ስምምነቱን ለማጽናት ፍቱን መሥመሮች

ስምምነቱን ለማጽናት ፍቱን መሥመሮች

በፈረኦን ደበበ

የሀገራችንን መሠረታዊ የልማት ችግሮችን በመመልከት መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ትክክለኛ ነው፡፡ በታሪክ ያጣናቸውን ዕድሎች ለመመለስና የቀጣዩን ትውልድ ህይወት ለማቃናት ሁሉ ይረዳል፡፡

ለቀይ ባህር ሲባል ደማችንን ስንገብር እንዳልኖርን ሁሉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን እጃችንን አጣጥፈን እንድንቀመጥ ተገደናል። ሀገራዊ ጥቅማችንን አጥተን ለሥቃይና እንግልትም ተዳርገናል፡፡ የባህር በር በማጣታችን መነሻ፡፡

ስለሆነም የሀገራችንን አንድነትና እድገት በተገቢው ለማስጠበቅ የተነሳሳው መንግሥት ሀገር በቀል የለውጥ እርምጃዎች እያካሄደ ይገኛል፡፡ በታሪክ ያጣናቸው ዕድሎችን ሁሉ እየፈተሸ ለማስተካከል ጥረቱን ቀጥሏል። ምንም እንኳን የተዘጋውን በር ለመክፈት ተግዳሮቱ ብዙ ቢሆንም፡፡

እየገጠሙ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ሁሉ በመጋፈጥ መንግሥት ሰሞኑን ያስተላለፈው አንድ መልካም ዜና ኢትዮጵያዊያንን አስደስቷቸዋል፡፡ አንገታቸውን ካቀረቀሩበት ቀና እንዲሉና ከሚሠማቸው ትካዜም እንዲላቀቁ የሚያደርግ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያዊያን ሠላም ለማስከበር ሲባል በሶማሊያ ምድር ህይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የእኛ ልማት ካለእነሱ ሠላም አይረጋገጥም በሚል ድጋፍ እየተሰጡና ከአሸባሪው አልሻባብ ጋር ፊት ለፊት ግጥሚያ እያደረጉ ሀገሪቱን ከዳግም መፈረካከስ ታድገው ነበር ያቆዩት፡፡

መንግሥትም ይህን ዕሳቤ ሳይቀይር ወንድም ከሆነው የሶማሊያ ህዝብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ እየሠራ እያለ ነው ለሀገራችንና ለህዝባችን ቋሚ የሆነ ቅርስ ለመጣል የተነሳሳው፡፡ ይህ ደግሞ የማንንም መብት ሳይጋፋ ለሀገሩ አንገብጋቢ የሆነውን ችግር በመቅረፍ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተገንዝቦ ነው የባህር በር ጥያቄውን ለጎረቤቶቹ ያቀረበው፡፡

የባህር በርን የማግኘት አንዱ አማራጭ ሶማሊ ላንድ ከተባለችውና ካለፈው 3ት አስርት ዓመታት በላይ እራሷን በራሷ ስታስተዳድር የቆየችውን ግዛት መጠየቁ ተጠቃሽ ሲሆን በርበራ የተባለውንም ወደብ በጋራ ለማልማት መንግሥታችን ስምምነት አድርጓል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት ግን ሀገራችን የምትሰጠውን ድጋፍ ከቁብ አልቆጠረም፡፡ ያለብንን ችግር እያወቀ አንድም ቀን ቀና ምላሽ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ የሶማሊ ላንድ መንግሥትን በአመጽ እየፈረጀና ውሎ አዷሯን ሁሉ ለመቆጣጠር እየሞከረ ካለ ወዳጅ እንድትቀር ሲያስገድዳትም ከርሟል፡፡

ይህ ሁሉ ጫና ቢደረግም የቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበሩት የግዛቲቱ ህዝቦች አንድም ቀን ለሶማሊያ መንግሥት እጅ ሳይሰጡና ሳይንበረከኩ ቆይተዋል፡፡ በድርድር ስም ላስታርቃችሁ የሚሉ ወገኖች ሲመጡም “በፍጹም መታረቅ አንችልም” እያሉ የተናጠል ህይወት ነው እየገፉ የቆዩት፡፡ ለዚህ በቅርቡ ለዩጋንዳው ፕሬዝዳንት የሰጡት ምላሽ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ይህ አቋማቸው አንዴ በሙስና ሌላ ጊዜ በብልሹ አሠራርና ከዚያም አልፎ በሠላም እጥረት እየተናጠ ላለው ለሶማሊያ መንግሥት ትምህርት ሰጪ ነው፡፡ ግጭትና ጦርነት የለባትም የተባለችውና ሠላማዊ የውሰጥ አስተዳደር እየገነባች ያለችው ግዛት ወደፊትም ቢሆን ውጥረት ከተሞላበት ሶማሊያ ጋር እንደማትዋኽድ ነው እየገለጸች ያለችው፡፡

4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ፣ የራሷ መገበያያ ገንዘብና ሁሉንም መንግሥታዊ አገልግሎቶች እየሰጠች ያለችው ግዛቲቱ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ነበር ከሶማሊያ የተነጠለችው፡፡ በዚህ አቋሟ ላይ ነው በቅርቡ  ሀገራችን የባህር በር ጥያቄዋን ይፋ አድርጋ ያቀረበችው፡፡ በጋራ የመልማት ፍላጎትና መተባበርን መሠረት በማድረግ፡፡

ይህ በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተው መርህ የማንንም ጥቅም የማይጎዳና ከፍላጎት ጋርም የማይጻረር ሆኖ እያለ የሶማሊያ መንግሥት ግን ሠሞኑን አፍራሽ አስተያየቱን ማውጣት ጀምሯል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባህር በር ጥያቄ እንጂ ማንንም ለመውረር አለመሆኑን ለዘመናት ከምትከተለው ባህሪ ሁሉ መገንዘብ ይችሉ ነበር፡፡

እውነታውን ወደ ጎን በማለት የሚናገሩት ቃላትና እንዲሁም ለመሄድ እየተዘጋጁበት ያለው መንገድ በሀገራቸውና በቀጠናው ያለውን ችግር ከማባባስ በቀር ምንም ገንቢ ሚና የለውም፡፡ ግለሰብም ሆነ ሀገር መደጋገፍ ሳያደርግ ብቻውን መቆም በማይችልበት በአሁኑ ዓለም የሀገሪቱ መሪዎችና አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች እያስተላለፉ ያሉት የጥላቻ ንግግር እና መግለጫ የሚያሳስብ ነው፡፡

ድርጊታቸው ከኃያላን መንግሥታት ፍላጎት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአፍሪካ ህብረትና እንዲሁም ከኢጋድ መርሆ ጋርም ይጻረራል ፤ምክንያቱም ሁሉም አካላት በህዝቦች መካከል የሚፈጠረውን ሠላማዊ ግንኙነት ስለሚደግፉ፡፡ በተለይ ኃያላን ሀገራት ከአካባቢው ሀገራት ጋር ውል በመግባት ንግድና የተለያዩ የጸጥታ ማስከበር ሥራዎችን ማከናወናቸው የዚሁ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ከሶማሊያ ጋር መሆን ወይም መገንጠል የሶማሊ ላንድ ህዝብ ፍላጎት ብቻ እንጂ የኢትዮጵያ አቋም የማንንም ሉዓላዊ መብት ያልተጋፋ እስከሆነ ድረስ ሀገራችንም የሚገጥማትን መሰናክል ለማለፍ በቁርጠኝነት መሥራት እንጂ ሌላ ምንም አማራጭ አይኖራትም፡፡ በራሷ ላይ ሊደርስ የሚችለውንም ጉዳት እንዲሁ መከላከል ይኖርባታል፡፡

የሶማሊ ላንድ ህዝብ የረጅም ጊዜ የነጻነት ህልም በኢትዮጵያ መንግሥት ቀስቃሽነት ተነሳስቷል የሚሉት ያሁኖችና የቀድሞዎቹ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት የሚፈጥሩትን መሰናክል ለመቀልበስ ሀገራችን ልታከናውን የሚገባቸው ፖለቲካዊ ሥራዎች ብዙ ናቸው፡፡

በተለይ በሀገር ውስጥ፣ በሶማሊ ላንድ፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከኃያላን መንግሥታት ጋር ሊፈጠር የሚችለው መስተጋብር እንቅፋቱን ለመቀልበስ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን በሀገር ውስጥ ግን መንግሥት እስካሁን ሲያደርግ እንደነበረው የባለሙያዎችና የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎን ማጎልበት ይገባል፡፡ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ሁሉም አስተዋጽኦ ሊኖረው ስለሚገባ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙሀንና የተለያዩ ህዝብ አደረጃጀቶችም ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ለመልካም ተብሎ የተጀመረው ሥራ በአደናቃፊዎች ተሰናክሎ እንዳይቀር ለማድረግ፡፡

የባህር በርን ለዘመናት እንደ ዓይን ብሌኑ ሲጠብቅ የኖረው የሀገራችን ህዝብ ወደብ አልባ ህይወት ሲመራ ቆይቷል፡፡ አንዳንድ ወገኖች ችግሩን ከወቅታዊ የኑሮ ውድነትና ሌሎች ችግሮች ጋር እያወሳሰቡ አቅጣጫ እንዳያስቱ የመከላከል ሥራም ሊሠራ ይገባል።

ስለ የባህር በር አስፈላጊነትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚረዱት ኃያላን መንግሥታትም ጉዳዩን ተረድተው የራሳቸውን ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል ፤ምክንያቱም በተለያዩ የውይይት መድረኮች የሚሰጧቸው አስተያየቶች ተሰሚነት ያላቸው እንደመሆኑ፡፡ ይህንን በሚጻረር መልኩ ያልሆነ ውሳኔ ከሰጡም እንዲሁ ሁኔታዎችን የማወሳሰብ አቅም ስለሚኖራቸው፡፡

ባለፈው ዓመት ከኬኒያ ጋር በድንበር ምክንያት የገቡበትን ውዝግብ እያስታወሱና በፍርድ ቤት እንረታለን እያሉ እየፎከሩ ያሉት የሶማሊያ ባለሥልጣናት አሁን የተፈጠረውን ክፍተት ለመጠቀምም እየተንደረደሩ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ሶማሊ ላንድ ከተነፈገችው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ጋር ይገናኛል፡፡

ግዛቲቱ ከ30 ዓመታት በላይ የራስ አስተዳደር ዘርግታና መንግሥታዊ ሥርዓት መሥርታ እያለ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና መነፈጓ እንደ ድክመት ይወሰዳል፡፡ ሁኔታው ለዓመታት ከግዛቲቱ ጋር ምንም ዓይነት አዎንታዊ ግኝኙነት ያልነበረው የሶማሊያ መንግሥት አሁን ላይ የበላይ ጠባቂነት ሥልጣን አለኝ የሚለውን ጥያቄ እንዲያነሳም ረድቶታል፡፡

ስለሆነም ሀገራችን ከችግሩ በአሸናፊነት ለመውጣት የግዛቲቱን ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና መደገፍ ቀዳሚ ተግባሯ ሊሆን ይገባል፡፡

በህዝቦችና ሀገራት መካከል መልካም ወዳጅነት እንዲፈጠርና አካባቢያዊ ትሥሥር እንዲጠናከር እየሠሩ ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረትና ሌሎች አካላትም ጉዳዩን በሰከነ አግባብ እንዲገነዘቡ የማድረግ ሥራ ሊሠራ ይገባል። ምክንያቱም ግጭት በለሌበት ቦታ ወረራ ተፈጸመ ወዘተ እያሉ የሃሰት መረጃ የሚነዙ የሶማሊያ መሪዎች አቋም ሊጋለጥ ስለሚገባ፡፡