ከደረሰኝ ጋር ተይይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ህግ ማስከበር ይገባል- ስንታየሁ ወ/ሚካኤል
ሀዋሳ: ጥር 09/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ያለ ደረሰኝ ህገ ወጥ የንግድ ሥራ በሚያከናውኑ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ የክልሉን የገቢ አቅም ማሳደግ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ተናግረዋል::
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ6 ወራት አፈፃፀም እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው::
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ልማት የሚፋጠነው ጠንካራ የገቢ አቅም ሲኖር ነው ብለዋል::
የክልሉ መንግስት የገቢ አቅሙን ለማሳደግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑንም ገልፀዋል::
ባለፉት 6 ወራት የገቢዎች ሴክተር ያደረገው እንቅስቃሴና ያስገኘው ውጤትም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል::
ቅንጅታዊ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የገቢ ሥራን ተቋማት በቅንጅት እንዲፈፅሙ ማድረግ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ስንታየሁ በዚህም የክልሉን የወጪ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል አቅም መፍጠር እንደሚቻል አብራርተዋል::
እስከአሁን የማይነኩ የገቢ ርእሶች መኖራቸውን የገለፁ ሲሆን በቀጣይ በማይነኩ የገቢ ርእሶች ላይ በትኩረት መሥራት ያሻል ብለዋል::
ከታክስ ተገዥነትና ህገ ወጥነት ጋር ተያይዞ ህግ ማስከበር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል::
በከተሞች በተለይም ደረሰኝ የመስጠት ባህል ከበፊቱም ይልቅ አሁን ላይ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረው ይህን ለማስተካከል ግንዛቤ በመፍጠርና አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ህግ ማስከበር ይገባል ብለዋል::
በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ በቀጣይ የታክስ አገልግሎትን ከንክኪ ነፃ የማድረግና የማዘመን ሥራ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አቶ ስንታየሁ አስታውቀዋል::
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 5 ቢሊዮን 895 ሚሊዮን 819 ሺ 999 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 5 ቢሊዮን 43 ሚሊዮን 467 ሺ 461 ብር መሰብሰቡን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘይኔ ቢልካ ናቸው::
ሥራው ቅንጅታዊ አሰራን የሚጠይቅ በመሆኑ የፊት አመራሩ ተግባሩን በባለቤትነት ወስዶ መንቀሳቀስ መጀመሩ ለተሻለ አፈፃፀም አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል ::
ይሁንና ከክልሉ የወጪ ፍላጎት አንፃር በቀጣይ በልዩ መልኩ መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል::
የሰው ኃይል አለመሟላት፣ የሥነ ምግባር ችግሮች፣ የጥቅም ግጭትና አድሎአዊነት እንዲሁም በዜጎች ዘንድ ደረሰኝ የመጠየቅና የመቀበል ባህል አለመዳበር ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አቶ ዘይኔ አብራርተዋል::
በቀጣይ ለህግ ተገዥ ባልሆኑት ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ሥራ ይከናወናልም ብለዋል::
ከብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ የሚደገውን ጥረት ሁሉም እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል::
በውይይት መድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል፣ የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ እና የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘይኔ ቢልካን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል::
ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ