ጉዞ በተራሮች የወገብ መቀነት ላይ
በአንዱዓለም ሰለሞን
ማልጄ ነበር ከቤት የወጣሁት፤ ለ12 ሩብ ጉዳይ፡፡ የውጪው ቀዝቃዛ ዓየር እንቅልፌን አባረረልኝ፡፡ የባበጃጅ መያዣው ከቤቴ ብዙም አይርቅም፡፡ ወልደ አማኑኤል አደባባይ፣ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ህንጻ ፊት ለፊት ያለው ቦታ ላይ በርካታ ሰዎች ማልደው ተነስተው ስፖርቱን ተያይዘውታል፡፡ ስፖርቱ ከስፒከር በሚወጣ ሙዚቃ የታጀበ ነበር። ጾታና የዕድሜ ክልል ሳይለይ ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይሰራሉ፡፡
አስፓልቱን ተሻግሬ ባጃጅ ጥበቃ ቆምኩ፤ ወደ አሮጌው መናኻሪያ ለማምራት፡፡ አጠገቤ ሁለት በዕድሜ ጠና ያሉ ሴቶች ነበሩ፤ እንደ እኔው ባጃጅ የሚጠብቁ፡፡ አንድ ባጃጅ መጥቶ ከፊት ለፊታችን ቆመ፡፡ “መናኻሪያ ናችሁ? 30 ብር ትከፍላላችሁ ግቡ” አለ ሾፌሩ፡፡
“20 ብር ውሰደን” አለች አንደኛዋ ሴቲዮ።
ሾፌሩ ተስማማ፡፡ ወደ ባጃጇ ስንገባ አንድ ወጣት እየተጣደፈ መጣ፡፡ ሾፌሩም አጠገቡ አስቀመጠውና ጉዞውን ጀመረ፡፡
መናኻሪያ ስንደርስ ትኬት ወደ ትኬት መቁረጫው አመራሁ፡፡ የጉዞ መዳረሻዬ የባስኬቶ ዞኗ ዋና ከተማ፣ ላስካ ነች፡፡ እናም ከሀዋሳ ሳውላ አምርቼ ከሳውላ ወደ ላስካ አቀናለሁ ማለት ነው፡፡
“ሳውላ ስንት ነው?” በማለት ትኬት ቆራጯን የጉዞውን ዋጋ ጠየኳት፡፡
“የሳውላ መኪና የለም” አለችኝ፡፡
ያለው አማራጭ ወላይታ መሄድ ነበር። የወላይታ ትኬት ቆርጨ ወደ መኪናው አመራሁ፡፡ የመጀመሪያው መኪና ሞልቶ ነበር፡፡ ቀጣዩ ላይ ገብቼ እስኪሞላ ድረስ እጠባበቅ ጀመር፡፡ መኪናው ለመሙላት ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ 12፡30 ከመናኻሪያ ወጣን፡፡
ሰፈር ስንደርስ “ባለሞንታርቦዎቹ” ስፖርተኞች አልነበሩም፡፡ ዘግይተው የመጡቱ ቦታው ላይ ውር ውር ይላሉ፡፡ ይህ ነገር እየተለመደ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
የወልደ አማኑኤል አደባባይን አልፈን፣ በአዲሱ መናኻሪያ አድርገን ጉዟችንን ቀጠልን። መኪናችን ፈጣን ነበር፡፡ በመንገዳችን ላይ ያሉትን ከተሞች ገና ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ ነበር ያለፍናቸው፡፡ በመንገዳችን (ኬላውን እንዳለፍን) ያየነው የመኪና አደጋ ግን መረጋጋትን የሚያስገነዝብ ነበር፡፡ አንድ ሲኖ ትራክ አይሆኑ ሆኖ ተገልብጧል፡፡
ቱላ፣ ሞሮቾ፣ ይርባ፣ በሊላ፣ ዲምቱ፣ ብላቴ፣ ቢጠና እያልን ተጉዘን፣ ሶስት ሰዓት ላይ ሶዶ ደረስን፡፡ ቁርስ ከበላሁ በኋላ ወደ ሳውላ ለመሄድ ትኬት ቆረጥኩ፡፡ አጋጣሚው ጥሩ አልነበረም፡፡ የመጀመሪያው ተሳፋሪ እኔ ነበርኩ፡፡ ቁርስ በምበላበት ቅጽበት የሞላ መኪና እንዳመለጠኝ ተገነዘብኩ፡፡ አማራጭ አልነበረኝም፤ ወደ ውስጥ ዘልቄ ከሾፌሩ አጠገብ ካለው ወንበር ላይ ተቀመጥኩ፡፡
እንደተቀመጥኩ የታዘብኩት ነገር አስገረመኝ፡፡ በእኔ ወንበርና በሞተሩ መካከል ሁለት አነስተኛ የፕላስቲክ ጀሪካኖችን በመሰንቀር አንድ አነስተኛ ወንበር ተበጅቷል። “ትርፍ ሰው” መጫኛ መሆኑ ነው፡፡ ጉዞ ስንጀምርም የሆነው ይኸው ነበር፡፡ ከወንበሯ ባሻገርም ሞተሩ ላይ ሌላ ሰው ተቀምጧል።
ያውም ደግሞ ፖሊስ፡፡ በመንገዳችን ላይ የነበሩት ትራፊኮች ሁኔታውን ቢታዘቡም ነገሩን በዝምታ ከማለፍ ውጪ ያደረጉት አንዳች ነገር አልነበረም፡፡
መኪናው እስከሚሞላ መጠበቁ ግን አሰልቺ ነበር፡፡ ይሄኔ የመኪና ረዳቶች ትዝ አሉኝና አዘንኩላቸው፡፡ ግን ደግሞ እነርሱ ሥራቸው ነውና ነገሩን ለምደውታል። ደግሞም እኮ ዝም ብለውም አይደለም የሚቀመጡት፡፡ “ነይ እናቱ፤ ሳውላ ነሽ?”፣ “አርባ ምንጭ ከሆንክ የሞላ መኪና ይኸው”፣ ሰላም በር ነሽ? ትኬት ቆርጠሻል? እዚህ ላይ ግቢ” … እያሉ ሥራቸውን ያቀላጥፋሉ፡፡
መኪናው እስከሚሞላ ለሶስት ሰዓት ያህል ጠበቅን፡፡ የልብስ ቦርሳዬ ውስጥ መጽሀፍ አለመያዜን ሳስታውስ ተበሳጨሁ። ለወትሮ እንደ ቅያሪ ልብሴ ሁሉ ትኩረት የምሰጠው ነገር ነበር፡፡ (ይሄኔ ነው እንግዲህ “ስማርት ፎን” ያለመጠቀም ጉዳቱ) እናም ያለኝ አማራጭ ከገዛ ራሴ ጋር ማውጋት ነበር፡፡ ለነገሩ የምደሰትበት ነገር ነውና አልጠላሁትም።
ከሀሳቦቼ መካከል፡- “መቼ ይሆን ግን ከጥበቃ የምንወጣው? ከነጮች እርዳታ ጥበቃ ወጥተን ራሳችንን የምንችለው? መቼስ ነው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምትሆነው?
“እኛ እኛን፣ ራሳችንን መሆን ስንችል::
“እኮ መቼ?
“እሱን በውል ለማወቅ ይከብዳል::
“እስቲ እንደው በግምት?
“እንግዲህ እሱ የሚወሰነው እንደ እኛ ሁኔታ ነው፤ እንደ ትውልዱ…›
የትውልዱን ሁኔታ አሰብኩትና ጥያቄዬ ምላሽ የሚያገኝበትን ጊዜ ለመገመት ሞከርኩ። ሩቅም ቅርብም ሆኖ ታየኝ፤ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ቢኖሩም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችም አሉና፡፡
እንዲህ ከአንድ ሀሳብ ወደ አንድ ሀሳብ ስዘል ቆይቼ መኪናው ሞልቶ ጉዞ ጀመርን፤ 6፡30 ላይ፡፡ ብዙም ሳንርቅ፣ ገሱፓ ስንደርስ መኪናው ቆመ፡፡ መጀመሪያ መኪናው እንከን አጋጥሞት ነበር የመሰለኝ፡፡ ከመኪናው ወርደን ስንቆይ ግን ወደ ሾፌሩ በመሄድ ስጠይቀው የሰጠኝ ምክንያት አስገረመኝ። ረዳቱ የሾፌሩን መንጃ ፈቃድ ለማምጣት በሞተር ወደ ገሱፓ በመሄዱ ነበር የቆምነው፡፡
“ይቅርታ በጣም፤ ቶሎ ይመጣል፤ አይቆይም” አለኝ ሾፌሩ የቆምንበትን ምክንያት ከነገረኝ በኋላ፡፡ ትህትናው ደስ ይላል፡፡
ከመጠበቅ ውጪ ሌላ ምን አማራጭ ይኖራል? ረዳቱ እስከሚመጣ ድረስ ተሳፋሪዎች በአካባቢው ባሉ የንግድ ቤቶች በረንዳ ላይ አረፍ አረፍ አሉ፡፡ ከሙዙ፣ ከዳቦው፣ ከሻይ ቡናውና ከለስላሳ መጠጡ እየተቋደሱ ቆዩ፡፡ መኪና እንዳያመልጠው ብሎ ምሳ ሳይበላ የተሳፈረው መንገደኛ ርሀቡን አስታገሰ፡፡ ሌላውም በጎደለ ሞላ፡፡ ምንም ፍላጎት ያልነበረውም በሾፌሩ ነገር እየተገረመ ስለሁኔታው መኪና ውስጥ ከተዋወቀው ሰው ጋር ይጨዋወት ጀመር፡፡
ረዳቱ መጥቶ ጉዞ ጀመርን፡፡ ከወላይታ ሶዶ እስከ ሳውላ ያለውን 148 ኪሎ ሜትር ተያያዝነው፡፡ የተጀመረው የአስፓልት መንገድ አሁንም አልተጠናቀቀም፡፡ ከሠላም በር በኋላ ያለው ጎዳና መሀል መሀል ላይ ያለው ፒስታ መንገድ የጉዟችንን ጊዜ ለማራዘም ምክንያት ሆኗል፡፡
የማዜ ፓርክን ስንያያዝ የቀትሯ ጸሀይ ሙቀት እየበረታ መጣ፡፡ እኔም ከፊት ለፊት እንደመቀመጤ ለጸሀይዋ በቀጥታ መጋለጤ አልቀረም፡፡ በጉዟችን መሀል ሾፌሩ “ትርፍ ሰው” መጫኑ ደግሞ ነገሩን የባሰ መጥፎ አደረገው፡፡ ቆመው በመጓዝ ላይ ያሉትን ተሳፋሪዎችና የሰውን መተፋፈግ ሳስበው ከፊት (ጋቢና) መቀመጤ በጀኝ ማለቴ አልቀረም፡፡
ሾፌሩ ትኩረቱን መሪው ላይ እንዳደረገ ነው፡፡ እኔም በመስታወቱ ወደ ውጪ እየተመለከትኩና ከሀሳቤ ጋር እየተጨዋወትኩ ወደ መዳረሻችን መቃረባችንን እያሰብኩ ተቀምጫለሁ፡፡ ከዚህ ባሻገርም አጠገቤ ያሉ ሰዎች የሚጨዋወቱትን መስማቴም አልቀረም፡፡
“ወይ ቻይና እንደዚህ ትጫወትብን! አሁን ይህንን ድልድይ ብለው ነው የሰሩት!?” አለ ከጀርባዬ ካለው ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ ሰው በመንገዳችን ላይ ያለ አንድ ድልድይ ተመልክቶ፡፡ በእርግጥ ድልድዩ የመንገዱ አካል ሆኖ አልቀጠለም፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ባለመሆኑ ሌላ ተሰርቷል፡፡”
“የእነሱ ምን ይገርማል፤ እኛው አለን አይደለም እንዴ የራሳችንን ነገር የምናጠፋ” አለ አጠገቡ ተቀምጦ የነበረው ሰው፡፡ ከዚያም እንዲህ ሲል አከለ፡-
“ሲጀመር እኛ እነሱን ለመውቀስ ምን ሞራል አለን!?”
“እሱስ ልክ ነህ” አለ ሰውዬው ዝግ ባለ ድምጽ፡፡
ጨዋታቸውም እዚሁ ላይ ተገታ። ከሰዎች ጭውውት ወደ ጆሮዬ ከዘለቁ ንግግሮች መካከል አንዱ ጥሩ መረጃ ሆነኝ። በዕለቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሳውላ ከተማ መገኘታቸውን ሰማሁ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ እንግዶች ወደ ከተማዋ መግባታቸውንና ምናልባትም የእንግዳ ማረፊያ (አልጋ) ለማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ከሰዎች መስማቴ አስቀድሜ የራሴን አማራጭ እንድወስድ ምክንያት ሆነኝ። የማውቃቸው ሰዎች ዘንድ በመደወልም አልጋ እንዲይዙልኝ ነገርኳቸው፡፡
ከቀኑ 11፡30 ሳውላ ደረስን፡፡ ጉዞው አድካሚ ነበር፡፡ እናም የታየኝ ነገር ቢኖር ወደ ማደሪያዬ አምርቼ ሻወር ወሰድኩና አረፍ አልኩ፡፡ አስቀድሜ ወዳጆቼ አልጋ እንዲይዙልኝ ማድረጌ በእርግጥም ጠቀመኝ፡፡
በእለቱ እግር ጥሎት ወደ ከተማዋ ለመጣ እንግዳ አልጋ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ለሥራ ወደዚህች በተራሮች ወደ ተከበበችው ከተማ ባመራሁበት ወቅት ለዞኑ አስተዳዳሪ ስለጉዳዩ አንስቼላቸው ስንወያይ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ ነግረውኝ ነበር፡፡ በርግጥም በእለቱ የታዘብኩት ሁኔታ ይህንኑ እውነታ የሚያስገነዝብና ጉዳዩ አሁንም ትኩረት የሚያሻው ስለመሆኑ የሚጠቁም ነው፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው