በገነት ደጉ
የዛሬው የንጋት እንግዳችን አቶ ታሪኩ ሮቤ ይባላሉ፡፡ በጌዴኦ ዞን ገደብ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ናቸው፡፡ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ለ9 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከእሳቸው ጋር በገደብ ከተማ አስተዳደር ያሉ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡- በንጋት ጋዜጣ እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ታሪኩ፡- እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- ትውልድ እና እድገትዎን ቢያስተዋውቁን?
አቶ ታሪኩ፡- የተወለድኩት በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ ልዩ ስሙ ባንቆ ጨልጨሌ በምትባልበት ቀበሌ ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ወርቃ በሚባልበት ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተምሬያለሁ፡፡
ከ9ኛ እስከ 10ኛ ገደብ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው በግብረሰናይ ድርጅት ትምህርት ቤት ነበር የተከታተልኩት፡፡
የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን ደግሞ ከ2001 ዓ.ም እስከ 2002 ዓ.ም በይርጋጨፌ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ። በ2003 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመግቢያ ፈተና ውጤት በማምጣት በ2004 ዓ.ም አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ ማናጅመንት ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ድግሪዬን ተከታትዬ በ2006 ዓ.ም ተመረኩኝ፡፡
በ2007 ዓ.ም በገደብ ወረዳ የገቢዎች ጽህፈት ቤት የገቢ አሰባሰብ ባለሙያ በመሆን ተቀጥሬ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ከሰራሁ በኋላ በ2011 ዓ.ም አካባቢ በገደብ ወረዳ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት የግዥ ፋይናንስ እና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን በሹመት ሳገለግል ቆይቻለሁ፡፡
ከ2016 ዓ.ም ወርሃ መስከረም ጀምሮ የገደብ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡
የሁለተኛ ድግሪዬን በኢንፎሊንክ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድምንስትሬሽን በ2015 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ተመርቄያለሁ፡፡
ንጋት፡- ተወልደው ባደጉበት አካባቢ በኃላፊነት ቦታዎች መስራትዎን እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ታሪኩ፡- በተማርኩት የትምህርት ሙያ ለመንግስት እና ለህዝብ ገቢ ለማሰባሰብ ከከተማ ወጣ በማለት እስከ 27 ኪሎ ሜትር ድርስ ርቀት እንቀሳቀስ ነበር፡፡
ክረምት ሲሆን በጭቃ ተጉዘን ነበር ገቢ የምንሰበስበው፤ አካባቢውም ርቀት ስላለው እና ተሽከርካሪ ስለማይገኝ ፈታኝ ነበር፡፡
በዚህም በጣም ዋጋ ከፍያለሁ፡፡ ውርጩ፣ ፀሐይ፣ ርሀብ እና ጥማቱ እየተፈራረቀ ነበር ስሰራ የቆየሁት፡፡
ከባለሀብቶች ጋርም የመንግስት ግብርን ለማሰባሰብ እሰጥ አገባ ውስጥ ነበር ስገባ የቆየሁት፡፡ በዚህም ጥሩ አፈፃፀም ስለነበረኝ ከገቢ አሰባሰብ በማንሳት የገቢ አሰባሰብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አስተባባሪ ሆኜ ቦታ ተሰቶኝ ነበር፡፡
በዚህም ጠንካራ ውሳኔ በመስጠት ከበላይ ካሉ አመራሮች ጋር በመነጋገር በርካታ ሥራዎች በመስራት ነበር ወደ አመራርነት የመጣሁት፡፡ በምሰራቸው ስራዎች ወደ አመራርነት ስመጣ እጅግ ደስተኛ ነበርኩ። ተወልደው ባደጉበት አካባቢ የራስን ህዝብና ወላጅ በታማኝነት ማገልገል በጣም ያስደስታል፡፡ በዚህም ከሚባለው በላይ ደስተኛ ነበርኩ፡፡
የምሰራው ስራ ለህዝብና ለመንግስት አይመስለኝም ነበር፡፡ ለግል እስኪመስለኝ ድረስ ነበር ተነሳሽነቱና ታማኝነቱ፡፡ ችግሮች እና ተግዳሮቶቹ እንደነበሩ ሆነው ማለቴ ነው።
በፋይናንስ ሴክተር መስራት እጅግ ፈታኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ የመልካም አስተዳደር ችግር ያሉበት እና የህዝብ ጩኸቶች የሚደመጡበት በመሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ውጣ ውረድ አለው፡፡
ይሁን እንጂ ለህዝቡ ጩኸት ምላሽ በመስጠት ጠንካራ ሥራዎችን ነበር ስሰራ የቆየሁት፡፡
ትልቁ ስራ ነው ብዬ የማምነው እንደ ከተማዋ የቤት ኪራይ ችግሮች በስፋት የነበሩ ሲሆን ይህንንም ለመቅረፍ ከአመራሮች ጋር በመሆን በርካታ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ የተጀመሩ ስራዎች ወደ 70 በመቶ ተጠናቀው ነበር ከዚያው የወጣሁት፡፡
ንጋት፡- አካባቢው በካሽ ክሮፕ (በቋሚ ሰብሎች) የታወቀ በመሆኑ የንግድ ሰርዓቱ ምን ይመስላል?
አቶ ታሪኩ፡- በጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ አምራች አካባቢ እንደሆነች ነው የምትታወቀው፡፡ ነዋሪዎቿ፣ የመንግስት ሰራተኞች እና የአካባቢው ህብረተሰብ ከማሳው ነው የሚመገቡት፡፡
ጥቂት የፋብሪካ ውጤት ነው ገዝተው የሚጠቀሙት ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
በዚህም የተነሳ ለረጅም ጊዜ ከመንግስት ገቢ ሳይፈልግ የቆየ ወረዳ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ህዝብ እየጨመረ ሲመጣ እርሻውም ሆነ የሚበላው በነበረበት አልቀጠለም፡፡ ዛሬም ገደብ ላይ የሚመረተው ቆጮ ወደ አዲስ አበባ፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ፣ ጩኮ፣ አርባ ምንጭ እና ዲላ ይጫናል፡፡
ጎመን፣ የቅጠል ሽንኩርት እና ጥራጥሬን ጨምሮ በሳምንት ሁለት ጊዜ በሚኖረው ትልቅ ገበያ በቀን እስከ አስር እና ከዚያ በላይ መኪናዎች ጭነው ይወጣሉ፡፡ ሌላው ስጋ አሁን ላይ በጥራትም ይሁን በዋጋ ከሌላ አካባቢ የተሻለ ነው፡፡ በቀንድ ከብት ትታወቃለች። አንድ ኪሎ ስጋ 4 መቶ ብር ነው፡፡ በተጨማሪም በወተት፣ ዶሮ እና እንቁላል ምርቶች ትታወቃለች፡፡
ይህም ኢንተርፕራይዝ ላይ ተደራጅተው ሳይሆን እራሱ አርሶ አደሩ በራሱ ማሳ ዘርቶ እና አምርቶ በማምጣት በስፋት ለገበያ ሚያቀርብበት ዕድሎች ሰፊ ናቸው። ህብረተሰቡ እንሰትን እራሳቸው ፍቀው ነው ከምግብነት ባሻገር ለገበያ በስፋት የሚያቀርቡት፡፡
አርሶ አደሮቻችን ከገበያ ቆጮ ገዝተው አይበሉም፡፡ ልብስ እና ሌሎች ነገሮችን ለመግዛት ነው ቆጮ አውጥተው የሚሸጡት። እነዚህ ግብይቶች የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ ዛሬም ቢሆን በዚህ ኑሮ ውድነት እንኳን ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ በልቶ የማደሩ ነገር አለ፡፡ ከጥራትም አንፃር ያልተበረዘ እና ያልተከለሰ ምግብ ነው የሚገኘው፡፡
በተለይም በ2010 ዓ.ም ከኦሮሚያ ጉጂ ጋር በተፈጠረው ጦርነት ወዲህ ሰፋ ያለ ምርት የሚወጣ ባይሆንም ተያይዞ የመጣው እሴት ግን ጥሩ የሚባል ነው፡፡
ንጋት፡- የወረዳዋን የእድገት እና የለውጥ ጉዞ እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ታሪኩ፡- የገደብ ከተማ ቀደም ሲል በኮቸሬ ወይም (ጨለለቅቱ) በሚባለው ወረዳ ውስጥ ነበር የምትተዳደረው፡፡ በ1996 ዓ.ም በማዘጋጃ ቤት ስትተዳደር ነበረች፡፡ በዚህም አንድ ቀበሌ እና አንድ ማዘጋጃ ቤት ነበር አገልግሎት እየሰጠ የነበረው፡፡
ከዚያም ቀስ በቀስ በምታሳየው እድገት እና የህዝብም ፍላጎት ስለነበረ ሳይቆይ በ1998 ዓ.ም የገደብ ወረዳ ተመሰረተች፡፡ ስለዚህ ገደብ ወረዳ ሲመሰረት እዛው ገደብ ከተማ መቀመጫዋን አድርጋ ነው የቀጠለችው፡፡
አሁንም ከተማዋ የህዝብ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ስለነበረ በ2011 ዓ.ም በቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ምክር ቤት በከተማ አስተዳደርነት ውሳኔ አግኝታ እራሷን ችላ በከተማ አስተዳደርነት ተሰይማለች፡፡
በ2012 ዓ.ም ወርሀ ሐምሌ ላይ የከተማ አስተዳደርነቱን ሙሉ እውቅና አግኝታ ሙሉ መዋቅር ተሟልቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ የመሰረተ ልማት አውታሮች መብራትና ውሃን ጨምሮ የገባበት እና የኢትዮ ቴሌ ኮም አገልግሎትም ማግኘት የቻለችበት ነበር፡፡ የመሰናዶ ትምህርት ቤት እና በውስጧ ይዛ የነበረችው ጤና ጣቢያ ወደ ገደብ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚያስፈልገው ቁሳቁስ ተሟልቶለት አድጓል።
የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ እና የጎርፍ መሄጃ ቦዮች እንዲሁም ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፎች መንገዶች ተሰርተው አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡
የነዳጅ ማደያዎች ከዚህ በፊት አልነበሩም። የመንግስት ተሽከርካሪዎች ይርጋ ጨፌ እና ሀገረማሪያም ሄደው ነበር ነዳጅ የሚቀዱት፡፡ አሁን ላይ በከተማዋ አራት ማደያዎች ተገንብተዋል፡፡
ሌላው የባንክ አገልግሎት ሲሆን ከዚህ በፊት ከተማዋ ወረዳ በነበረችበት ወቅት አንድ የንግድ ባንክ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ አምስት የግል ባንኮችን ጨምሮ ስድስት ባንኮች በከተማዋ አገልግሎት እየሰጡ ናቸው።
ይህም ለእኛ ትልቅ ለውጥ እና እድገት ነው፡፡ የእድገት ጎዳናዋ ይህን ይመስላል፡፡
ንጋት፡- የገደብ ከተማ አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ታሪኩ፡- ከተማዋ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጨረሻው እና ከኦሮሚያ ጋር የሚያዋሰንና ከጌዴኦ ዞንም በስተ ደቡብ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡
ከከተማዋ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት የኦሮሚያ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡ በ2010 ዓ.ም የጌዴኦ ጉጂ ግጭት ከፍተኛ የህዝብ ፍሰት ያመጣበት ነው፡፡ በህዝቦችም መካከል ትልቅ ቁርሾ የፈጠረበት ነው፡፡
በወቅቱ መንግስት በያዘው አቋም ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡ የጌዴኦ ማህበረሰብ በጌዴኦ ውስጥ ካለው ሊበልጥ በሚችል ደረጃ ጉጂ ዞን ውስጥ ይገኛል፡፡
የጉጂ ዞን ደግሞ አቃፊ ነው፡፡ ባህል እና ታሪካችንም አንድ ነው፡፡ ደግሞም ጌዴኦና ጉጂ የአንድ አባት ልጆች እንዲሁም የመጀመሪያ እና የመጨረሻ በመባል የሚታወቁ እና በጋብቻም መለየት በሚከብድ ደረጃ አንድ ናቸው፡፡ በዚህም ማህበራዊ መስተጋብራችን እጅግ የተጋመደ እና ማንም ሊለየው የማይችል ነው።
ዛሬ ድረስ የጉጂ ማህበረሰብ በገደብ አለ፡፡ የጌዴኦም በተመሳሳይ ጉጂ ላይ አሉ፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች የተጠቀሙት እና በወቅቱ በሰሩት ደባ እና ሸፍጥ ብዙ ሰዎች ተሰውተዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ያም በዚያ ታልፏል፡፡
ያ ደግሞ ዝንት ዓለም እንደ ትርክት አድርገን የምንወስደው ሳይሆን አንድ ወደሚያደርገን እና ወደ ህብረብሔራዊነት ወደሚያመራን ሀሳቦች ላይ ተደምረን ሰላም ማምጣት አለብን፡፡ ወደ ቤታቸውም የተመለሱ ሰዎች አርሰው ሰላማዊ ኑሮአቸውን እየኖሩ ነው፡፡
በርግጥ በጉጂ አካባቢ አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች አሁንም ድረስ እዚያው አካባቢ መንግስት በሚዛን ማየት ያለበት ነው የሚል እሳቤ አለኝ፡፡
እንደ እኛ ከተማም ይህንን የምንዘናጋው አይደለም፡፡ በተለይም በ2015 ዓ.ም ወርሀ ጥር ላይ ከተማችን ድረስ ገብተው የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡ ፈጣሪ ይመስገን መንግስትም ቶሎ በፍጥነት በመድረስ ታድጎታል፡፡
ያም ሆነ ይህ ዛሬም የገደብ ህዝብ የውጪውንም የውስጡንም ሰላም ለመጠበቅ ውጪ የሚያድር ህዝብ ነው፡፡
ንጋት፡- ከፀጥታው መዋቅር ጋር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዴት ይገለፃሉ?
አቶ ታሪኩ፡- በ2015 ዓ.ም ጥር ወር ላይ የተከሰተው ክስተት ብዙ አስተምሮናል፡፡ በዚህም በየጊዜው ከምስራቅ ጉጂ አመራሮች ጋር ሌት ተቀን በጋራ እንሰራለን፡፡
እነሱም ይሁን እኛ ጋር ያለውን የውስጥ ችግሮችን ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ካሉ ገላና ወረዳ፣ ከሀገረማሪያም ዙሪያ ወረዳ እና ከቀርጫ ወረዳ ጋር በመቀራረብ በየጊዜው በችግሮች ዙሪያ መረጃዎችን የምንቀባበላቸው አጋጣሚዎች በስፋት አሉን፡፡
ከዚህም የተነሳ በወሬ ደረጃ በአካባቢው ካምፕ አለ የሚል ነገር ቢነሳም እስካሁን ድረስ እነርሱ ካምፕ አድርገው የሚቀመጡበት ሳይሆን በየጊዜው ቦታን ቀይረው የሚንቀሳቀሱ አካላት በመሆኑ አንድ የተመረጠ ካምፕ የላቸውም፡፡
በተለይም ብዙውን ጊዜ ገብተው የመውጣት ነገሮች መኖራቸው ከህዝብ ዘንድ ጥቆማዎች ይመጣሉ፡፡ በዚያ ልክ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እየተከታተለ ያለበት ሂደቶች አሉ፡፡
አሁን ጥሩ ስሜት ውስጥ ያለንበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ የውስጥ አቅምን አስመልክቶ የመንግስት መከላከያ ሰራዊት፣ የክልል ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና የአካባቢ ነዋሪዎችን አስተባብረን ኮሚቴ ተዋቅሮ በቀንም ይሁን በማታ የአካባቢውን ደህንነት እየጠበቅን ነው።
ንጋት፡- በከተማዋ ያለውን የገቢ አሰባሰብ ስርዓት እንዴት ይገልፁታል ?
አቶ ታሪኩ፡- በርግጥ በቂ ገቢ ይሰበሰባል ብለን በድፍረት መናገር ባይቻልም ከተማዋ እራሷ በምትሰበስበው ገቢ ደመወዝ የምትከፍልበት አቅም ላይ ነው ያለችው፡፡ ከተመሰረተች ዛሬ ወደ አምስት ዓመት ነው። በዚህም አጭር ጊዜ ውስጥ ያላትን አቅም ተጠቅማ ሁሉም ነገር ተሟልቶላታል ብሎ ግን በድፍረት መናገር አይቻልም፡፡
በዚህም መነሻ ከተማ አስተዳደር ሆና ስትወጣ የውስጥ ገቢ 12 ሚሊየን ነበር። ዘንድሮ ደግሞ በአምስት ዓመት ልዩነት ወደ 76 ሚሊየን የውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡
ክልሉም አዲስ ስለሆነ የጥሬ ገንዘብ ችግሮች በመኖሩ ዘንድሮ የደረሰው የበጀት ጫናዎች በብዙ የመሰረተ ልማት ስራዎች ላይ ክልሉን እንዳንጠብቅ አድርጓል፡፡
በተለይም የውስጥ ገቢ አቅምን አሳድገን በ2015 ዓ.ም ሀያ ሚሊየን የነበረውን አቅም ዘንድሮ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሮ ወደ 76 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን እስካሁን ወደ 22 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡ ዓምና ከነበረው አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ገቢ አሰባሰብ ስራ ነው የተሰራው፡፡
አብዛኛው የቡና ነጋዴ የሚኖረው በወረዳው ሲሆን ግብርም ይሁን ዊዞሊዲንግ የሚከፍሉት በወረዳው ነው፡፡ ነገር ግን የቡና መፈልፈያ በወረዳ ያለ ቢሆንም ነጋዴው የሚያርፈው እዚህ ስለሆነ የትኛውንም ቋት ለይተን በመሰብሰብ የገቢ አቅማችንን ከዓምናው አንፃር የተሻለ እያደረግን ነው፡፡
የነጋዴውን የእለት ገቢውን በመለየት ደረጃቸውን በማሻሻል ከደረጃ ሐ ወደ ደረጃ ለ በማምጣት የተሻለ ስራ በስፋት ተሰርቷል። ወደ 20 የሚሆኑ ግብር ከፋዮች የደረጃ ማሻሻያ ተደርጎላቸዋል፡፡
በዚህም በውስጥ ገቢ ሰርተን ደመወዝ እንከፍላለን የሚለው ከባድ ቢሆንም በቀጣይ የተጀማመሩ ስራዎች አበረታች በመሆናቸው አጠናክረን የምንቀጥል ነው የሚሆነው፡፡
ንጋት፡- እንደ ሀገር ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች መኖራቸው ይታወቃል፤ የእናንተ ወረዳስ ምን ያህል ከዚሁ ችግር የፀዳ ነው?
አቶ ታሪኩ፡- ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ የፋይናንስ አመራር ሆኜ ወረዳ ላይ ስለቆየሁ ችግሩን አውቃለሁ፡፡ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የሚገናኝ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ የለም፡፡
ነገር ግን ወረዳችን ብዙ የፀዳ ነገር እንደሌለ አስባለሁ፤ ከዚህም መነሻ አስተያየት ብሰጥ መልካም ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም የተሰጠ የአፈር ማዳበሪያ እዳ ዛሬም ድረስ ይቆረጣል። ስለዚህ ወጥ የሆነ የኦዲቲንግ ስራ አለመኖሩ በራሱ ለምን እንደሚቆረጥ እና መቼ ተቆርጦ እንደሚያልቅ በማይታወቅ ሁኔታ ከትሬዥር ጭምር የሚቆረጥበት ሁኔታዎች አሉ፡፡
በገደብ ወረዳ በነበርኩበት ወቅት እስከ ክልል ድረስ ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ስለዚህ የተቆረጠ የማዳበሪያ እዳ እየተቀናነሰ መሄድ አለበት፡፡ የወለድ ምጣኔው ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
በዚህም ህዝቡ ውሃና መብራት ማግኘት ሲገባው መሰረተ ልማት ማግኘት እያለበት በዚህ ምክንያት እያጣ ያለበት ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ ይህም እንደ ክልል ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
እንደ ክልል ደመወዝ መክፈል የማይችሉ ወረዳዎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ስለዚህ የክልሉ መንግስት በተለይ ከዚህ ከማዳበሪያ ዕዳ ጋር ተያይዞ ከክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ጀምሮ ከፍተኛ የኦዲቲንግ ስራ ቢደረግ መልካም ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ጋርም ያሉ መረጃዎች በደንብ ሊፈተሹ ይገባል፡፡ በጎን ኦሞ ተቋሙ እየሰበሰበ በክልል ፋይናንስ የሚቆርጥበት ስርዓት ከህዝብ ጉሮሮ እየተቆረጠ ልማት የሚያሳጣበት እንደ ገደብ ወረዳም ከፍተኛ ችግር ውስጥ የተገባበት ነው። እንደ ከተማ አስተዳደር ግን ንክኪ የለንም፡፡
የውስጥ ገቢ በማነሱ ምክንያት ጡረታ መክፈል ባለመቻላችን ምክንያት የጡረታ ብር ይቆረጥብናል፡፡ ይንም የጡረታ ዋስትናዎች መጥተው የሚቆርጡበት እነዚህን የመሳሰሉ ፈተናዎች አሉ፡፡
በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሚጎዳው ህዝቡ ስለሆነ በተለይም ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ያለውን ከክልል ጀምሮ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ቢያየው መልካም ነው፡፡ በተለይ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ያሉ እዳዎች በደንብ ለማን ምን ተሰጥቶ ነበር? ከማን ምን ያክል ተቆረጠ? ምን ያክል ቀሪ እና ወለድ መጣል የለበትም የሚለው ጭምር ቢታይ መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከማዳበሪያው ዕዳ ጋር ተያይዞ እታችኛው መዋቅር ላይ ከደረሰው ጫና አንፃር በአጽኖት መናገር እወዳለሁ። በተለይም የመንግስት ሰራተኞች በልተው የማደራቸውን ጉዳይ ጥያቄ ላይ የጣለበት ነው ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡
ንጋት፡- በከተማዋ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በስፋት ይነሳል፤ ይህንንስ እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ታሪኩ፡- ከውሃ ጋር ተያይዞ መንግስት በሰጠን እድል ከ2013 የበጀት ዓመት ጀምሮ የውሃ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንድትሆን ከተመረጡ አምስት ከተማዎች መካከል አንዷ ናት፡፡
የ65 ሚሊየን ብር በጀት አግኝታ የውሃ ማስፋፊያ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን በሀገሪቱ ደረጃ ካለው የጥሬ ዕቃ መናር እና የግብዓት ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የተቸገሩበት ፕሮጀክቱ በነበረበት ሆኖ ዋጋ ሲጣራ ወደ 1መቶ 19 ሚሊየን የደረሰበት ሁኔታዎች አሉ፡፡
ይህም በፌዴራል፣ በክልል እና በከተማ አስተዳደሩ ጣምራ ፈንድ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ለ20ሺ የህብረተሰብ ክፍሎች ማድረስ ሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡
ማለቅ የነበረበት በ2015 ዓ.ም ነበር፡፡ አሁን ላይ ከ97 በመቶ በላይ ሄዷል፡፡ ነገር ግን ዋናው ኤሌክትሮመካኒካል ስራዎች ምንም ያልተገፋበት ሂደቶች አሉ፡፡ እንደ ገደብ ከተማ ከፍተኛ የህዝብ ጩኸት ያለበት ነው፡፡
እንደ መፍትሄ ከአስተዳዳሪው ጋር ተነጋግረን የውሃ ቢሮ መቀመጫው ዲላ በመሆኑ ተነጋገረናል፤ እነርሱም ምልከታ እናደርጋለን ያሉበት አጋጣሚዎች አሉ። ይህንንም የህዝብ ጩኸት ለማስታገስ ፕሮግራሞች ተይዘዋል፡፡
በዚህም ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ ገምግመው ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ነው ምላሽ የሰጡት፡፡ መቼ አልቆ አገልግሎት ይሰጣል የሚለውን ቁርጥ ያለ ቀን መናገር ግን ይከብዳል፡፡
ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት መካልዎት?
አቶ ታሪኩ፡- ሀገር ማለት ህዝብ ነውና ለአንድ አካባቢ ዕድገት መንግስት ብቻውን የሚሰራው ስራ የትም ሊያደርሰው እንደማይችል ተረድተን ህዝብ ከመንግስት ጋር በቁርጠኝነት ቢሰራ የሚታይ ዕድገት ማምጣት ይቻላል፡፡ በተለይም ካሽ ክሮፕ አካባቢ በመሆኑ ባለሀብቶች ለከተማዋ ዕድገት የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ እንዳለባቸው መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ታሪኩ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው