ተስፋ የፈነጠቀው ምክክር
በፈረኦን ደበበ
አዎን ተስፋው ተፈጥሯል፡፡ የዓለም ህዝብ ወደ እልቂት ይገባ ይሁን የሚለውን ሥጋት የሚቀርፍ ውይይት በአካባቢው እየተካሄደ ስለሆነ፡፡ በኃያላን መካከል ነግሦ የቆየው ሽኩቻና ጥላቻ ሙሉ በሙሉ ባይወገድም ምሥራቅ ኤሲያን ሲያነታሪክ የቆየው ውዝግብ በሠላም እንዲፈታ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የአካባቢው ሀገራት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መነሳሳታቸው ለዓለምም ተስፋ ፈንጥቋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ኃያላን ያለ የለሌ ኃይላቸውን አሰባስበው ወደ ፍጥጫ የገቡት፡፡ ሰሞኑን የተሰማው ዜና ግን በአንዱ የዓለም ክፍል የተስፋ ብርሃን አሳይቷል፡፡ ይህ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከተስፋፋም ውዝግብ ላንገሸገሸው የዓለም ህዝብ የተስፋ ብሥራት እንደሚሆን እምነት ተጥሎበታል፡፡ ቦታው የምሥራቅ ኤሲያ ነው፡፡ ሀገራት ደግሞ ቻይና፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ (የኮሪያ ሪብሊክ)፡፡ እነዚህ በባላንጣነት እርስ በርስ የሚፈላለጉ ሀገራት ነበሩ፡፡
መሪዎቻቸው ግን ሰሞኑን ባልተጠበቀ ሁኔታ በአንድ ቦታ ላይ ተገናኝተዋል፡፡ ቡሳን በተባለችው የደቡብ ኮሪያ ወደብ ከተማ፡፡ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወንግ ይ ጨምሮ የሦስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሰበሰቡ፡፡ ትብብሩም በመሠረታዊ ምክንያት፣ ጎላ ብሎ በሚታይ የህዝብ ፍላጎት፣ በትልቅ አቅምና በሠፊ እይታ ላይ መመሥረቱን አስታውቀዋል፡፡ 10ኛ ነው ባሉት የጋራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ። በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተጽዕኖ ፈጣሪነት የተካሄደ በሚመስለው በዚህ መድረክ ላይ ሀገራት እንዴት ባለ ሁኔታ እርስ በርስ እንደሚገናኙና በምን በምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚወያዩ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን የተባለው የቻይ ዜና ወኪል ገልጿል፡፡ በመድረኩ ላይ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሳሰቡት ከሆነ ሚናን በማሳደግና አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ሦስቱ ሀገራት ከፍተኛ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
በምዕተ ዓመቱ ያልታየ ፈጣን ለውጥ በማምጣትና ደካማ የሆነውን የምጣኔ ሀብት ዕድገት በመቀየር፡፡ ሚኒስትሩ የቻይናን አቋም በገለጹበት ጊዜም ለጎረቤቶቿ ቅድሚያ የምትሰጠውን ፖሊሲ እንደምታጠናክርና በወንድማማችነትና በጋራ ትብብር ከሁለቱ ሀገራት ጋር እንደምትሠራ አስታውቀዋል፡፡ ይህ መልካም ግንኙነት በሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ጤናማ፣ የማይናወጥና ቀጣይነት ያለው እንደሚያደርግም አስረድተዋል፡፡
በአዲስ የሚመሠረተው ትብብር ለአካባቢው፣ ለዓለም ሠላምና ብልጽግና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የተናገሩት ዋንግ ይ ይህን ለማሳካትም አንዱ የሌላኛውን የዕድገት ዘይቤ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችና ትኩረት የሚሰጥባቸው ጉዳዮችን በአግባቡ ማክበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የእርስ በርስ ግንኙነቱን አስተማማኝ የማድረግ አስፈላጊነትንም በመጠቆም፡፡ እነዚህ ጉዳዮችን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም ለሁለንተናዊ ግንኙነትና ለዘላቂ ሦስትዮሽ ትብብር እንደሚረዳ የገለጹት ዋንግ ይ ስለ ነጻ ንግድ ሲያወሱም ሦስቱ ሀገራት ቻይና-ጃፓን-ኮሪያ ሪፐብሊክ በሚል በአዲስ መልክ እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሂደቱ ለአካባቢያዊ ምጣኔ ሀብታዊ ውህደትም እንደሚረዳ በማስታወቅ፡፡ እንደ መረጃ ምንጫችን ከሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሌላው ነጥብ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚደረገው ትብብር ሲሆን ይህም ከፍተኛ መረጃዎችና ጥቅሎችን እንዲሁም ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ያጠቃልላል ብለዋል፡፡ ሦስቱ ሀገራት የኢንዱስትሪ ቀጣይነት ለማረጋገጥና የአቅርቦት ሠንሠለቶችን ለማጠንከር እንደሚረዳቸው በመጠቆም፡፡ በቅርቡ የተካሄደውን የኤሲያ ፓስፊክ ትብብር ጉባኤን ተከትሎ የተዘጋጀው የሦስቱ ሀገራት የውይይት መድረክ ትኩረት ያደረገው ሌላው ነጥብ የህዝብ- ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከርን ሲሆን ይህ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ለመደገፍ፣ ለአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች አንገብጋቢ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
የጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም የእርስ በርስ ተግባቦትና ትብብርን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በተለያዩ ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት መነሳሳታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ ሚኒስትሮቹ ገልጸዋል እንደተባለው ሦስቱ ሀገራት መሠረታዊና መጪው ዘመንን በሚያሳምሩ ጉዳዮች ላይ የሚተባበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የምጣኔ ሀብት፣ ንግድ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የሥራ ፈጠራ፣ ባህል፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ዘርፎች ይገኙታል፡፡
የኮሪያ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርክ ጂን እና የጃፓኑ አቻቸው ዮኮ ካምካዋ እንዳስታወቁት ከሆነ በሦስቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው የትብብር ስምምነት ከሰሜን ምሥራቅ ኤሲያ በተጨማሪ ለዓለምና አካባቢያዊ ሠላምና ብልጽግና አስተዋጽኦ የሚኖረው መሆኑም ነው፡፡ ክፍፍልና የእርስ በርስ ጥርጣሬ በተመለከተም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሀገራቱ ርዕዮተ[1]ዓለምን መነሻ አድርገው ከሚነሱ ክፍፍሎችና ልዩነቶች ይታቀባሉ፡፡ ከዚህ አንጻር ”እኛ እንደ ሠላም አምጪ በመሆን አካባቢያዊ ሠላምና ጸጥታ ማረጋገጥ ይገባል ካሉ በኋላ አብሮነትን ከመተግበር አንጻርም የጋራ፣ ሁሉ አቀፍ፣ ትብብራዊና ዘላቂ ሠላምን ማምጣት አለብን“ ብለዋል፡፡
በሠላማዊ መንገድ የሚደረጉ ውይይቶችና ምክክሮችን በማጠናከር ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ እናስወግዳቸው ማለታቸውንም ነው ሲ.ጂ.ቲ.ኤን. የዘገበው፡፡ ሀገራቱ ውጥረቶች በሚከሰቱበት ጊዜ በማርገብ ረገድ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ያደረጉት የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ስለነገሰው ውጥረትም እንዲህ በማለት ተናግረዋል “ማንንም የማይጠቅም” መሆኑን በማውሳት፡፡ ትልቁ ጉዳይ ችግሩን ማብረድ እንደሆነ አስታውቀው በዚህም ውይይትን ለማስጀመር አመቺ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም ሀገራት ትርጉም ያለው አቋም መያዝ እንዳለባቸው በማሳሰብ፡፡
ከላይ የተገለጹ ሀሳቦችን ከወሰድን በውጥረት ታጅቦ ለቆየው ዓለም አዲስ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ መነሻውን በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ያደረገው የወቅቱ ፍጥጫ በማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች ታጅቧል፡፡ አፍሪካን አካልሎ ወደ ሩቅ ምሥራቅ ካዘገመ በኋላ በቅርቡ በእሥራኤልና በፍልስጤም መካከል በተካሄደው ግጭት እንደገና አገርሽቷል፡፡ በአንድ አካባቢ የተቀጣጠለው ቀውስ ሳይበርድ ወላፈኑ ወደ ሌላው አካባቢ እየተዛመተና ህዝብን ለሥጋት ሲዳርግ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል በተለይ ቻይናና ሩሲያ በአንድ በኩል እንዲሁም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና አውስትራሊያ ሆነው በደቡብ ቻይና ባህር የፈጠሩት ግንባር በቻይናና ታይዋን መካከል የተካረረ ሁኔታ ፈጥሮ ነበር፡፡
በሩሲያና ዩክሬን መካከል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ባልተቋጨበትና በታይዋን ምክንያት በቻይናና አሜሪካ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫም ባልሻረበት በአሁኑ ሰዓት በቻይና፣ ጃፓንና በደቡብ ኮሪያ መካከል የትብብር ማዕቀፍ መቀረጹ ትልቅ ተስፋ ይፈጥራል፡፡ ዓለም ከኒውክሌር ሥጋት ወጥቶ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞርም ዕድል ይፈጥራል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው