የአርሶ አደሮቻችን ኑሮ ለማሻሻል በግብርና ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

የአርሶ አደሮቻችን ኑሮ ለማሻሻል በግብርና ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 02/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርሶ አደሮቻችን ኑሮ ለማሻሻል በግብርና ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር አስታውቋል።

በወረዳው ያረጁ ቡናዎችን የመንቀልና በአዳዲስ የመተካት ሥራ በሰፊው እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።

ቡና ከሚለማባቸው ከዞኑ ወረዳዎች አንዱ የሆነው የዲላ ዙሪያ ወረዳ ያረጁ ቡናዎችን በአዳዲስ ቡና በመተካት በተሠራው ሥራ አበረታች ውጤት ተገኝቷል ተብሏል።

የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ ረጋሣ እንደገለፁት፤ በወረዳው ከ12ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ እንደሆነና ከዚህም ውስጥ ከ7መቶ 31 ሄክታር በላይ መሬት ያረጀ ቡና መሆኑን ጠቁመዋል።

ያረጁ ቡናዎች በቂ ምርት ስለማይሰጡ በአዳዲስ መተካት በቂ ምርት ለማግኘት የጎላ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ኃላፊው ከዚህ በፊት ከ1 ሄክታር መሬት 4 ኩንታል ብቻ ይገኝ እንደነበር አንስተው በትኩረት በተሠራው ሥራ ከ1 ሄክታር ማሣ እስከ 18 ኩንታል ቡና መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ታደሰ በበኩላቸው የአርሶ አደሮቻችን ኑሮ ለማሻሻል በግብርና ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና በዚህም ግብርናውን ማዘመን ቀዳሚ ጉዳይ ይሆናል ነው ያሉት።

ወጣት ሀብታሙ አማረ በወረዳው የጤና ባለሙያና ሞዴል አርሶ አደር ሲሆን ያረጁ ቡናዎችን ከማሳው በመንቀሉ ከማህበረሰቡ ዘንድ ብዙ ተቃውሞ ገጥሞኛል ያለው ወጣቱ በውጤት ደረጃ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ እንደሚያመዝን በመጠቆም ሌሎችም ተሞክሮውን እንዲጋሩት መክሯል።

ዘጋቢ፡ አብነት አበበ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን