ጤናን እየጠበቁ ማህበራዊ ተሳትፎ ማድረግ
በአስፋው አማረ
ሀዋሳ ከተማ በቅርብ ጊዜ ከባድና አስደንጋጭ ሀዘን አስተናግዳ አልፋለች። ይህም የብዙ ተሰጥኦ ባለሙያ የሆነው አለማየሁ ሽፈራው ህልፈት ነው፡፡
በተለይም ደግሞ ከተግባቢነቱና ከተጫዋችነቱ ባለፈ በበጎ አድራጎት ሥራ ተሳትፎ ያበረከተው ተግባር ሁሌም ከመቃብር በላይ የሚታወስ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ተግባሩ በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነትን ማትረፍ ችሏል፡፡
ታዲያ ከህፈቱ በኋላ የአለማየሁን (አሊ) ቤተሰብ ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ የጤና እግር ኳስ ስፖርት ፌዴሬሽንም በበኩሉ የአለማየሁ ሽፈራሁ ቤተሰብን ለመደገፍ “አሊ ካፕ” በሚል ስያሜ ውድድር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ውድድሩን አስመልክቶ የዩኒክ ስታር ኮሌጅ (መሀል ጤና) እግር ኳስ ቡድን ተጫዋችና አሰልጣኝ ማርቆስ ታንቱ የውድድሩን ዓላማ ሲያስረዳ፦
“የዚህ ውድድር ዋናው ዓላማ በቅርቡ በድንገት በሞት ላጣነው አለማየሁ (አሊ) ቤተሰብ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡ አሊ በህይወት እያለ ለጤና እግር ኳስ ቡድኖች በርካታ ድጋፎችን አድርጓል፡፡
“ምንም እንኳን ወንድማችንን ከዚህ ዓለም በድንገት ብናጣውም ቤተሰቦቹን በመደገፍ አሻራችንን ማኖር ይገባናል፡፡ ከዚህ ሀሳብ በመነሳት የስፖርት ቤተሰቡ በጋራ በመሆን ውድድር እያካሄድን እንገኛለን” ሲል ተናግሯል፡፡
አለማየሁ በሕይወት በነበረበት ወቅት አረጋዊያንን እና እናቶችን በመደገፍ እንዲሁም በተለያዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ይሳተፍ እንደነበርም አጫውቶናል፡፡ ውድድሩ የእሱን በጎ ተግባር ለማስቀጠልና ለመከተል ታስቦ የተሰናዳ ስለመሆኑ ነው አሰልጣኝ ማርቆስ የሚገልጸው፡፡
አሰልጣኝና ተጫዋች የሆነው ማርቆስ “በዝክረ አሊ” ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ውስጥ መስራቱን አውግቶናል፡፡ በውድድሩ ላይ እየተሳተፈ መሆኑንም አጫውቶናል። ይህም ደግሞ በጤና ቡድኖችም ዘንድ ድጋፍ መደረግ እንዳለበት ከበርካታ ክለቦች በተነሳው ጥያቄ መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጾልናል፡፡
በአንድ የጤና ስፖርት ቡድን ውስጥ ከአርባ በላይ አባላት መኖራቸውን ይናገራል፡፡ እነዚህን በማስተባበር ቤተሰቡን የመደገፍ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻል።
“እሱ በህይወት እያለ በሀዋሳ ከተማ በስፋት ይታወቅ የነበረው አሰልጣኝ ህዝቅኤል ህልፈት ጋር ተያይዞ ጤና ቡድኖች በፈቃደኝነት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ድጋፍ ያደረጉበት ሁኔታ ነበር፡፡ ጤና ቡድኖች የተቋቋሙበት ሌላኛው ዓላማ ደግሞ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ለመረዳዳትና ለመደጋገፍ ነው” ብሎናል፡፡
በውድደሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ክለቦች በአጠቃላይ 28 መሆናቸውን ይናገራል። እነዚህ ክለቦች እያንዳንዳቸው 6 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡ አንድ ክለብ በፍቃደኝነት 10 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ 1 መቶ 72 ሺህ ብር በተዘጋጀው ዝግ አካውንት ማስገባት መቻሉን ገልጾልናል፡፡
በተለይም ቡድኖች በስፋት በማህበራዊ ጉዳዮቻቸው በሀዘንም ሆነ በደስታ መረዳዳትና መደጋገፍ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ ካደጉበት ማህበረሰብ የተማሩት መሆኑን ማርቆስ ይናገራል፡፡
በዚህ ተግባር የሚሳተፉት የቡድን አጋሮች ከምንም በላይ የህሊና እርካታ እንደሚያገኙበት ይናገራል፡፡ “ሌሎች ቡድኖችም በእንደዚህ አይነት ተግባር ያልተሳተፉ ካሉ እንዲሳተፉ በራችን ክፍት ነው” በማለትም ሃሳቡን አካፍሏል፡፡
“ከጤና ስፖርት እግር ኳስ ቡድን አባላት መካከል የልጅ አባት ለሆነ አባል በግ በመግዛት አራስ ጥየቃ እንሄዳለን። እንደዚሁም በሀዘን ጊዜ አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ከሀዘንተኛው አጠገብ በመሆን እናጽናናለን፡፡ በተለይም ደግሞ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያለን አቋም ጠንካራ ነው” ሲል አጫውቶናል፡፡
የሀዋሳ ከተማ ጤና ስፖርት ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ፣ የውድድር ስነ-ስርዓት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ እንደዚሁም የአማ ጤና እግር ኳስ ቡድን አባል ሄኖክ ጌታቸው ስለውድድሩ ሲናገር፦
“እየተካሄደ ያለው ውድድር ‘አሊ ካፕ’ ይባላል፡፡ ስያሜውንም ያገኘው በቅርቡ በሞት ለተለየን ወንድማችን አለማየሁ ሽፈራው መታሰቢያ ነው፡፡ በሀዋሳ ከተማ ለሟች ቤተሰቦች ድጋፍ ይረዳ ዘንድ ድጋፍ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡
“እኛም ደግሞ የበኩላችንን ለማበርከት ውድድር በማዘጋጀት ለቤተሰቦቹ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ በ28 ክለቦች መካከል ጥሩ የሚባል የጥሎ ማለፍ ውድድር እና ድጋፉ ደስ በሚል ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
“የውድድሩ ዋናው ዓለማ ደግሞ የወንድማችንን አሊ ቤተሰብ መርዳት ስለሆነ ያለው የውድድር ድባብ እና ፉክክር ያማረ ነው፡፡ ይሄም ውድድር እሱ ትላንት ለስፖርቱ ቤተሰብ ለሰራው ሥራ ምላሽ ጭምር ስለሆነ ሁሉም ክለቦች ደስ ብሏቸው እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
“እየተካሄደ ላለው ውድድር በርካታ አካላት ድጋፍ አድርገውልናል። ከእነዚህም መካከል የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ስፖርት መምሪያ እና የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለውድደሩ ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
“እነዚህ አካላት ዳኞችን በመመደብ፣ ሜዳዎችን በመፍቀድ እና የማስተባበር ሥራ በመስራት እየደገፉ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ውድድሩን የሚመሩት ዳኞች በነጻ እያጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ለዳኞቹም የላብ መተኪያ በሚል ክለቦች ይከፍላሉ፡፡
“የቡድኖች ተጫዋቾች በቀጣይም የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ላይ ለመሳተፍ አቅደዋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ውስጥ 55 የሚደርሱ የጤና ስፖርት ቡድኖች ይገኛሉ፡፡ አሁን በእርዳታው ያልተሳተፉ ቀሪ 27 ቡድኖችን በማሳተፍ ክረምት ላይ የአሊን ልጆች በቀጣይነት ለመደገፍ ሰፊ እቅድ አላቸው፡፡
“እስካሁን 1 መቶ 72 ሺህ ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በውድድሮች መካከል የሚደረጉ ድጋፎች አሉ፡፡ ውድድሩ ሲጠናቀቅ ድጋፉ የሚቀጥልበት ሁኔታ ይኖራል” ሲል አጫውቶናል፡፡
አንድ ውድድር የበለጠ ውበት የሚኖረው ሽልማት ሲኖረው ነው፡፡ ውድድሩ ሲጠናቀቅ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ክለቦች ሽልማት ተዘጋጅቷል። ሜዳሊያን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶች መዘጋጀታቸውን ሄኖክ ይናገራል፡፡
ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ የጤና እግር ኳስ ስፖርት ውድድር ሲካሄድ መቆየቱን ወጣት ሄኖክ ጠቁሟል። ይህም ደግሞ ተሳታፊዎቹ ጤናቸውን በመጠበቅ የእርስ በእርስ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አግዟል፡፡
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት