አቶ ሀይለሚካኤል ሌንጮ
በገነት ደጉ
የዛሬው ባለታሪካችን የወላይታ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በመንግስት ስራ ለ29 ዓመታት ያህል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው አገልግለዋል፡፡
ባለታሪካችን አቶ ሀይለሚካኤል ሌንጮ ይባላሉ፡፡ ትውልድ እና እድገታቸው በወላይታ ዞን በቀድሞው ዳሞት ወይዴ፥ በአሁኑ ዱጉና ፋንጎ፥ ወረዳ ልዩ ስሙ ዋራዛ ላሾ በሚባለው ቀበሌ ነው፡፡ በ1940 ዎቹ ይችን ዓለም መቀላቀላቸውን ነው በነበረን ቆይታ ያጫወቱን፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን፥ በፊደል ገበታ በቄስ ትምህርት ቤት እና 1ኛ ክፍልን ደግሞ እዛው ዋረሻላዞ ተከታትለው ታላቅ ወንድማቸው ለማስተማር ወደ ይርጋለም እንደወሰዷቸው ነው የሚናገሩት፡፡
በይርጋለም ከተማ ከ2ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ድረስ ራስ ደስታ ዳምጤ ትምህርት ቤት ተምረው ትምህርታቸውን በ1962 ዓ.ም ማጠናቀቃቸውን ነው የገለፁልን፡፡
የትምህርት ውጤታቸው በወቅቱ ለዲፕሎማ የሚያበቃ በመሆኑ ወደ ሀዋሳ በመምጣት በሰራተኛ እና ማህበራዊ ሚኒስቴር የእድገት ሰራተኞች ማሰልጠኛ በሚባለው ትምህርት ቤት በ1963 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ሰልጥነው መመረቃቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
እንደማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ በመስሪያ ቤቱ ምደባ አግኝተው ወደ ቀድሞው ኢሉባቡር ክፍለ ሀገር ሶሮና ጋባ አውራጃ ብሎ ሎጳ ወረዳ ሄደዋል፡፡ የመንግስት ስራ አሀዱ ብለው ሲጀምሩም በአደረጃጀት ኃላፊነት ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ማገልገላቸውን ነው የሚያስታውሱት፡፡
ከሶስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በገዛ ፍቃዳቸው ዝውውር በመጠየቅ ወደ ደብረብርሃን ገቡ፡፡ ከስድስት ወር ቆይታ በኋላ በ1967 ዓ.ም የገጠር መሬት አዋጅ ሲታወጅ ለሶስት ወራት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ገቡ፡፡ ከዚያም በወቅቱ በነበረው የመሬት ይዞታ ሚኒስቴር ወደ አርባምንጭ በስራ አስኪያጅነት መድቧቸው ወደ እዛው መሄዳቸውን ነው ያጫወቱን፡፡
በ1968 ዓ.ም የጋርዱላ አውራጃ ፥ የመሬት ይዞታ ስራ አስኪያጅ በመሆን ፥ ለአራት ተከታታይ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ የገጠር መሬት አዋጅ ይዞታ ሲያስፈጽሙ ቆይተው በ1971 በገዛ ፈቃዳቸው ስራ ለቀው ወላይታ እርሻ ልማት ህብረት ስራ አደራጅ በመሆን እና ሲቀጥል ደግሞ ገበያና ልማት ኦፊሰር በመሆን እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ ማገልገላቸውን ነው ያስረዱን፡፡
በወቅቱም የወላይታ እርሻ ልማት ሲበተን የአጠቃላይ ሰራተኛ ስም ወደ ግብርና ሚኒስቴር ተላልፎ ስለነበር እንደ ገና የሰራተኞች ድልደላ ተደርጎ በ1974 ዓ.ም ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ደብረማርቆስ አውራጃ ምደባ አግኝተው መሄዳቸውን ነው የገለፁት፡፡
በደብረማርቆስ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ያህል በአውራጃው የህብረት ስራ ኤክስፐርት በመሆን ማገልገላቸውን ያጫወቱን አቶ ሀይለሚካኤል በኋላም ወደ ሀዋሳ ግብርና ቀጠና ምደባ አግኝተው በ1977 ዓ.ም ወደ ሀዋሳ መምጣታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
በዚህም የደቡብ ግብርና ቀጠና ህብረት ስራ ኤክስፐርት በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው የደቡብ ቀጣና መፍረሱን የሚናገሩት አቶ ሀይለሚካኤል በ1978 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ወደ ወላይታ ሶዶ አውራጃ ግብርና ተመልሰው የህብረት ስራ ቡድን መሪ እና ኤክስፐርት በመሆን ለ13 ዓመታት አገልግለዋል፡፡
በ1990ዎቹ አካባቢ በወላይታ ወጋጎዳ ( ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እና ዳውሮ) ውህደት ወቅት ከህዝብ ጋር ተቃውሞ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከታቸውን የገለፁት አቶ ሀይለሚካኤል በዚህ የተነሳም ከአካባቢው እንዲነሱ ተደረገ፡፡ ከዚያም በጎፋ አውራጃ መለኮዛ ወደሚባልበት አካባቢ ተመድበው ለቤተሰባቸው እና ለራሳቸውም አካባቢው ስላልተመቻቸው በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን ለቀው ወደ ወላይታ መመለሳቸውን ነው ያጫወቱን፡፡
በ1992 ዓ.ም ሁሉም ሰው ወደ ቦታው ይመለስ ተብሎ መመሪያ ሲተላለፍ በቦታቸው ሰው መመደቡን የሚናገሩት አቶ ሀይለሚካኤል የሀኪም ማስረጃ አቅርበው ህጋዊ አይደለህም ከስድስት ወር በላይ ቆይተሀል ተብለው ያለፈቃዳቸው ወደ ሁምቦ ወረዳ አደራጅ ሆነው መመደባቸውን ነው የገለፁት፡፡
ሁምቦ ወረዳ ላይ ህብረት ስራ አደራጅ በመሆን ለስድስት ዓመታት ከሰሩ በኋላ በ2000 ዓ.ም በጡረታ መሰናበታቸውን ነው ባለታሪካችን ያጫወቱን፡፡
ህይወት ትቀጥላለች፤ ጡረታ ወጥቻለሁ ብዬም አልቦዘንኩም የሚሉት አቶ ሀይለሚካኤል በጡረታ ከተገተገለሉ 16ኛ ዓመታቸውን አስቆጥረዋል፡፡ ባለታሪካችን ባለትዳር እና የሁለት ወንድ እና አራት ሴት ልጆች አባት ናቸው፡፡
ባለታሪካችን እንደሚሉት ዛሬ ላይ ሁሉም ልጆቻቸው እራሳቸውን እንደቻሉ እና ለወግ ማዕረግ እንደበቁላቸው አስታውሰው የልጅ ልጆችም ማፍራታቸውን ነው የገለፁት፡፡
አንዱ ልጃቸው አዲስ አበባ ላይ ሁለተኛ ድግሪውን ሰርቶ በመምህርነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ተከታዩ ወንድ ልጃቸውም በኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል በድግሪ ተመርቆ አዲስ አበባ ላይ እየሰራ ሲሆን አንደኛዋ ልጃቸው ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመርቃ በአሁኑ ሰዓት ቤተሰቧን ይዛ ኑሮዋን አሜሪካ እንዳደረገች ነው ያጫወቱን፡፡
ቀሪዎች ባለትዳር እና የልጆች እናት በመሆን በንግዱ ስራ እንደሚተዳደሩ አጫውተው ሁሉም ልጆች እንደሚያግዟቸው ነው የገለፁት፡፡
ጡረታ ከወጡ በኋላ በግለሰብ መድሃኒት መሸጫ ውስጥ እየሰሩ ሲሆን ጎን ለጎን ማንኛውንም የኮሚሽን ስራዎችን እንደሚሰሩ ነው ያጫወቱን፡፡
ባሳለፉት በርካታ ዓመታት በማህበራዊ ህይወታቸው በሶዶ ዙሪያ ወረዳ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበር ለመንግስት ሰራተኞች እንዳቋቋሙ የሚናገሩት አቶ ሀይለሚካኤል በሁምቦ ወረዳም በተመሳሳይ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበር ማቋቋማቸውን ነው የጠቆሙት፡፡
እርሳቸው ጡረታ ቢወጡም እንኳን እስካሁን ድረስ የብድርና ቁጠባ ማህበሩ የበለጠ ተደራጅቶ አገልግሎትን እየሰጠ በመሆኑ የመንግስት ሰራተኞች እያመሰገኗቸው እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
ሶዶ ከተማ ላይ የእድር ሰብሳቢ እና የሀገር ሽማግሌ በመሆን የተጣሉትን በማስታረቅ እና እድሩ ጥሩ ደረጃ እንዲደርስ እስካሁን ከመሰል አባቶች ጋር የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ጥሩ ተግባቦት እንዳላቸውና ለታመሙት እና ለተቸገሩት ፈጥነው ደራሽ በመሆን ለጉልበታቸው ሳይሰስቱ የሚችሉትን ሁሉ እያበረከቱ መሆናቸውን በነበረን ቆይታ አጫውተውናል፡፡
ጡረታ ከወጡ በኋላ ብዙ አባቶች እና እናቶች ስራ የለም ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ከጡረታ በኋላ በርካታ ስራዎች አሉ፡፡ በተለይም ከህብረተሰቡ ጋር ያለው ትስስር ይበልጥ የሚጠናከረው ከጡረታ በኋላ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡
የጡረታ ዳረጎት 3ሺ 500 ብር እንደሚደርሳቸው የተናገሩት አቶ ሀይለሚካኤል መኖሪያ ቤታቸው ቅጥር ጊቢ ውስጥ አራት ክፍል የሚከራይ ቤት ሰርተው በወር ከ7ሺ ብር በላይ ገቢ እንደሚገኙም ነው የሚናገሩት፡፡ ይህም ለእኔ እና ለባለቤቴ በቂ ነው ይላሉ፡፡
“ልጆቼም ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ይረዱኛል፡፡ በተለይም ውጪ ሀገር ያለችው ልጃችን በአግባቡ ትረዳናለች፡፡ ፈጣሪ ይመስገን ከባለቤቴ ጋር ጥሩ ኑሮ እየኖርን ነው፡፡
“ጡረታ ለወጡ መሰል ጓደኞቼ የምመክረው ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር እኔ ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረኝ እና ለህዝቡ ጊዜ እንድሰጥ ረድቶኛል፡፡ ይኸውም አቅሜ የፈቀደውን ያህል ደግሞ አቅመ ደካሞችን እየረዳሁ በመሆኔ ነው፡፡ በዚህም እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሰዎችን እንደመርዳት የሚያስደስተኝ ነገር የለም፡፡”
“ከጠንካራ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች” የሚለው እሳቤ ባለቤቴን ይገልፃታል። ባለቤቴ ዛሬ እዚህ ለመድረሴ ስኬቴ ናት። ሁሉ ነገሬም ናት ሲሉም ባለቤታቸውን ሲያሞካሹም ተደምጠዋል፡፡ “የሚቆጨኝ ብዙ ቦታዎች ተዛዙሬ በመስራቴ ጊዜ ባለማግኘት የትምህርት ደረጃዬን አለማሻሻሌ ነው፡፡ የቀጣይ ጊዜ እቅዴ ከልጆቼ ጋር ተመካክሬ መኖሪያ ቤት / ፎቅ/ ለመስራ እና ልጆቼ በየሀገሩ ተበታትነው ያሉትን አንድ ቦታ ሰብሰብ ለማድረግ ሃሳብ አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ስራ የሌላቸውን የራሳቸው የሆነ ነገር ከፍቼ መስጠት እፈልጋለሁ በማለት እቅዳቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ጡረታ የወጣችሁ አባቶች እና እናቶች ከእኚ ባለታሪካችን የህይወት ልምድ እንደምትጋሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡
More Stories
“ሳንቲም ሲጥሉልኝ አመስግኜ ነው የምመልሰው” – ወጣት ማህቶት በለጠ
“ጥበብ ነገሮችን በተለየ መንገድ ማየት መቻል ነው” – ተወዛዋዥ ተስፋ ጽዮን ንጉሴ
ትኩረት ሊሰጠው ይገባል!