በኮንታ ዞን አመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የእናቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
በአመያ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ሲያገኙ ካነጋገርናቸው እናቶች መካከል ወ/ሮ ቅድስት ዳርጫ የጫታ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፥ በሆስፒታሉ የጤና ባለሙያ እንክብካቤ እና እገዛ ጤነኛ ልጅ መገላገል መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
በወሊድ ምክንያት የሚያጋጥም የደም መፍሰስ ችግር እንዳያጋጥም እናቶች በጤና ተቋማት ሊወልዱ እንደሚገባ አመላክተው፥ ከዚህ በፊት በቤት በወሊድ ምክንያት የደም መፍሰስ ችግር ተጋላጭ መሆኗን የገለጸችው ወ/ሮ ቅድስት፥ በጤና ተቋም የወሊድ ክትትል በማድረግ ልጃቸውን በሰላም መገላገል መቻላቸውን ተናግረዋል።
ወ/ሮ ደስታ ፋንታ የአመያ 02 ቀበሌ ነዋሪ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የቅድመ ወሊድ ክትትል ለስምንተኛ ጊዜ እንደመጡና ለእናቶችና ህፃናት የሚሰጠው አገልግሎት የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ የእናቶችና ህፃናት ክፍል አስተባባሪ ገብረሚካኤል ታደስ በሆስፒታሉ የእናቶችና ህፃናት ለመቀነስ የእናቶች ቅድመ-ወሊድ ክትትል እንዲያደርጉ በተፈጠረው ግንዛቤ በስድስት ወር ውስጥ 665 እናቶች የመጀመሪያ ዙሪያ ክትትል በማድረግ አልትራሳውንድን ጨምሮ ሌሎች የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ሙሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከ400 በላይ እናቶች በሆስፒታሉ የወሊድ አገልግሎት እንዳገኙ ያነሱት አቶ ገብረሚካኤል፥ የህፃናት ሞት መመዝገቡ አሁንም የባለድርሻ አካላት ርብርብ አስፈላጊ መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ሀረገወይን የአመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሥራ አስኪያጅ ተወካይ በበኩላቸው፥ በሆስፒታሉ ከአዋላጅ ነርሶች ጀምሮ የወላድ እናቶች ምጥ ከረዘመ የቀዶ ህክምና ዶክተሮች የተሟሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
ሆስፒታሉ በጤና ባለሙያዎችና ህክምና መገልገያ መሣሪያዎች የተደራጀ ስሆን የውሃ መስመር ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የአመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በዞኑ ብቸኛ ሆስፒታል በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የሚገልጹት የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኡቴ አየለ፥ በዞኑ ባሉት 39 መሠረታዊ የጤና ኬላዎች አራት አጠቃላይ ጤና ኬላዎች የጤና ባለሙያዎች ተመድቦ የእናቶች ቅድመ ወሊድ ክትትልና የህፃናት ክትባት ሥራ እየተሠራ እንዳለ ጠቁመዋል።
በዞኑ አንድ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልና አራት ጤና ጣቢያዎች ላይ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ለእናቶች የወሊድ አገልግሎት እየተሰጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፥ ክፉኝና የጉበት ክትባት ጨምሮ ከአስር በላይ ክትባቶች ለህፃናት ተደራሽ መሆኑን አስረድተዋል።
የህክምና አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የአመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ጠቅላላ ሆስፒታል ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ያነሱት አቶ ኡቴ፥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አስተላልፏል።
አመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ300 ሺ በላይ ለሆነ የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎት ይሰጣል።
ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፋ መጀመሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት አስታወቀ
በኮሬ ዞን አራተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፈ ተጀመረ
የጡት ካንሰር ተገቢው ህክምና በወቅቱ ካልተደረገ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ እንደመሆኑ ድንገት ሲያጋጥም በባህል ህክምና ከመዘናጋት ይልቅ በአፋጠኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ተገቢ ነው – ዶክተር ተሾመ አለምቦ