ከራስ በላይ ለሰው (ቅን ልብ የወለደው በጎነት)
በቤተልሔም ለገሰ
አንዳንድ ጊዜ ተፈጥሮ ካደለችን መልካም ገጾች መካከል፥ የሰው ልጆች አብሮነታቸውን የሚያጸኑበት የመደጋገፍ መስተጋብር ነው። የደከመውን ደግፎ፣ የሰነፈውን ማበርታት፣ ያጣውን ማገዝ፣ የተቸገረውን መርዳት፣ የታመመውን ማሳከም… ወዘተረፈ የሰው ልጆች የጋርዮሽ ስርዓት የወለደው የኑሮ አንዱ ገጽ ነው፡፡ ለዚህ ሰናይ ምግባር እውን መሆን ደግሞ የተመረጡ ደጋግና ቅን ልቦች በየአካባቢው አይጠፉም፡፡
“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ” ነው ከሚሉት አንስቶ፥ በርካቶች ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ያበቃቸው ከታች ጀምሮ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሳይታክቱ መወጣት በመቻላቸው ነው፡፡ ልግስናን በቅን ልቦና ለማካፈል የተትረፈረፈ ሃብት ወይም ተቀማጭ ሊኖር ግድ እንደማይል ከዲላው ወጣት ነብዩ መማር ይቻላል፡፡ ለመልካም ስራ አይረፍድምና በየትኛውም አጋጣሚ ሰዎችን ለማገዝና ለመርዳት የነገሮች አለመመቻቸት ሰበብ ማድረግ እምበዛም ዋጋ የላቸውም፡፡ ወጣት ነብዩ ሊዚህ ጥሩ አብነት ነው፡፡
ወጣት ነብዩ ፍቃዱ ትውልድና እድገቱ በዲላ ከተማ ነው፡፡ እናትና አባቱ በጋራ 5 ወንድ ልጆቹን ሲያፈሩ እሱ ለቤተሰቡ 3ኛ ልጅ ነው፡፡ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ በዲላ መካነ ኢየሱስ ትምህርት ቤት ተማረ፡፡ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ደግሞ በአፄ ዳዊት ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ትምህርቱን በዲላ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቢማርም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባውን ውጤት ግን ማምጣት አልቻለም፡፡ ከዚያም የዲላ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅን ተቀላቅሎ በታይላንግ የትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ መመረቅ ቻለ፡፡ ከዚህ በላይ ግን በትምህርቱ መቀጠል አልቻለም፡፡ እንጀራ ፍለጋ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይኳትን ጀመር፡፡
አንዴ በወዛደርነት፣ ሌላ ጊዜ መኪና በማጠብ፣ ሲያሻው ደግሞ ባሬላ በመሸከም የቀን ስራ በመስራት የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ከኑሮ ጋር ግብግብ ገጠመ፡፡ እግረ መንገዱን ከልጅነቱ ጀምሮ በፍቅር የተያዘበትን እግር ኳስ ስራዬ ብሎ መጫወት ጀመረ፡፡ ሰፈሩ ዲላ ስቴዲየም አቅራቢያ መገኘቱ በስፖርቱ እንዲገፋበት ምክንያት ሆነው፡፡ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች የመሆን ህልሙን ሰንቆ መንገድ የጀመረው ወጣቱ ነብዩ፥ ለአራት የተለያዩ ክለቦች ቢጫወትም በጉዳት ምክንያት እግር ኳሱንም ለማቆም ተገደደ፡፡ ያም ሆኖ በስፖርቱ ገፍቶ ባይሄድም ህይወት በመራችው የበጎ አድራጎት ተግባር ላይ ተሠማርቶ፥ ግምባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ከራሱ በላይ የደከሙትን በማገዝ ስራ መጠመዱ አልቀረም፡፡ እርግጥ የኑሮ ውጣ ውረዱ ፈታኝ እንደነበረ የሚናገረው ነብዩ፥ ከትምህርቱ ጎን ለጎን እራሱን ለመርዳት ከቀን ስራ ጀምሮ የተለያዩ ሙያዎችን ሲሞክር ነበር፡፡
“ለዛሬው ማንነቴ ትላንትን በተለያዩ የስራና የኑሮ ጫናዎች ውስጥ ማለፍ መቻሌ ረድቶኛል” ይላል፡፡ ወትሮም የህይወት ጥሪው በጎነት በመሆኑ ከልጅነቱ የነበረውን ለሰዎች የመድረስ ፍላጎቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ አጋጣሚ እውን ለማድረግ ሞከረ፡፡ ወቅቱ እንኳን የእለት ጉርሱን ከሰው እጅ ጠብቆ ለሚያድረው ቀርቶ ለብዙዎችም አሳሳቢ የነበረበት በመሆኑ፥ በጊዜው አጋዥ የራቃቸውን የጎዳና ልጆች ማዕድ የማጋራት ሃሳብ ይዞ ብቅ ቢልም ዳሩ ግን ያን ያህል ተቀባይነትና የሚተባበረው ሊያገኝ አልቻለም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ ሳይቆርጥ ከሰፈሩ፣ ከጓደኞቹና ከአካባቢው ማህበረሰብ ምግብና ምግብ ነክ እርዳታዎችን በመለመንና በማስተባበር አቅመ ደካሞችንና የጎዳና ልጆችን ማገዝ መቻሉን ይናገራል፡፡
እርግጥ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ አንዳንዴ እርዳታ ለማስተባበር ስትንቀሳቀስ ረጂዎችን ለማሳመን ብዙ ጥረት ማድረግና እገዛቸውንም በተጨባጭ ተግባር ላይ አውሎ ማሳየት እንደሚያስፈልግ ወጣት ነብዩ ይናገራል። በግል የሚያደርገውን የበጎ ፈቃድ ተግባር አደረጃጀት በመፍጠር “ኢትዮጵዊነት” የተሰኘ ማህበር በመመስረት የድጋፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት ጥረት ማድረጉን ተያያዘው፡፡ “አንዳንድ ጊዜ ኪሴ ባዶ ሆኖ ወይም ሌላውን ለማገዝ ቀርቶ ለራሴም የለኝም ብዬ ተስፋ እቆርጥ ነበር፡፡ ነገር ግን የሚረዳውን የሚያዘጋጀው እግዚአብሔር በመሆኑ እኔ ምክንያት እንጂ ረጂ ባለመሆኔ መንቀሳቀስ ስጀምር ብዙ ድጋፍና ተባባሪ ማግኘቴ ደስታዬን ልዩ ያደርገዋል፡፡
ስላለኝ ብቻ አይደለም ማድረግ የምችለው፤ መጀመሪያ የውስጥ ፈቃድ እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ለእኔ ተፈጥሮዬ ነው” ይላል ወጣቱ፡፡ ህክምና ለማድረግ አቅም ያነሳቸውን ሊያግዙ ከሚችሉት ጋር በማገናኘትና እንዲሁ የገቢ አቅም ለሌላቸው ገቢ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ድጋፍ የሚያደርገው ወጣቱ፥ ሁሉም በያለበት ቢረዳዳ ድህነት ብቻ ሳይሆን ሰላማችን ፍጹም ይሆናል ይላል፡፡
የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ የታመሙትን የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ የተቸገሩትን ማብላትና ከራስ በላይ ለደከሙት መቆም ከምንም በላይ አስደሳች ነገር ነው ይላል ወጣት ነብዩ፡፡ አሁን አሁን እየተለመደ የመጣው የአረጋውያንን ቤት ማደስና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከወቅት ባለፈ ባህል እንዲሆን የተጀመረው ስራ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በዚህም ትልቅ አቅም እየተፈጠረ በመሆኑ መረዳዳትና መተጋገዝ እንደባህል እየጠነከረ መልካም እሴት እንደሚሆን ይናገራል። ቀደም ሲል እሱና ጓዳኞቹን በማስተባበር የአረጋውያን ቤት በማደስና ሌሎች ድጋፎችን ሲያደርግ የነበረበት መንገድ የበለጠ አሁን በተደራጀ መልኩ በመንግስትም ሆነ በሌሎች ተቋማት እየተዘወተረ መምጣቱ እንዳስደሰተው ይገልጻል፡፡
እርሱ በበኩሉ በሚያከናውናቸው በጎ ተግባራት የሕሊና እረፍት እንደሚሰማው የተናገረው ወጣቱ፣ ለአንዲት እናት ያደረገውን መልካም ተግባር ለአብነት ያነሳል፤ እንዲህ ሲል፡- “ከዲላ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ አንዲት መንደር የሚኖሩ ወ/ሮ ታደለች አለማየሁ የሚባሉ የ65 ዓመት እናት አሉ፡፡ 3 ልጆች አሏቸው፡፡ ያገኘኋቸው ዲላ ከተማ መንገድ ላይ ሲለምኑ ነው፡፡ ድህነቱ ብቻ ሳይሆን በአንገታቸው እና በማህጸናቸው ውስጥ ያለው እጢ ለ22 ዓመታት በስቃይ አንከራቷቸዋል፡፡ “ካገኘኋቸው ወዲህ አድራሻ ተለዋወጥን። ከዚያም ወደ ሚኖሩበት መንደር አቅንቼ የተንቀሳቃሽ ምስል ዶክመንተሪ ሰርቼላቸው ፌስቡክ እና ቲክቶክ በመሳሰሉት ማህበራዊ ትስስር ገጾች ዶክመንተሪውን በመልቀቅ በግል አካውንታቸው እርዳታ እንዲሰበሰብ አደረግኩኝ፡፡ “ከዚያም በተሰበሰበው ገንዘብ ሕክምና ተደርጎላቸው ከስቃያቸው መዳን ችለዋል። ቤትም ተሰርቶላቸዋል፡፡ አሁን ደግሞ ለዕለት ገቢ የሚያግዛቸውን የሞተር ብስክሌት ለመግዛት ጥረት እያደረግኩኝ ነው፡፡” “በጎ ስራ ለራስ ነው” የሚለው ወጣት ነብዩ ላበረከተው አስተዋዕጾ የዞኑ አስተዳደር ሆነ ሌሎች ተቋማት የምስጋናና የእውቅና የምስክር ወረቀትና የዋንጫ ሽልማት አበርክተውለታል። ወጣት ነብዩ ባስተላላፈው መልዕክት በዚህ ተግባሩ የብዙሃንን ምርቃትና ጸሎት እያገኘ ከዚህም በላይ የሚያሳድጋትን ቆንጆ ልጅ ከዚሁ ሰናይ ምግባር ማግኘቱን ይናገራል፡፡
“ኑሯችን ከራስ በላይ ሲሆን ታሪክ በራሱ ቆንጆ አድርጎ ይጽፈናል” የሚለው ወጣቱ፥ “መኖራችን ይታይ ዘንድ ከዛሬ አልፈን እንኑር፤ ለማገዝ የራስ ተነሳሽነት እንጂ ሀብትና ቁስ ብቻውን በቂ አይደለም፤ የልብ መሻትና ቅንነት ትልቅ ቦታ አላቸው” ይላል፡፡ ለመርዳት መነሻ ሀሳብ ከራስ በላይ ማሰብ በቂ በመሆኑ፥ ለሀገር ለመትረፍ መጀመሪያ ጎረቤትን ማየት ብቻ ችግራችን ከመንሰራፋቱ በፊት በትንሹ መቅጨት መጀመር ነው። የወጣት ነብዩም የሕይወት ተሞክሮ የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡፡
More Stories
“አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ ሞጋችና ጠያቂ መሆን አለባቸው” – አቶ መሐመድ ሼይቾ ረዲ
የሁለቱ ወንድማማቾች ወግ
በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ መብት ወይስ ግዴታ?