በአጋጣሚ ሳይሆን በዋጋ ነው!

በአጋጣሚ ሳይሆን በዋጋ ነው!

በአለምሸት ግርማ

አካል ጉዳተኝነት በተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ በሆኑ ክስተቶች ሊያጋጥም ይችላል።በመሆኑም ማንኛውም ሰው ድንገት የአካል ጉዳት ሰለባ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። በተለይም በተፈጥሮ ከሚከሰተው አካል ጉዳት ባሻገር በሰው ሰራሽ አደጋ የሚከሰተው የአካል ጉዳተኛውን ቁጥር መጠን ከፍ እያደረገው መሆኑ ይነገራል። ሆኖም አካል ጉዳተኛው ህጎችናአዋጆች የሚፈቅዱለትን መብት በመጠቀም ራሱን መቻልና ማስተዳደር ይኖርበታል።

መብቱን ማወቅና መጠቀም እንዲችል ግን በተለይም ዕድሜያቸው ለጋ የሆኑ አካል ጉዳተኞችን በማስተማር ኃላፊነትን መወጣት ይገባል። ለዚህም ወላጅ፣ አሳዳጊ፣ በጎ አድራጊ ድርጀቶች ሚናቸው ከፍ ያለ ነው። ወይዘሮ ሲሳይ ታደሰ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በይርጋለም ከተማ ሲሆን አሁን ነዋሪነቷ በሃዋሳ ከተማ ነው። በችያለሁ አምዳችን የህይወት ልምዷን እንድታካፍለን ጋብዘናታል። ለቤተሰቦቿ አራተኛ ልጅ ናት። ስትወለድ ጉዳት አልባ ነበረች። አራት አመታትን ካሳለፈች በኋላ ነበር የጉዳቷ መንስኤ የሆነ እክል የገጠማት። ማንኛውም ልጅ ሲጫወት እየወደቀ እየተነሳ ቢሆንም ያቀን ግን ለሲሳይ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳት አልሆነላትም።

ያጋጠማት የመውደቅ ችግር በወቅቱ ዘላቂ የሆነ ጉዳት ያስከትላል ያለ ማንም እንደልነበር ታስታውሳለች። “ብዙ ጊዜ ወድቀሽ ታውቂያለሽ፤ ከዚያም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ ይመለሳል። የዚያን ቀን የወደቅሽው ግን የተለየ ሁኔታ ይዞ ነው የመጣው ብለው እናቷ ናቸው ያጫወቷት።” ይሁን እንጂ ያኔ ያጋጠማት መውደቅ እንደታሰበው ወይም እንደተለመደው አልነበረም። የቀኝ እግሯ አንደቀድሞው አልታዘዝ አላት። ቤተሰቦቿም ነገሩን ቀለል አድርገው በማየታቸው ፀበል እና ባህላዊ ህክምና አድረገውላት እንደነበርም አጫውተዋታል። ይሁን እንጂ እንደቀድሞው መሆን አልቻለችም። በዚህም ምክንያት ቆሞ መራመድስለተሳናት በእንብርክክ ለመሔድ ተገደደች። በዚያም ከከተማ ትንሽ ወጣ ከሚለው የገጠር ቀበሌ ቀላል የማይባል የእግር ጉዞ በማድረግ ነበር ትምህርቷን እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ የተከታተለችው።

በወቅቱ የነበረውን ነገር ስትናገር “ቤተሰቦቼ በተለይም እናቴ ትልቅ እገዛ ታደርግልኝ ነበር። ችግሬንም በቅርበት ስለምታይ ስለእኔ ትጨነቅ ነበር። “ባደረገችው ጥረት በአቅራቢያችን የነበሩ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ገብቼ እንድማር አመቻቸችልኝ። በዚያም ባገኘሁት ዕድል መሰረት ገብቼ ያለችግር መደበኛ ትምህርቴን መከታተል ቀጠልኩ። የተሻለ ህክምና ማግኘትም ቻልኩ። ቀዶ ጥገናም ተደረገልኝ። በዚህም ከቀድሞው የተሻለ አካሌ ለውጥ ማምጣት ቻለ። በድጋፍ ቢሆንም ከቀድሞው የተሻለ መንቀሳቀስ ቻልኩ።

“በዚህ ሁኔታ ትምህርቴን ከተከታተልኩ በኋላ በ2006 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ የመግባት ዕድሉን አገኘሁ። በእርግጥ ወቅቱ ጎንደር ዪኒቨርሲቲ ቢደርሰኝም ካለብኝ ችግር ከቦታው ርቀት አኳያ ወደ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስቀይሬ ሃዋሳ ዪኒቨርሲቲ ገባሁ። “በዚያም በሶሲዎሎጂ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቴን ተከታትዬ ተመርቄያለሁ። አሁን በሃዋሳ ከተማ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሴቶች እና ህፃናት አደራጅ ባለሙያ በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ። “በስራዬ ብዙ ሴቶችን የማግኘት ዕድል አለኝ። ሴቶች በተለያየ ሙያ እንዲሰማሩ እና የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው እናደርጋለን። በዚህም ብዙዎች እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አካል ጉዳተኞችን የማሳተፉ ነገር ላይ አሁንም ክፍተት ያለ ይመስለኛል በማለት በስራ አጋጣሚ የታዘበችውን አጋርታናለች።”

ወይዘሮ ሲሳይ ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት ነች። ባለቤቷ ጉዳት አልባ ቢሆንም ከውጪ ሲገቡ የቤት ውስጥ ስራዎችን በጋራ እንደሚያከናውኑ አጫውታናለች። ማድረግ የማትችለውን እንዲያግዛት ትፈልጋለች እንጂ መቀመጥ አትወድም። እሱም የሚችለውን ሁሉ በመስራት ያግዛታል።በዚህም ደስተኛ ህይወት እየመሩ መሆኑን ትናገራለች። በቀጣይ ያሰበቻቸውን ዕቅዶቿንም እንዲህ በማለት ነበር ያጋራችን፦ በቀጣይ ራሴን ለመቀየር በትምህርቴ መግፋት እና በሙያዬ ራሴን ማሻሻልና ብዙዎችን ማገዝ እፈልጋለሁ። በተለይም አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍና በማገዝ የራሴን አሻራ ማሳረፍ እፈልጋለሁ።

ፈጣሪ ከረዳኝ ስራን ፈጥሬ አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍና ተጠቃሚ ማድረግ ትልቁ አላማዬ ነው። እኔ በመማሬ ተወልጄ ባደኩበት አካባቢ አርኣያ መሆን ችያለሁ። በዚያ አካባቢ አካል ጉዳተኛ ልጆች ያላቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን የማውጣትና የማስተማር ልምዳቸው ዝቅተኛ ነው። በዚያ አካባቢ የሚያገኙኝ ወላጆች ተጠግተው እኔኮ አካል ጉዳተኛ ልጅ አለኝ፤ እንዴት ላድርግ ብለው የሚያማክሩኝ ብዙዎች ናቸው። ይህም የግንዛቤ ችግር መኖሩንና ብዙ መሰራት እንዳለበት ያመላክታል። “እኔ እዚህ ለመድረሴ ብዙዎች ዋጋ ከፍለውልኛል። ቤተሰቦቼ ደብቀውኝ ቢሆን እዚህ መድረስ አልችልም ነበር።በተለይም እናቴ ትልቁን ድርሻ ትይዛለች። ፍሬውን ለማየት ባትታደልም ለስኬቴ ብዙ ለፍታለች። ከእኔጋር አብራ ተሰቃይታለች። ማገዝ በምትችለው ሁሉ አግዛኛለች፤ በእኔ አፍራ አታውቅም። በአጋጣሚ ትምህርቴን ሳልጨርስ ነው ያረፈችው። ሆኖም ታላቅ ወንድሜ የእናቴን አቋም ስለሚያውቅ እሷን ተክቶ ዋጋ ከፍሎልኛል። እኔ ሀዘኑ በጣም ስለከበደኝና እሷን ማጣት ስላሰጋኝ ትምህርቴን ለማቋረጥ አስቤ ነበር በወቅቱ። ነገር ግን ወንድሜ ማቋረጥ የለብሽም ትምህርትሽን ጠንክረሽ መቀጠል አለብሽ ብሎ አበረታትቶ ለዚህ እንድበቃ አድርጎኛል። ስለዚህ በተለይ አካል ጉዳት ያለባቸውን ልጆች ቤተሰብ አካል ጉዳተኛውን መርዳትና እንዲማር ማድረግ ይኖርበታል። ካልሆነ ግን አካል ጉዳተኛው የተደራራቢ ጉዳቶች ሰለባ ነው የሚሆነው።

ቢማር እና ራሱን ቢችል ግን ከራሱ አልፎ ለሌላውም መጥቀም የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረስ ይችላል። አካል ጉዳተኛን ቤት ውስጥ መደበቅ የግለሰቡን መብት ከመጣስ በተጨማሪ ሀገርንም ጥቅም ማሳጣት መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል ስትል ነው አስተያየቷን ያጋራችን። አካል ጉዳተኝነት የሁሉም ጉዳይ ነው። በተለይም በቤታችን ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያችንየሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ከቤት እንዲወጡና ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ልናደርግ ይገባል። አካል ጉዳተኛ የሆነ ግለሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ ካገኘ የማይለወጥበት ምክንያት የለም።

ለመለወጥ ግን በጉድለቱ ሊታገዝ ያስፈልጋል። ስኬት በዋጋ እንጂ በአጋጣሚ ስለማይመጣ ልናግዛቸው ይገባል የሚል አቋም አላት። በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ሊስተካከል ይገባል የምትዪው ምንድነው? ብለን ላነሳንላት ጥያቄ እንዲህ ስትል መልሳልናለች፦ በእርግጥ አሁን በመንግስትም ሆነ በአጋር ድርጅቶች ከቀድሞው የተሻለ ነገር እየተሰራ ነው።አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአካል ጉዳተኛ አጋዥ የሆኑ ነገሮች እጥረት አለ። ያንን በመፍራት ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ሰዎች አሉ። በስራ ላይ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችም አንዳንድ ጊዜ መድሎ ያጋጥማቸዋል። ለሚጠይቁት አጋዥ መሳሪያዎች፣ ትራንስፖርትና የመሳሰሉት ተገቢ ምላሽ አይሰጣቸውም። በተለይም ሴት አካል ጉዳተኞች በእርግዝናና ወሊድ ወቅት ከጉዳት አልባው እኩል ሊታዩ አይገባም። ችግሮቻቸው ከግንዛቤ ልገቡ ያስፈልጋል። እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች የሰውን ስነ-ልቦና የሚጎዳ በመሆኑ ሊስተካከሉ ይገባል።

አካል ጉዳት ከመስራት አያግድም። በየትኛውም አጋጣሚ ሲለምን የማገኘውንአካል ጉዳተኛ ስራ እንዲሰራ ሳልመክረው አላልፍም። ስራ መስራት ያስከብራል። ከልመና አመለካከት ራስን ማውጣት ያስፈልጋል። አካል ጉዳት ለልመና አይዳርግም። ስለዚህ ማንኛውም አካል ጉዳት ያለበት ሰው ሰርቶ እንጂ ለምኖ ማደር የለበትም ስትል ነው አያይዛ ለአካል ጉዳተኞች ምክሯን የለገሰችው። አካል ጉዳት ሁሉም ሰው ላይ በተለያየ አጋጣሚ ሊከሰት ይችላል።

በምን፣ እንዴትና መቼ እንደሆነ ባይታወቅም ሁሉም ሰው ለአካል ጉዳት ተጋላጭ በመሆኑ የአካል ጉዳተኛ ጉዳይ አይመለከተኝም ማለት አይቻልም። ይልቁንም በጋራ በመስራት የግንዛቤ ለውጥ እንዲመጣ ልንሰራ ይገባል!