ከመከላከል ባለፈ የህክምና ዘርፉን ለማሻሻል በጤና አገልግሎት ተቋማት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 25/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከመከላከል ባለፈ የህክምና ዘርፉን ለማሻሻል የጤና አገልግሎት ተቋማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ::
በክልሉ ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም መድረክ በሆሳዕና ከተማ አካሂዷል::
በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ም/ልና የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ደርጌ፥ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ሆስፒታሎች ለህብረተሰቡ ጥራት ያለውን አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረምና የተሻለውን ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን አመልክተዋል::
የህክምና ቁሳቁስ በወቅቱ ለተቋማት ተደራሽ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሆነ ጠቁመው፥ ጥራትና ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገ ስራ በቀጣይ በአጽንኦት እንደሚሰራ አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል::
በሆስፒታሎች የሚከሰቱ የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ግብአት በሚቀርብበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ ስለመሆኑም የቢሮ ም/ኃላፊ አክለዋል::
በሁሉም ክልሉ አካባቢዎች ያለውን ወጥ ያልሆነውን የጤና መድህን አገልግሎት ውስንነቶችን ለመፍታትና የታካሚ ህብረተሰብ እንግልት ለማስቀረት እንደሚሰራም አመላክተዋል::
በሆስፒታሎች ከወረቀት ነጻ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ ም/ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ጠቁመዋል::
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤና አገልግሎቶች ዳይርክቶሬት ዳይርክተር አቶ ቢኒያም ሽፈራው በክልሉ ካሉ ሆስፒታሎች በአገልግሎት አሰጣጥ ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውን የወራቤ እና የቡታጅራ ሆስፒታሎችን ጥሩ ተሞክሮ ለሌሎች ሆስፒታሎች ለማስፋፋት ውይይቱ አቅም እንደሚፈጠር ገልጸዋል::
የጤና ባለሙያዎች በተላያዩ ቦታዎች ችግሮችን ቢኖሩም አገልግሎት ለሚፈልጉ ተገልጋዮች ተገቢ አገልግሎት እንዲሰጡ ጠይቀዋል::
አምቡላንስን ከታለመለት ዓለማ ውጪ የሚጠቀሙ የመንግስት አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አቶ ቢኒያም አስገንዝበዋል::
በዉይይቱ የተገኙ የወራቤ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አብዲ ዋነጎ በሆስፒታሉ የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችን በማዘመን ተመራጭ ሆስፒታል ለመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል::
ከመድሀኒት አቅርቦት ጋር በሆስፒታሉ ችግሮች እንዳይከሰቱ መድሃኒት በበቂ ሁኔታ መኖሩን ገልፀው፥ በሆስፒታሉ ከ80 በመቶ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆኑም ዶክተር አብዲ አክለዋል::
ሌላኛው የሀላባ ዞን የበሻኖ የመጀመሪያ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልመን ግርሚሶ በበኩላቸው ውይይቱ ሆስፒታሎች ያሉባቸውን ደረጃ ለማየት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን ለማሻሻል ጠቃሚ እንደነበር ገልጸዋል::
የታካሚዎችን እንግልት ለማስቀረት እና የመረጃ አያያዝ ስራዓትን ለማዘመን በሆስፒታሉ ከወረቀት ነጻ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አክለዋል ::
ዘጋቢ፡ በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ