ያልተንበረከከው

ያልተንበረከከው

በይበልጣል ጫኔ

“ሰው በተፈጥሮው አካል ጉዳተኛ ሆኖ ሊወለድ ይችላል። በጦርነት አልያም በሌላ ምክንያት እንዲሁ አካል ጉዳት ሊያጋጥም የሚችልበት ዕድል አለ። በትራፊክ አደጋ ወይም በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሰዎች ለአካል ጉዳት ሊዳረጉም ይችላሉ። የእኔ ግን ከእነዚህ ይለያል” ይለናል÷ በዛሬው “ችያለሁ” አምዳችን የህይወት ልምዱን የሚያጋራን÷ መምህር የሺጥላ ተስፋዬ።

የሺጥላ ተስፋዬ የተወለደው÷ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ውስጥ ነው። ሲወለድ ምንም ዓይነት የአካል ጉዳት አልነበረበትም። ተወልዶ ባደገበት ቀዬ አፈር ፈጭቶ፣ ጭቃ አቡክቶ ተጫውቷል። ከዕድሜ ተጋሪዎቹ ጋር በመሆንም በመስኩ ላይ ቦርቋል። አቅሙ በፈቀደለት ልክም÷ ቤተሰቦቹን ለማገዝ ተፋጥኗል።

ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው በሚገኝ “ጦስኝ” በሚባል ትምህርት ቤት ገብቶ ራሱን ከፊደል አስተዋውቋል። እስከ አራተኛ ክፍል ከተማረ በኋላ ነው እንግዲህ÷ የህይወቱን መልክ የቀየረ ክስተት በህይወቱ ላይ የተከሰተው። ባለታሪካችን ጉዳዩን እንዲህ ያስታውሰዋል፦

“ጊዜው ሚያዝያ 25 ቀን 1984 ዓ.ም እሁድ ቀን ነው። በምንኖርበት ቀበሌ ውስጥ ሁለት ሰርጎች ነበሩ። እንዳጋጣሚ የሴቷም የወንዱም ሙሽሮች ቤተሰቦች ዘመዶቻችን ናቸው። እኔ በሰዓቱ ወደ ወንዱ ቤት ሄድኩኝ። የሰርጉ ስርዓት እየተከናወነ÷ ሙሽራው ሙሽሪትን ሊያመጣ ጉልበት ስሞ በሚወጣበት ጊዜ የደስታ መግለጫ ጥይት መተኮስ ተጀመረ። በዚያ አጋጣሚ ለደስታ ይተኮስ የነበረው ጥይት እኔ ላይ ጉዳት አደረሰ። የዓይኔን ብርሃን ያጣሁትም በዚሁ ምክንያት ነው”

ይኼ ዕለት የየሺጥላን ህይወት ሌላ መልክ አስያዘው። ህክምና እንዲያገኝ መጀመሪያ ወደ ደብረ ዘይት ተወሰደ። የሆነው ነገር ከአቅም በላይ ስለነበርም÷ ከደብረ ዘይት በአስቸኳይ ወደ ጥቁር አንበሳ እንዲሄድ ተደረገ። በዚህም ተባለ በዚያ በዶክተሮቹ ጥበብ÷ በሚያዙለት መድኃኒት ኃይል የብላቴናውን ዕይታ መመለስ ሳይቻል ቀረ።

ዓይናማው እና ባሻው ሰዓት ወደፈቀደበት ቦታ ሮጦ መድረስ ይችል የነበረው ትንሹ የሺጥላ÷ በድንገት ዓይነ ስውር ሆነ። ይህ ሁኔታ ለእርሱ ቀላል አልነበረም፦

“በጣም ከባድ ነበረ። ከባድ ያደረገውም ነገር አንደኛ … የገጠመኝ ነገር ድንገት ስለነበር በልጅነቴ የማስባቸው÷ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደሚሆነው ይኼን ነግጄ … ያንን ሰርቼ አንድ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ እያሰብኩ እና እየተማርኩ በነበርኩበት ሰዓት እንዲህ ዓይነት ነገር ሲደርስብኝ ትልቅ ተራራ ተንዶ የወደቀብኝ ያክል ነበር የተሰማኝ። በጣም ደንግጫለሁ። በጣም አዝኛለሁ” ይላል ያንን ጊዜ በማስታወስ።

ከህክምናው በኋላ የዓይኑ ብርሃን ድንገት የሚመለስ እየመሰለውም÷ ሁል ጊዜ ማለዳ እየተነሳ ብርሃን ይታየው እንደሆነ ይሞክራል። በሁኔታው እጅጉን የተፈተኑት ቤተሰቦቹም ቢሆኑ የአቅማቸውን ሁሉ አድርገው ልጃቸውን የልጅነት ብርሃን መመለስ ስላልቻሉ በጣም አዝነው ነበር።

የሺጥላ አደጋው ካጋጠመው በኋላ÷ የመጀመሪያዎቹን ጥቂት ወራት በህክምና አሳለፈ። የመዳን ተስፋ አጥቶ ወደ ትውልድ ቀዬው ከተመለሰ በኋላም÷ የልጅ ነገር ሆኖ ከዕድሜ ተጋሪዎቹ ጋር እንደ ቀድሞው መጫወት ይሞክር ነበር።

በዚህ ሁኔታ ብዙም ሳይቆይ÷ ቤተሰቦቹ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት መኖሩን ስለሰሙ በ1985 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ባኮ ወደሚባል አካባቢ ላኩት። በባኮ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤትም÷ አዲስ የትምህርት ህይወት ጀመረ። በእርግጥም ይኼ ለሱ አዲስ ነገር ነበረ።

“በእስኪቢርቶ ከመፃፍ በብሬል ለመፃፍ ወደመለማመዱ መምጣት÷ ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ነበረ። የምችለውም አይመስለኝም። እያንዳንዱን ነገር ስዳብሰው ተመሳሳይ መስሎ ነበር የሚሰማኝ። በኋላ ግን መምህራኖቻችን በጠጠር የሚመሰረቱ፣ በብረት ቁልፍ የሚመሰረቱ ትላልቅ ሰሌዳዎች እያዘጋጁ አለማመዱን። በኋላም በሂደት ወረቀት ላይ መፃፍ እየተለማመድኩ መጣሁ” ይላል÷ የባኮ ትዝታውን እያስታወሰ።

በዓይን ከማንበብ በእጅ ወደማንበብ ተሸጋገረ። አስቸጋሪውን ሂደት አልፎም እንደገና ፊደል ቆጠረ። ከባድ የመሰለው ነገር ሲቀል÷ ዳግም ማንበብ እና ከዕውቀት ጋር መገናኘት ሲችል ይኼኔ እፎይታ ተሰማው። በባኮ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት እስከ አምስተኛ ክፍል ተማረ።

እዚያ በነበረው ቆይታ ሙዚቃ እንዲጫወቱ ስለሚረዷቸው፣ ሚኒ ሚድያ ውስጥ ይሳተፍ ስለነበር÷ በድራማ እና ስነፅሑፍ ክበባት ውስጥ ድርሻ ስለነበረው እጅግ ደስተኛ ነበር። ነገር ግን ባኮ በተፈጥሮው ሞቃታማ አካባቢ ስለሆነና እሱም በተደጋጋሚ ራሱን ያመው ስለነበር÷ ለተቋሙ አመልክቶ ወደ ወላይታ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ተቀየረ።

“ወላይታ ከመጣሁ በኋላ ስድስተኛ ክፍል ገባሁ። አዳሪ ትምህርት ቤት ስለነበረ ምንም አይነት ችግር አልነበረብኝም። እንደኔው ዓይነ ስውራን ልጆች ስለነበሩ ከነሱ ጋር እወጣለሁ÷ እገባለሁ”

ለሁለት ዓመት በጥሩ ሁኔታ ሲማር ከቆየ በኋላ ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ ድርጅቱ አዲስ ሃሳብ አመጣ። ወጪያቸው ተችሎላቸው ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ ወጥተው ራሳቸውን ችለው እንዲማሩ አደረጋቸው።

ከተከራዩበት ቤት ወደ ትምህርት ቤት በሚመላለሱበት ጊዜም የመልክዓ ምድሩ ምቹ አለመሆን፣ የሞተሮች እና መኪናዎች ያለ ቦታቸው መቆም፣ አንዳንድ ጊዜም ከገጠር የሚመጡ እንጨት የጫኑ አህዮች ግፊያ ቆይታቸውን አስቸጋሪ አድርገውታል። በተለይ ከጥቅምት እስከ ጥር ባሉት ወራት ከፍተኛ ግፊት ያለው ንፋስ ይፈትናቸው ነበር። የዚያኔ የከተማዋ መንገዶች በአስፋልት እና ጌጠና ድንጋይ የተዋቡ ስላልነበሩ በንፋሱ ግፊያ የሚነሳው አዋራ መንገዳቸውን እስከመሳት ያደርሳቸው ነበር።

ይህ ሁሉ ቢሆንም÷ ለአላማ የወጣው የሺጥላ ተስፋዬ በሊጋባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ተማረ። ኋላ ላይ በየወሩ ይከፈላቸው የነበረው ገንዘብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመምጣቱ እና ለችግር በመዳረጉ÷ ወደ መነሻው ተመልሶ ምንጃር ሸንኮራ አረርቲ ከተማ ላይ የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን ቀጠለ።

በእርግጥ ወደ ምንጃር ሲመለስ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም። የመጀመሪያው ችግር ዓይነ ስውር ተማሪ ለመቀበል ትምህርት ቤቱ ፈቃደኛ አልነበረም። ለዚህም ሊያግዘው የሚችል ሰው እና ለሱ የተዘጋጀ መፅሐፍ አለመኖሩን ምክንያት አድርገው ነበር። ትምህርት ቤቱ ተቀብሎት ትምህርት ሲጀምር ደግሞ÷ ከተማው እምብዛም የለማ ባለመሆኑ ራሱን ችሎ ለመንቀሳቀስ ተቸግሮ ነበር። ይኼ ሁሉ ቢሆንም የሺጥላ በጥረቱ የኮሌጅ መግቢያ ውጤት እንዳያመጣ አላገደውም።

የየሺጥላ ቀጣይ የሕይወት ምዕራፍ ወደ ሃዋሳ አመራ። በሃዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ገብቶም ከታሪክ ትምህርት ክፍል በዲፕሎማ ተመረቀ። ዕድሉ ሆነና ወደ ስራው ዓለም ሲገባም÷ በዕጣ ሃዋሳ ሐይቅ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደበ።

የሺጥላ ከማስተማሩ ጎን ለጎን በክረምት መርሃግብር ትምህርቱን ተከታትሎ በዲግሪ ተመርቋል። የትምህርት ዝግጅቱ የተሻለ ሲሆንም÷ ወደ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛወረ። ከመማር የማይቦዝነው ባለታሪካችን ትምህርቱን ቀጥሎ በታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር በማስተርስ ዲግሪ ተመርቋል።

የሺጥላ ተስፋዬ ያለፈበት መንገድ ብዙ ነው። ይኼን ሁሉ መንገድ ያለፈው ያለፈተና አይደለም። ፈተናውን በብርታቱ ማሸነፍ ስለቻለ እንጂ።

“ለትምህርት የሚያስፈልጉን ቁሳቁስ አለመሟላት ከባድ ችግር ነው። አንድ ቦታ ተረጋግቼ መኖር አለመቻሌም የሚያመጣው ችግር አለ። የኛ ጓደኞች ክፍል ውስጥ ከጥቁር ሰሌዳ ሲፅፉ÷ እኛ ደግሞ በኋላ ነው ከእነሱ የምንገለብጠው። የመንገዶች አለመመቸት፣ የመሰረተ ልማቶች አለመሟላት እና መሰል ነገሮችም የየዕለት ህይወታችንን ያከብዱብናል” ብሏል÷ ያለፈውን ትላንት በማሰብ።

መምህር የሺጥላ ተስፋዬ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነው። የትዳር አጋሩ ወዳ እና ፈቅዳ አብራው ብትሆንም÷ ቤተሰቦቿ ሊቀበሉት አልወደዱም ነበር። ይህም ከአካል ጉዳተኝነት ፈተናዎች አንዱ ነው። በሂደት ግን ነገሮች መልካቸውን ለውጠዋል። ጥረቱን፣ የትምህርት እና የስራ ስኬቱን ሲያዩ እንዲም ኑሮውን አሸንፎ መኖሩን ሲረዱ “እንዲህም ይቻላል ለካ” ብለዋል። መምህሩም በጥረቱ እያሸነፈ ዛሬ ላይ ደርሷል።