የጂንካ መምህራን ማህበር የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር የአባላት ጥቅም በማስጠበቅ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲሰፍን ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታወቀ

የጂንካ መምህራን ማህበር የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር የአባላት ጥቅም በማስጠበቅ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲሰፍን ጠንክሮ እንደሚሠራ አስታወቀ

ማህበሩ 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በጂንካ ከተማ አባላት በተገኙበት አካሂዷል።

በማህበሩ በመታቀፋቸው የቁጠባ ባህላቸውን ለማሰደግና ከማህበሩ ብድር በማግኘት ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅምን ለመፍጠር ትልቅ ጥቅም ማግኘታቸውን የማህበሩ አባላት ይገልፃሉ።

ወደፊት በማህበሩ ተጨማሪ ዕጣዎችን በመግዛት የተሻለ ቁጠባ ለማድረግና ማህበሩ ወደ አክሲዮን ደረጃ ከፍ በሚልበት ዙሪያ ጠንክረው እንደሚሠሩም አባላቱ ገልፀዋል።

የጂንካ መምህራን ማህበር የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጌታቸው እንደገለፁት ማህበሩ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በ72 አባላት በ5 ሺህ 870 መነሻ ካፒታል ተቋቁሞ በአሁን ወቅት የአባላት ብዛቱን ወደ 279 ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በዚህም የቁጠባ መጠኑን ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ከፍ ማድረግ መቻሉንም አቶ ዘላለም አስረድተዋል።

በዋናነት የማህበሩ አባላት በመቆጠብ በማህበሩ ከሚመቻቸው ብድር ተጠቃሚ በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙም ሰብሳቢው ገልፀዋል።

በቀጣይ ወደተሻለ ምዕራፍ ለመሸጋገር በጂንካ ከተማ አስተዳደር ሁለገብ ገቢ ማስገኛ ኮፕሌክስ ህንፃ ለመገንባት ቦታ የጠየቁ ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡአቸው የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ጠይቀዋል።

በ20ኛው ጠቅላላ ጉባኤ የክንውን፣ የኦዲትና ሌሎች ሪፖርቶችና ውስጠ ደንቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጉራልቅ ይዥማል ማህበሩ እያከናወነ ያለው ተግባር ልምድ የሚወሰድበት ስለመሆኑ ገልፀዋል።

ለተጠየቀው የገቢ ማስገኛ ቦታ በቀጣይ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሠራ አቶ ጉራልቅ ተናግረው የማህበሩ አባላት ጠንክረው በመሥራት ራሳቸውንና በገበያ ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ችግርን ለማረጋጋት የድርሻቸውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን