ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከ8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ለጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ

ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከ8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ለጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከ8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ለጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ።

ድርጅቱ ከዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ተቋማት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው ወጪያቸው የተሸፈነ እንደሆነም ተመላክቷል።

የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት በዓይን ህክምና እና በሌሎች የጤና ልማት ስራዎች በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች የማይተካ ሚናውን በመወጣት የተቋቋመበትን ኃላፊነት ሲወጣ መቆየቱን አመልክቷል።

የዚህ ድጋፍ አካል የሆነውን ከ8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ወጪ በጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል እጥረት የሚታይባቸው የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ታጋይ ሳህሉ በርክክቡ ወቅት እንደገለፁት፥ በድጋፍ የተገኙት የህክምና ቁሳቁሶች በተለይ ትኩረት የተነፈጋቸው ሀሩራማ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከልና ለመግታት ለሚደረገው ርብርብ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

አክለውም በሆስፒታሉ ተኝቶ ለሚታከሙት በሚሰጠው አገልግሎት የሚስተዋለውን ችግር በእጅጉ ይቀርፋልም ብለዋል።

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በድጋፍ ሥነ ሥረዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የአሪና ደቡብ ኦሞ ዞንን ጨምሮ ከአጎራባች ዞኖች የሚመጡ ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ማህበረሰብ ድጋፍ እየሰጠ ያለ ቢሆንም የተቋሙ የቁሳቁስ ችግር አገልግሎቱን የተሟላ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።

የኦርቢስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የአሁኑን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በሁለቱ ዞኖች የመንግስት ህክምና አገልግሎት ክፍተትን በመሙላት የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ ላበረከተው አስተዋፆ ምስጋና አቅርበው በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንድቀጥል ጠይቀዋል።

የኦርቢስ ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ስዮም እንደገለፁት፥ ድጋፍ የተደረጉት ቁሳቁሶች በተለይ ትኩረት የተነፈጋቸው ግን በማህበረሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያሉ ሀሩራማ በሽታዎችን ስርጭት ለመከላከልና የሆስፒታሉን የቁሳቁስ ችግር በመቅረፍ የተሟላ ህክምና ለመስጠት ያለመ ነው ብለዋል።

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሥራ ኃላፊዎችና የኦርብስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያና የኢንድ ፈንድ ተወካዮች የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታልን የጎበኙ ሲሆን የሆስፒታሉ ስራ አስከያጅ አቶ ታጋይ ሳህሉ የሆስፒታሉን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ለእንግዶቹ ገለፃ አድርገዋል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን