ጥበብ ለአንድነት
በአለምሸት ግርማ
ጥበብ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የጎላ አበርክቶ አለው። ዜጎችን እርስ በእርስ በማስተሳሰርም ከፍተኛ ሚና ያበረክታል። ባህልን፣ቋንቋን ማህበራዊ ግንኙነትን አዋዝቶ በማቅረብ ያስተምራል፣ ያበረታታል፤ ያወራርሳል። በተለይም ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ነው የሚባለው በተለምዶ አይደለም። ሙዚቃ ሁሉን የማግባባት እና የማቀራረብ ኃይል አለው።
በዛሬው ቅኝታችን የሀዲያ ዞን ኪነት ቡድንን የስራ እንቅስቃሴ ለመዳሰስ ወደናል፦
አባይነሽ አዲሱ ትባላለች። የባህል ኪነት ቡድኑ አባል ነች። ጥበብ ከልጅነቷ ጀምሮ በውስጧ እንደነበረ ትናገራለች። ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በባህላዊ ተወዛዋዥነት ትሰራ የነበረ ሲሆን በመቀጠልም በዚያው በቡድን ውስጥ በድምፃዊነት የማገልገል ዕድሉን አግኝታለች። ባገኘችው ዕድልም በመጠቀም ባለብዙ ተሰጥኦ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ከስራዋ የሚያስደስታትን ስትናገር፦
“የኢትዮጵያን ባህል የማስተዋወቅ ዕድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። ስራዬ ደስታን ይፈጥርልኛል። ሙዚቃ፣ በተለይም ደግሞ የባህል ዘፈን እወዳለሁ። የኪነት ቡድኑ በውስጤ ያለውን ተሰጥኦ ማውጣት እንድችል ረድቶኛል፥ ልምድም ቀስሜበታለሁ” ትላለች።
አንድ ሰው የራሱን ተሰጥኦ ማወቁ ለስኬታማነት የመጀመሪያው መንገድ ነው የምትለው ወጣቷ እንደባህል ኪነት ቡድን በቀጣይም ከቀድሞው በተሻለ መልኩ እንደሚሰሩና በራሷም የግሏን ስራ ለህዝብ የማድረስ አላማ እንዳላት አጫውታናለች።
ሌላኛዋ የቡድኑ አባል ሰብለወርቅ እሸቱ ስትሆን በቡድኑ ውስጥ የኬሮግራፈር ባለሙያ ናት። በቡድኑ ውስጥ ስላላት ቆይታ ስትናገር፦
“ከልጅነቴ ጀምሮ በቡድኑ ውስጥ ነው ያደኩት፤ ልጅነቴን እንዳልረሳው አድርጎኛል። ስልጠናም ያገኘሁት የቡድኑ አባል ሆኜ ተሳትፎ ማድረግ ከጀመርኩ በኋላ ነው። ጊዜዬን ለቁም ነገር እንዳውልም ዕድል ፈጥሮልኛል። በተለይም ደግሞ የሀገሬን ባህል እንዳውቅ አድርጎኛል። ጥበብ ፍቅርን ያስተምራል፣ ይሰብካል፣ በመሆኑም በስራዬ ደስተኛ ነኝ” በማለት ለጥበብ ያላትን ፍቅር ትገልፃለች።
ጥበብ የእርስ በእርስ ግንኙነትን እንደሚያጠናክር ባለሙዎቹ ይናገራሉ። አባላቱም እንደየተሰጥኦቸው የተሻለ ነገር ለመስራት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በተለይም ደግሞ ከባህሉ ላለማፈንገጥ ቦታው ላይ ተገኝተው ትክክለኛውን ባህል በማጥናት ሙያቸውን ያዳብራሉ። ራሳቸውን ብቁ ለማድረግ በሳምንት ሶስት ጊዜ በመገኛኘት ልምምድ ያደርጋሉ። ከዚህ በተጨማሪ በተሰማሩበት ሙያ ስኬታማ ለመሆን በርትቶ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የባህል ቡድኑ አስተባባሪ ወጣት አስፋው ዳንኤል ስለቡድኑ አመሰራረት ሲናገር፦
“የኪነት ቡድኑ በ1997 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ነው የተመሰረተው። ቡድኑ ባህልን ከማስተዋወቅ አኳያ የተለያዩ ስራዎች እየሰራ ይገኛል። ለዚህም በዓላትን፣ ሁነቶችንና የመሳሰሉትን መድረኮች እንጠቀማለን። ከተመሰረተ 19 ዓመታትን ያስቆጠረው የሀዲያ ዞን ኪነት ቡድን በአሁኑ ወቅት 24 አባላት ያሉት ሲሆን ከነዚህም 18ቱ ወንዶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ 6ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው።
“የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህል የምንሰራ ሲሆን አሁንም የበለጠ ተጠናክረን እየሰራን እንገኛለን። ለዚህም ባለሙያዎቹ በትጋት እና በተነሳሽነት እየሰሩ ነው።”
ሙያው በፍቅር የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ስራቸውን ወደው እየሰሩ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው የቡድኑ አባላት ያስረዳሉ። በቡድን የሚሰሩ ስራዎች ባህልን በአብሮነት ማስተዋወቅና አንድነትን ማጠናከር የመሳሰሉ አበርክቶዎች አላቸው።
በቡድን የሚሰራ የጥበብ ስራ በህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርም ይረዳል በማለት ባለሙያዎቹ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።
አባላቱ እንደነገሩን ከቡድን አባላቱ መካከል ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ለህዝብ አበርክተዋል። እነሱም ፈለጋቸውን የመከተል ፍላጎት አላቸው።
ብዙውን ጊዜ የሚሰለጥኑት እርስ በርሳቸው ልምድ እየተለዋወጡ በመማማር መሆኑንና የመሰልጠኛ ቦታ ችግር እንዳለባቸው የተናገሩ ሲሆን፤ አያይዘውም “ከዚህ የተሻለ ለመስራት ይቻል ዘንድ ሙያ ባላቸው አሰልጣኞች መሰልጠን እንድንችል ዕድሉ ቢመቻችልን፤ እንዲሁም የመሰልጠኛ ቦታ ችግር ቢቀረፍልን” ሲሉ አስያየታቸውን አቅርበዋል።
በቡድን የሚከናወን የባህል ትዕይንት በግል ከሚሰራው ይልቅ የራሱ የሆነ ውበት እና ድምቀት አለው። አቀራረቡ ማራኪ በመሆኑም ሰውን ከማዝናናት ባለፈም የአንዱን ባህል ለሌላው ማስተዋወቂያ መንገድ በመሆንም ያገለግላል።
ከዚህም ባሻገር የባህል ኪነት ቡድን ለባህል ብሎም ለኪነ-ጥበብ ዕድገት ትልቅ አበርክቶ አለው። ለዚህ ደግሞ ቀድሞ በሀገራችን የነበሩ ብዙዎችን ያፈሩ የባህል ኪነት ቡድኖች ምስክር ናቸው። ከዚሁ ጋር በተገናኘ ለብዙ፥ በስራቸው አንቱታን ላተረፉ የጥበብ ባለሙያዎች መፍለቅ ምክንያት በመሆናቸውም ለእነዚህ የሀገር ባለውለታ ለሆኑ የጥበብ መፍለቂያዎች ድጋፍ ሊደረግና ተገቢው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ማለት እንወዳለን!
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው