በአንዱዓለም ሰለሞን
ከወጣት ተመስገን ቲልቻሞ ጋር የተገናኘነው በቅርቡ ወደ ባስኬቶ ዞን፣ ላስካ ከተማ ለሥራ ጉዳይ በሄድኩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ገና በለጋ ዕድሜው በፖሊዮ ምክንያት በአንድ እግሩ ላይ የአካል ጉዳት ቢያጋጥመውም እሱ ግን እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ ኑሮን ለማሸነፍ ከሚደረግ ጥረት ባሻገር በብዙ የህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ ከራሱ አልፎ ለሀገር የሚጠቅም ሥራ እስከመስራት ደርሷል፡፡ ይህ የሆነው ግን እንዲሁ በዋዛ፣ እንዳልነበር ወጣቱ ስለሁኔታው እንዲህ ያስታውሳል፡-
“አካል ጉዳተኝነቴ ባሳደረብኝ ተጽዕኖ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ እቤት ውስጥ ተቀምጬ ነበር፡፡ እስከ 9 ዓመቴ ትምህርት ቤት ባለመግባቴም ብዙ ጊዜ እቤት ውስጥ አሳልፍ ነበር፡፡ ይህም ስለገጠመኝ ሁኔታ በጥልቀት እንዳስብና መሆን ስላለበት ነገር ራሴን እንድጠይቅ አስችሎኛል፡፡ ሥራ ሰርቼ ራሴን ማኖርም ሆነ መማር እንዳለብኝ የወሰንኩትም የዚያን ጊዜ ነበር፡፡ ይህን ሳስብ ከቤተሰቦቼ ባሻገር ድጋፍ የሚያደርግልኝ ሰው አላጣም የሚል እምነትም ነበረኝ፡፡”
ምንም እንኳ ወጣቱ ከራሱ ጋር በእንዲህ መልኩ ቢመክርም በምን ዓይነት የሥራ ዘርፍ ለመሰማራት እንደሚችል ግን አላወቀም ነበር። እርግጥ ነው፤ እንደ አንድ ታዳጊ ሲታይ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስራ ለመስራትና ለመማር መወሰኑ በራሱ ትልቅ አድናቆት የሚያስቸረው ነው፡፡
ጠንካራ በራስ መተማመን ያለው ወጣት ተመስገን በእርግጥም እንዳሰበው ትምህርት ቤት ገባ፡፡ በወቅቱ ከልጆች ጋር የትምህርት ገበታ ላይ ለመገኘት መቻሉ በራሱ ትልቅ ነገር ነበር። በየጊዜው የሚያጋጥሙትን ችግሮች ተቋቁሞ ትምህርቱን መቀጠሉ ደግሞ ትዕግስቱን የፈተነና ጽናቱን የጠየቀ ሌላ የህይወት ምዕራፍ ነበር። በትምህርት ቤት ቆይታው ወቅት ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል አንዱ የሆነውን እንዲህ በማለት ያስታውሳል፡-
“በክራንች ድጋፍ መንቀሳቀስ ከመጀመሬ አስቀድሞ እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ በእንብርክክ ነበር የምሄደው፡፡ በዚህ ጊዜ ታዲያ የእኔ ትልቁ ፈተና ደብተርና መጽሀፍቶቼን በእጄ ይዤ በዚያ መልኩ መጓዝ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ብዙ ተማሪዎች ያግዙኝ ስለነበር ብዙም አልተቸገርኩም። በተፈጥሮዬ ተጫዋችና ከሰው ጋር ተግባቢ ስለሆንኩ ብዙዎች ይወዱኝ ነበር፡፡ ጥረቴን በማየትም ብዙዎቹ እኔን ለመርዳት ፈቃደኞች ነበሩ፡፡”
እነዚህንና መሰል ፈታኝ አጋጣሚዎችን ተቋቁሞ ትምህርቱን እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ የተማረው ወጣቱ ሥራ ለመስራትና ራሱን ለማኖር ሲል ትምህርቱን ለማቋረጥ መገደዱን ይናገራል። በአሁኑ ሰዓት የሞባይል ጥገና ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የተወሰኑ የፈጠራ ስራዎችንም ሰርቷል፡፡ ጥገናውንም ሆነ የፈጠራ ሥራውን እንዴት ሊጀምር እንደቻለ ሲናገር ተሰጥኦውን ተከትሎ በልምድ እንዳዳበረው ይገልጻል፡-
“ነገሩን ትምህርት ቤት ከመግባቴ አስቀድሞ ነበር ያሰብኩት፡፡ የወደፊት ተስፋዬ ምንድነው? የሰው እጅ ሳልጠብቅ ምን ሰርቼ ነው ራሴን የማኖረው? በማለት ራሴን ስጠይቅ የመጣልኝ ሀሳብ ውስጤ ያለውን ተሰጥኦ አውጥቼ መጠቀም እንዳለብኝ ነበር፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የፈጠራ ሥራዎችን መሞካከር ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ከወዳደቁ ቁሳቁሶች አንዳንድ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት እሞክር ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ሳለሁ ከትምህርቴ ጎን ለጎን ይህን ለማድረግ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ በእርግጥ ጥረቴ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በቀጣይ ደግሞ ከዚህ በተሻለ ለሀገር የሚጠቅም ሥራ ለመስራት ሀሳብ አለኝ፤ እንደሚሳካልኝም ባለሙሉ ተስፋ ነኝ።”
የመጀመሪያ የፈጠራ ሥራውን (የእጅ ባትሪ) በሰራበት ወቅት ድጋፍ ያደርግለት የነበረው አንድ መምህር ወደ አርባ ምንጭ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በመሄድ ልምድ እንዲቀስም ሁኔታዎችን አመቻቸለት፡፡ በወቅቱም ኮሌጁ 3ሺህ ብርና አንድ ስፒከር ሸለመው፡፡ በዚህ ሽልማት በመበረታታትም ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችን ይሰራ ጀመር፡፡
ከወዳደቁ ዕቃዎች የእጅ ባትሪ በመሥራት የፈጠራ ሥራውን አሀዱ ያለው ወጣቱ ተሰጥኦውን በልምድና በንባብ እያዳበረ በመቀጠል የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን መስራት ችሏል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የስጋ መጥበሻ፣ የጁስ መጭመቂያ፣ በፀሐይ ሃይል የሚሰራ ጀነሬተር፣ የጫጩት መፈልፈያ እንዲሁም አሁን ሥራው በሂደት ላይ ያለው በዓይነቱ የተለየ የዘር መዝሪያ ማሽን ይጠቀሳሉ፡፡
የሰራሀቸው ቴክኖሎጂዎች ምን ያህል ውጤታማ ናቸው? ስል መጠየቄ አልቀረም። እርሱም ለጥያቄዬ እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጥቶኛል፡-
“ሥራዎቼ ውጤታማ ነበሩ ለማለት ይቻላል። ለአብነት በ2015 ዓ.ም መግቢያ ላይ የሰራሁትን የጫጩት መፈልፈያ እኔ ራሴ ሞክሬ ውጤታማ መሆኑን አረጋግጫለሁ። በ12 እንቁላሎች ሞክሬ 6 ጫጩቶች ተፈልፍለዋል፡፡ በወቅቱ ከክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም ባለሙያዎች እዚህ ድረስ በመምጣትና ሥራዬን በአካል በማየት አበረታተውኝ ነበር፤ ምንም እንኳ ከዚያ በኋላ ያደረጉልኝ ድጋፍ ባይኖርም፡፡
በአሁኑ ሰዓት የምሰራው የዘር መዝሪያ ማሽንም በክልል ደረጃ ለሚደረግ የፈጠራ ሥራ ውድድር ዞኑን ወክዬ የምቀርብበት ነው፡፡ ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ እገኛለሁ። የፈጠራ ሥራዬ ነዳጅ የማይፈልግና በአህያ ጉልበት የሚሰራ ሆኖ በአንድ ጊዜ በአስር የእርሻ መስመሮች ዘር መዝራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡”
ከዚህ ባሻገር የስጋ መጥበሻውን አሰራር (አጠቃቀም) ያለ ስጋ ቢሆንም አሳይቶኛል። እርሱ ከነገረኝም ሆነ ካየሁት ሁኔታ እንደታዘብኩትም ድጋፍ የሚያደርግለት ግለሰብ አልያም ተቋም ቢኖር ከዚህ በተሻለ ሊሰራ እንደሚችል ነው። እርሱም ቢሆን ያረጋገጠልኝ ይህንኑ እውነታ ነው፤ “አቅም ባያንሰኝ ደግሞ ብዙ ነገሮችን ለመስራት አስብ ነበር” በማለት፡፡
ይህን ይበል እንጂ ወደ ፊት ለሀገር ታላቅ ጥቅም የሚሰጥ አንድ የቴክኖሎጂ ውጤት የማበርከት ሀሳብ ግን አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ አካል ጉዳተኛ መሆኑ የሚያሳድርበት ተጽዕኖ እንደማይኖር በሙሉ ልብ ይናገራል፡-
“አካል ጉዳተኝነት አለማቻል አይደለም። እንዲያውም በርካታ አካል ጉዳተኞች ጥበብ በእጃቸው ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ወደ ውስጣቸው የማየታቸው ነገር ከፍተኛ ነው፡፡ ሙሉ አካል ኖሮት የሚሰርቅ አለ፤ የሚለምንም እንዲሁ፡፡ ዋናው ነገር የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው። መጀመሪያ ራሱን ያሰነፈ ሰው እንዴት ሊበረታ ይችላል? ስርቆትንና ልመናን እያሰበም በሥራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ በበኩሌ አካል ጉዳተኝነቴን ሰበብ አድርጌ ራሴን ዝቅ አላደርግም። ቤተሰቤንና ሀገሬንም አላሰድብም። የማስበው ሥራ ሰርቼ ራሴን ስለማኖር ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ምንም የሚገርም ነገር አይደለም። ይልቁንም በቅርብ ቀን ለሀገሬ አንድ ታላቅ ሥራ እንደምሰራ ተስፋ አለኝ”
በእርግጥም የወጣት ተመስገን ሀሳብ ጥልቅ፣ ምኞቱም ሩቅ ነው፡፡ ግን ደግሞ ምኞት ብቻም አይደለም፤ በውጣ ውረድ የተፈተነ ማንነት የወለደው፣ ነገ እውን ሊሆን የሚችል ታላቅ ህልም ነው እንጂ፡፡ ያሰበው እንደሚሳካም ያለ አንዳች ጥርጥር ሆኖ ነበር የሚናገረው፡፡ እንዲህ እንዲሆን ያደረገውም በችግሮች ተፈትኖ ካለፈው ህይወቱ ካገኘው ልምድ በመነሳትና እስከ አሁን በጥረቱ ካሳካው ስኬት አንጻር ነው፡፡
እኔም ያሰበው ተሳክቶ ይመለከት ዘንድ በጎ ፈቃደኛ የሆኑም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት የተቻላቸውን ድጋፍ ቢያደርጉለት መልካም ነው በማለት ለወጣቱ ቸር ተመኝቼ ጽሁፌን በዚሁ ቋጨሁ፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው