ያመረትናቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጥን ነው – በጌዴኦ ዞን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ማህበራት

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሀገር በቀል ግብዓቶችን በመጠቀም ያመረቷቸውን ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን በጌዴኦ ዞን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ማህበራት ተናገሩ።

በዲላ ከተማ ለአራት ተከታታይ ቀናት በቆየው ባዛር ከዞኑና ከከተማው የተመረጡ ማህበራት ምርቶቻቸውን ለገበያ አቅርበዋል።

ወጣት ቢኒያም ብርሃኑና ወ/ሮ ድንቅነሽ በቀለ በዞኑ ዲላ ዙሪያ ወረዳና በዲላ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ በመግባት የተለያዩ ምርቶችን አምርተው ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በባዛሩ ጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች፣ ብረታ ብረት፣ የእንጨት ሥራ፣ የፈጠራ ሥራዎችንና የመሳሰሉትን ማቅረባቸውን የተናገሩት ወጣት ቢኒያምና ወ/ሮ ድንቅነሽ የመሥሪያ ቦታ፣ የገበያ ትስስርና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ቢፈታ አሁን ካለበት በተሻለ መልኩ በመሥራት ውጤት ለማስመዝገብ አቅሙ እንዳላቸው ገልፀዋል።

በባዛሩ ማር ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ብሩክ ተፈራ የዲላ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ለገበያ የቀረቡ ምርቶች በጥራት የተሻሉ ከመሆናቸውም ባለፈ ዋጋቸውም የኅብረተሰቡን ኪስ የማይጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ የዲላ ዙሪያ ወረዳ VIS የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ግብረ ሰናይ ድርጅት ዋና አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ዝናቡ፤ ድርጅቱ በወረዳው በ27 ሚሊዮን ብር ወጣቶች አገልግሎት የሚያገኝባቸውን ቦታዎች ምቹ ማድረግ፣ ማዕከላትን መደገፍ፣ የኢንተርፕራይዝ አቅም ማሳደግና የሞኒተርንግ ተግባራትን ድጋፍ እየተሳተፈ መሆኑን አስረድተዋል።

ድርጅቱ ከወረዳው አልፎ በዞኑ በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ የገቡ የኢንተርፕራይዝ ማህበራትን የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በመሰጠትና የተለያዩ ቁሶችን በመለገስ ሁለተናዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።

በዞኑ የሚገኙ ኢንተርፕራይዝ ማህበራት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሀገር በቀል አምራቾችን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ ከተለያዩ አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የዞኑ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን አለማየሁ ገልፀዋል።

ለዘርፉ ተግባራት ከ1 መቶ 20 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ምክንያት የሚባክነውን ምንዛሪ በመቀነስ ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ በሀገር በቀል ምርቶች ለመተካት እየተሠራ መሆኑንም አቶ መስፍን ጠቁመዋል።

ከመሥሪያ ቦታ፣ ከገበያ ትስስርና ከፋይናንስ አቅርቦት ማነስ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግም ኃላፊው ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ዘሪሁን ሹፌር – ከፍሰሃገነት ጣቢያችን