አስከፊው ወረርሽኝ
በኢያሱ ታዴዎስ
መላው ኢትዮጵያ በሰቆቃ ድምጾች የታመሰበት ያ ጊዜ፡፡ ዜጎች ሕይወታቸው እንደዋዛ አልፏል፡፡ ባል ያለሚስት፣ ሚስት ያለባል ልጆቻቸውን ለማሳደግ ተገደዋል። ሕጻናት ያለወላጆች፣ ያለአሳዳጊዎች ቀርተዋል፡፡ ሞት የአብዛኞቹን በር አንኳክቷልና፡፡
ወቅቱ በኢትዮጵያዊያን ዘመን አቆጣጠር 1990ዎቹ መጀመሪያ ነው። እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አፍሪካ፣ ሻገር ሲልም እንደ ዓለም በአዲስ ወረርሽኝነት ከተፍ ያለው የኤች.አይ.ቪ ኤድስ በሽታ፣ አስከፊነቱ አይሎ የበርካቶችን ሕይወት ቀጠፈ፡፡
ክስተቱ እንግዳ ነበር፡፡ ሕብረተሰቡ በወረርሽኙ ላይ በቂ ግንዛቤ ስላልነበረው ውድ ዋጋ አስከፍሏል፡፡ እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ፕሮግራም መረጃ፣ በ1991 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ ደረጃ ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች በቫይረሱ ተጠቅተው ነበር።
ይህ አሃዝ ደግሞ ኢትዮጵያን በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁት ደቡብ አፍሪካ እና ሕንድ በመቀጠል በዓለማችን ሶስተኛዋ ተጠቂ ሀገር አድርጓታል፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም። ኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት የ280 ሺህ ዜጎቿን ሕይወት አጣች፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኤች.አይቪ ኤድስ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ደረጃ እንደተከሰተ የታወቀው ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ከአንድ ወይም ሁለት ዓመታት በኋላ በ1976 ዓ.ም ነው፡፡
ቫይረሱም በተስፋፋበት ወቅት በአመዛኙ ተጠቂዎች የነበሩት ከአንድ በላይ የወሲብ ጓደኛ የሚይዙ ሰዎች ሲሆኑ፣ ከእናት ወደ ልጅ መተላለፊያ መንገድ ተጎጂ የሆኑ ሕጻናትም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 39 የሆኑ ወጣቶች በአብዛኛው ተጎጂዎች ሲሆኑ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ልቅ በሆነ የግብረስጋ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተንሰራፋው ቫይረሱ፣ በሀገሪቱ በተከሰተበት በ1970ዎቹ አጋማሽና መጨረሻ የመንሰራፋት ምጣኔው አዝጋሚ ቢሆንም፣ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቹ ግን በአስደንጋጭ ሁናቴ ንሯል፡፡
የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በ1985 ዓ.ም ከ15 እስከ 49 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 3 ነጥብ 6 በመቶ የነበረው፣ በ1991 ዓ.ም ወደ 10 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል፡፡
ሰዎች ለስራ እና ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ በየወቅቱ በተለይም ወደ ከተሞች አካባቢ የሚያደርጉት ፍልሰት ብዙ የወሲብ አጋር እንዲኖራቸው ማድረጉ ወረርሽኙ በአፋጣኝ ለመዛመቱ በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
ሰዎች በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከቦታቸው መፈናቀላቸው፣ በአፍላ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙና በተቀረው ሕዝብ ዘንድ በልቅ የግብረስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ የአባላዘር በሽታዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ፣ በአፍላ ወጣቶች ወሲባዊ ድርጊቶች መንሰራፋታቸው እና በአንድ ስፍራ የከተሙትን ወታደሮች ጨምሮ የስራ አጦች ቁጥር በተጋነነ መልኩ ማሻቀቡ ሌሎች ለወረርሽኙ መዛመት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጓዳኝ ለቫይረሱ ስርጭት መንሰራፋት ሰፊ ጥናት ተደርጎበት ከውጤት የተደረሰበት በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች ጉዳይ ነው፡፡ በ1980 ዓ.ም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በማህበረሰቡ መካከል የሚገኙ 6 ሺህ 234 በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ሲረጋገጥ፣ በወቅቱ የመያዝ ምጣኔው 18 ነጥብ 3 በመቶ ነበር፡፡
ምጣኔው ከአንድ ዓመት በኋላ (በ1981 ዓ.ም) በአስደንጋጭ ሁኔታ ወደ 29 ነጥብ 2 በመቶ አድጓል፡፡ ከዚህም መካከል 20 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተጠቂዎች ከአዲስ አበባ እስከ አሰብ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ እና ባህርዳር ባሉ ከባድ ተሽከርካሪዎች በሚጓጓዙበት ስፍራ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡
ይህም ማለት በአመዛኙ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች እና የከባድ ተሸከርካሪ አሽከርካሪዎች በቫይረሱ ይጠቃሉ፡፡ በተጨማሪም ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩ ወታደሮች፣ አፍላ ወጣቶችና መካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎችም የቫይረሱ ሰለባዎች ናቸው፡፡
ጤና ሚኒስቴር በ1991 ዓ.ም ባወጣው መረጃ መሰረት ደግሞ፣ አዲስ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው እናቶች የሚያስተላልፉባቸው ሕጻናት ናቸው።
ታዲያ በእነዚህ ጊዜያት ሀገሪቱ መልከ ብዙ ስንክሳሮችን ለማስተናገድ ተገዳለች። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው ከ1972 ዓ.ም እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት በየዓመቱ የ2 ነጥብ 7 በመቶ ዕድገት ቢያሳይም፣ የዜጎች የዕድሜ ጣሪያ ከ42 እስከ 43 ዓመት ድረስ ነበር፡፡ ይህም የሆነው በወረርሽኙ ምክንያት ሲሆን፣ በወቅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ አራተኛዋ ዝቅተኛ የዜጎች የዕድሜ ጣሪያ ያላት ሀገር አድርጓት ነበር፡፡ ወረርሽኙ በአጠቃላይ እስከ 7 ዓመት የዕድሜ ጣሪያ እንደቀነሰም ይነገራል፡፡
በምጣኔ ሃብት ረገድም ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ሕዝብ የምግብ ዋስትናው አልተረጋገጠም ነበር፡፡ ምርታማነት በመቀነሱና ድርቅ በመስፋፋቱ ምክንያትም በየዓመቱ ከ10 ሺህ እስከ 150 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡
በጤናው ዘርፍም የጤና ባለሙያዎችና አማካሪዎች እጥረት፣ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ያለማግኘት እና ደካማ ቁጥጥር መኖር የተስተዋሉ ችግሮች ነበሩ፡፡ የሰዎች ቁጥር ከጤና ተቋማት ቁጥር በእጅጉ መብለጡም ሌላ ሳንካ ነበር፡፡
ከእነዚህ ጊዜያት በኋላ በሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ ረድኤት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ወረርሽኙን መቀነስ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ጀመረ፡፡ ለዚህም ደግሞ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ነው፡፡
ከሶስቱ የመ – ሕጎች ጀምሮ (መታቀብ፣ መወሰን እና መጠቀም) አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እና እናቶች ወደ ልጆቻቸው እንዳያስተላልፉ በቂ ዕውቀት የሚያስጨብጡ የግንዛቤ ስራዎች በስፋት በመሰራታቸው ወረርሽኙን የመቀነስ ተግባሩ ቀስ በቀስ ውጤታማ እየሆነ መጣ።
ከባለፈው ዓመት በፊት በነበሩት አስራ አምስት ዓመታት በተሰራ ስራም አስቀድሞ በአስከፊነቱ ይጠራ የነበረው ወረርሽኙ፣ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር 59 በመቶ፣ እንዲሁም የሞት ምጣኔው 52 በመቶ ሊቀንስ ችሏል፡፡
ጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማህበራት፣ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በሰሩት ስራ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭትን በአሁኑ ወቅት ወደ 0 ነጥብ 91 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተወሰኑ መዘናጋቶች በህብረተሰቡ ዘንድ መስተዋላቸው ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 610 ሺህ 350 በላይ በደማቸው ውስጥ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ያለባቸው ወገኖች እንደሚገኙና 8 ሺህ 257 ሰዎች በየዓመቱ እንደ አዲስ እንደሚያዙ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህም መካከል 11 ሺህ 322 ዜጎች በበሽታው ለህልፈት እንደሚዳረጉ ተገምቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ጨምሮ እንደገለጸውም በ2030 ኤች.አይ.ቪ ኤድስ የህብረተሰቡ ችግር ወደ ማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ እና ከበሽታው ነጻ ትውልድ ለመፍጠር የተጣለውን ዓለም አቀፍ ግብ ለማሳካት እንደሚሰራ አረጋግጧል፡፡
36ኛው የዓለም ኤድስ ቀን ህዳር 21/2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበሩ ይታወሳል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው