየተጠቀሙ ስለሆነ የሀገር በቀል እዉቀትን በአግባቡ መጠቀም ይገባልም ብለዋል።
እንደ ሀገር በርካታ የእንሰት ዝርያዎች ያሉ ሲሆን በሸካ ዞን አርሶ አደሮች ማሳ ደግሞ 1መቶ 23 የእንሰት ዝርያዎች ስለመኖራቸው በአርሶ አደሮች መረጋገጡንና በተለይ የእንሰት አጠዉልግ በሽታን መቋቋም የሚችሉ ዝሪያዎች በስፋት እንዳሉም ጠቁመዋል።
በሽታዉን መከላከል እንጅ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ስለማይቻል ከንክኪ በፀዳ መልኩ ነቅሎ በማቃጠል እና በመቅበር በሽታዉን መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
በተለይ ምርቱ ከደረሰ በኋላ የመፋቂያ ዕቃዎች ባህላዊ በመሆናቸዉ ወጣት ሴቶች ተሳትፎ እየቀነሰ መሆኑን መነሻ በማድረግ በቴክኖሎጅ የታገዙ የምርምር ዉጤቶች በቅርቡ ይፋ ስለሚደረጉና ጊዜና ጉልበትን የሚቆጥቡ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
በቀጣይም ይህን መሰል ስልጠናና ሌሎች ድጋፎችን እንደሚሰጡ ዶ/ር በእዉቀቱ ኃይሌ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም ያገኙትን ዕዉቀት ለራስ ከመጠቀም ባሻገር ሌሎችንም ለማስተማር ስለሚረዳ ለዚህ መዘጋጀታቸዉን ጠቁመዋል።
እንደ ማሻ ወረዳ አንድ አርሶ አደር በተያዘዉ በጀት ዓመት በትንሹ ከ30 ጀምሮ እስከ 1መቶ የእንሰት ዘር በነፍስ ወከፍ እንዲያዘጋጅ ያሳሰቡት የማሻ ወረዳ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ልሳኑ አለማየሁ ከ2018 በኋላ ቆጮን ትርፍ አምርቶ የሚሸጥ እንጅ የሚሸምት አርሶ አደር አይኖርም በሚለዉ መነሻ ከአመራር ጀምሮ ልዩ ድጋፍ ለማድረግ በጽ/ቤቱ ዕቅድ መያዙንና አርሶ አደሩም በዚሁ ልክ እንዲዘጋጅ ጥሪ መቅረቡን አውስተዋል።
ከንቅናቄ መድረኩ ከተሳታፊዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎችና ሀሳቦች በየደረጃ የሚገኙ አካላት ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በመድረኩ ላይም የሸካ ዞን ግብርና ደን አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ሀላፊ አቶ አይምሮ ደሳለኝን ጨምሮ በየደረጃዉ የሚገኙ አመራሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና ሞደል አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ፡ ታሪኩ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ