በደረሰ አስፋው
ፖሊስ ከመሆናቸው በፊትና ከሆኑ በኋላ የነበራቸው አስተሳሰብ ለየቅል ነው። ወደ ስራው ከገቡ በኋላ ፖሊስነት ከፍተኛ ሀላፊነት ያለበት እና የሚወደድ ስራ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙ የስራ አማራጮች ቢኖራቸውም ሙያውን መልቀቅ አልቻሉም፡፡ በባለቤታቸው ሳይቀር ግፊት ቢደረግባቸውም ከስራቸው አልለያይም ብለዋል፡፡ ለ20 ዓመታት በሙያው ያገለገሉት የፖሊስ አባሏ ሴትነት እንኳ ሳይገድባቸው በርካታ ኃላፊነቶችን ተወጥተዋል፡፡
“ሀብት ፈጥረሽ እንዴት በዚህ ስራ ላይ ትሆኛለሽ?” እያሉ የሚተቿቸው ባይጠፉም፣ እሳቸው ግን ለጥቅም ሳይሆን የሙያውን ክብር ፈልገው እንደሚሰሩ ይሞግታሉ። “ገንዘብን ሳይሆን ዓላማን አስቀድማለሁ” ሲሉም ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ብዙ ፖሊሶች ተጓዳኝ ስራ እያላቸው እስከ ጡረታ መቆየታቸው ሚስጥሩ ይህ እንደሆነም ተረድተዋል፡፡ ከፖሊስ ስራ ወጥቶ በህይወት መኖር የሚቻል የማይመስላቸው እንዳሉም ነው የተናገሩት፡፡ “የፖሊስ ተቋም ጥቅም ማግኛ አሊያም ሱቅ አይደለም፡፡ ፍትህ ሰው በገንዘብ የሚገዛው ሳይሆን በነጻ የሚያገኘው ነው” ሲሉም ይናገራሉ፡፡ እኚህ እንስት ማናቸው? ማለታችሁ አይቀርም፡፡
ኢንስፔክተር አሳሳሺኝ አሸናፊ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በሲዳማ ክልል አለታ ወንዶ ከተማ ነው፡፡ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም በአለታ ወንዶ ከተማ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ ከ8ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ደግሞ በአማሮ ኬሌ ነው የተማሩት፡፡ በ1995 ዓ.ም የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የፖሊስነት ሙያን ተቀላቀሉ፡፡ በቅድሚያ ወደ ብላቴ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው ለአምስት ወር የተሰጠውን ስልጠና ወሰዱ፡፡ ከስልጠናው በኋላ በቀድሞው ከምባታ ጠምባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ ለ2 ዓመታት፣ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ለ8 ዓመታት፣ በሲዳማ ክልል ቀባዶ ከተማ ለ3 ዓመታት፣ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ወደ ሀዋሳ ከተማ ተዛውረው ህዝብንና ሀገርን በሚወዱት ሙያ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
በወቅቱ በ10ኛ ክፍል ፈተና የተመኙት ውጤት ባለማምጣታቸው ወደ ፖሊስነት ሙያ እንደገቡ ያስታውሳሉ፡፡ ስልጠናውን ወስደው ወደ ስራ ሲገቡ ግን ሙያውን እንደወደዱት ነው የተናገሩት፡፡ የፖሊስነት ሙያ ሁሉም ዕውቀት የሚገኝበት በመሆኑ ህይወትን በተገቢው መንገድ ለመምራት የሚያስችል ጠቃሚ ሙያ ነው ሲሉም ነው የተደመጡት፡፡ ኢንስፔክተር አሳሳሺኝ ሰርቶና ተምሮ መለወጥን መርህ ያደረጉ በመሆናቸው ትርፍ ጊዜያቸውን ማባከን በእሳቸው ዘንድ የማይታሰብ ነው፡፡ ለዚህም በዲላ ከተማ ተመድበው በሚሰሩበት ወቅት ከፖሊስ ስራቸው ጎን ለጎን ማታ በጤናው ዘርፍ በነርሲንግ ሙያ ተምረው በ1999 ዓ.ም ዲፕሎማ ይዘዋል፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን ሙያውን ለመልቀቅ አስበው አይደለም፡፡
ይልቅስ የፖሊስ ሀኪም ለመሆን እንጂ፡፡ ምንም እንኳ ያሰቡት ባይሳካም በትርፍ ጊዜያቸው ማታ ማታ በግል የህክምና ተቋማት ይሰሩ ነበር፡፡ የተማሩት የነርሲንግ ህክምና ዘርፍም ቢሆን አልተገታም። በጤና መኮንንነት በ2006 ዓ.ም በመጀመሪያ ዲግሪም ተመርቀዋል፡፡ በዚህም ሙያ ቀን በፖሊስነት ህዝብ እያገለገሉ ማታ ግን በግል የህክምና ተቋም በሙያቸው ይሰሩ ነበር፡፡ በዚህም ቢሆን ወደ ሀዋሳ መጥተው በፖሊስ ጤና ጣቢያ ለማገልገል ቢመኙም የኃላፊዎቻቸውን ይሁንታ ባለማግኘታቸው በሰለጠኑበት ሙያ ማገልገል አልቻሉም፡፡ “ስኬት አሊያም ውጤት ያለትጋት አይገኝም” የሚሉት ኢንስፔክተር አሳሳሺኝ፣ ለዛሬው ህይወታቸው መሰረት የጣሉትም በራሳቸው ትጋት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ የፖሊስነት ስራ ተግዳሮቶች ያሉበት እንደሆነ ገልጸው ችግሮችን ለማለፍ ግን ጥበብን እንደሚጠይቅ ያብራራሉ፡፡
በዲላ ከተማ የወንጀል መርማሪ ሆነው በሰሩበት ወቅት ይህን አይተዋል፡፡ ወንጀለኛ ወንጀል ሰርቶ ከወንጀል ለማምለጥ የሚያደርገውን ጥረት ብስለት በተሞላበት መልኩ ወንጀልን አጣርቶ ለፍርድ ማቅረብ እና ፍትህን ማስፈን እንደሚያስደስታቸው ነው የተናገሩት፡፡ “በህክምናው ህመምተኛ አክሞ ሲድን እንደሚያስደስት ሁሉ ፍትህንም ስታሰፍን ያስደስታል፡፡ የተበደለ ሰው ውስጡ ሲደሰት፣ ሲካስ ከመመልከት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም” ይላሉ፡፡ ኢንስፔክተር አሳሳሺኝ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በትራፊክ ፖሊስነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በአፖስቶ ፖሊስ ኮሌጅ ለ3 ወራት የሚሰጠው የትራፊክ ፖሊስ ስልጠና አጠናቀው ወደ ትራፊክ ስራ ገብተዋል፡፡
“የትራፊክ ፖሊስ በአብዛኛው ለሃሜትና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው፡፡ እርስዎ በዚህ አልተፈተኑም?? የሚል ጥያቄ አነሳንላቸው። ለዚህም መልሳቸው አጭር ነው፡፡ “ሀጢአት ነው፤ እርግማን ይዤ ወደ ልጆቼ አልገባም።” በማለት፡፡ በቀባዶ፣ ዲላና ሀዋሳን ጨምሮ ለ8 ዓመታት ያህል በትራፊክ ፖሊስነት አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ይገኛሉ፡፡ “ብልሹ አሰራርን እምነቴ ይኮንነዋል፡፡ ይህ ደግሞ በመስመር ላይ ስሰራ ልዩ መገለጫዬ ነው፡፡ ትዕቢትን እጠላለሁ፤ እውነትን እወዳለሁ፡፡ በስህተት ላይ ያሉ ሹፌሮችን አስተምራለሁ፤ እመክራለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ የሚገኙትን ግን በህጉ መሰረት እቀጣለሁ” ነው ያሉት፡፡ ብልሹ አሰራርን በመጸየፋቸው በስራ ባልደረቦቻቸው ጭምር ተጽእኖ እንደሚደርስባቸው የሚገልጹት ኢንስፔክተር አሳሳሺኝ “መንግስት የሚያመሰግንሽ መሰለሽ? ከዚህ ስትወጪ ማንም ዞሮ አያይሽም። ከዚህ ህዝብ ጋር ነው የምትኖሪው፤ እርምጃሽን ቀንሺ” የሚል ትችትና ተጽእኖ ይደርስባቸዋል። “ጉቦ ይዞ የሚመጣ ሰው በገንዘብ የለካኝ ስለሚመስለኝ ያበሳጨኛል፡፡
ጥፋት ፈልጌና ተደራድሬ ሰዎችን መጉዳት አልፈልግም፡ ፡ ከዚህ ውጪ ግን ህግን የሚጥሱትን በህጉ መሰረት እቀጣለሁ፡፡ ‘ህግን ለምን አከበርሽ’ ለሚሉት ቦታ የለኝም” ሲሉ አቋማቸውን ይገልጻሉ፡፡ የትራፊክ አደጋ በሀገራችን ግንባር ቀደም ገዳይ ክስተት ሆኗል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡ በኢኮኖሚ ባደጉ ሀገራትም ችግሩ ቢኖርም በሀገራችን ደግሞ የባሰ ነው፡፡ የአሽከርካሪዎች የጥንቃቄ ጉድለት፣ የእግረኞች ቸልተኝነትና የግንዛቤ ማነስ፣ የመንገዶች ችግርና የቁጥጥር መላላት ተደማምሮ ችግሩን እንዳባበሰው ነው የተናገሩት፡፡ ለዚህም በሙያቸው በማስተማር ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎችን በመስራት የአደጋ ተጋላጭነት ለመቀነስ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡
ኢንስፔክተር አሳሳሺኝ በትርፍ ጊዜያቸው በቤታቸው ውስጥ በርካታ ኃላፊነቶችን እንደሚወጡ ይናገራሉ፡፡ ባለትዳርና የ5 ልጆች እናት ናቸው፡፡ የእናትነት ሀላፊነታቸውን በተገቢው እንደሚወጡም ይገልጻሉ። ባለቤታቸው በምህንድስና ሙያቸው አብዛኛው ጊዜያቸውን በመስክ የሚያሳልፉ በመሆናቸው እሳቸው ከስራቸው ማታ ሲመለሱ ልጅ የማሳደጉን ስራም አልዘነጉም፡፡ ጊዜን በአግባቡ ከተጠቀምንበት በርካታ ነገሮች መስራት ይቻላል ባይ ናቸው፡፡ በትርፍ ጊዜያቸውም በንግድ ስራ ተሰማርተው ውጤታማ ሆነዋል፡፡ የብረታ ብረት መሸጫ ከፍተው ይሰራሉ፡፡ “ያዮ የብረታ ብረት ንግድ” በሚል፡፡ የቤት በርና መስኮት የሚሰራበትን ላሜራና ሌሎች ግብአቶችን ለሽያጭ ያቀርባሉ፡፡
ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚያሰሩ ካሉም በዚሁ ይሰራል፡፡ ሌላው በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩት ስራም አለ፡፡ “የሌምቦላ ሴክዩሪቲና ጠቅላላ ንግድ ማህበር” በሚል፡፡ በጥበቃ ስራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎችን በማሰልጠን ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ በድርጅታቸው ለመንግስትና ለግል ድርጅቶች በማሰልጠን ብቁ ያደርጋሉ። አሰልጥነውም ሰራተኛንና አሰሪን የማገናኘት ስራም ይሰራሉ፡፡ ከድርጅቶች አብቁልን የሚል ትዕዛዝ ሲመጣም ውል ገብተው ወታደራዊ ክህሎት አስጨብጠው ብቁ የጥበቃ ሰራተኛ ያደርጋሉ፡፡ በ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ስራ የገቡ መሆኑን ገልጸው መመዘኛውን አሟልተው ከፌደራል ፖሊስ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በድርጅታቸው ለ14 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ እስካሁንም ከ130 በላይ የጥበቃ ባለሙያዎችን ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ከሰለጠኑትም 12 የጥበቃ ሰራተኞችን የስራ ባለቤት አድርገዋል፡፡ ውል ተፈራርመው ወደ ስራ ለማስገባት የጠየቋቸው ሌሎች ድርጅቶችና ግለሰቦች እንዳሉም ይናገራሉ፡፡
ስልጠና እንዲሰጥላቸው ለጠየቁ ድርጅቶች ውል ገብተው ለ16 ቀን በተቋማቸው ስልጠናውን ይሰጣሉ፡፡ እስካሁን ከሰልጣኞች የሚቀበሉት ገንዘብ ባይኖርም ከድርጅቶች ጋር ግን ውል ገብተው በገንዘብ እንደሚያሰለጥኑ ተናግረው ክፍያውም እንደተቋሙ የሚወሰን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከልምዳቸው ሌሎች ሴቶችም እንዲማሩ ይሻሉ፡፡ ሴቶች ከወጡ የተሻለ ደረጃ እንደሚደርሱ ነው የተናገሩት፡፡ “በቤት ውስጥ ልጅ በማሳደግ ላይ ብቻ መወሰን የለባቸውም። ባህላዊ ተጽእኖዎችን ማሸነፍ አለባቸው። በዓለም ብዙ ሴቶች ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን እንደቻሉ መዘንጋት የለበትም፡፡
በቤት ውስጥ የባልን እጅ እያዩ መኖር አይገባም፡፡ ሴት ከወጣች ብዙ የስራ አማራጮችን ለማየት ዕድል ታገኛለች፡፡ አስተሳሰቧም ይሰፋል” ሲሉ ይመክራሉ፡፡ ኢንስፔክተር አሳሳሺኝ ወደ ፊትም የጀመሩትን የንግድ ስራ ማስፋት ይፈልጋሉ። በአስመጪና ላኪ የንግድ ዘርፍ ለመሰማራት እንዳቀዱ በመግለጽ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሀገር ሰላም መሆን ትልቁን ድርሻ የሚወጣ በመሆኑ ሰላሙን በመመኘት ነው፡፡ ጊዜ የለኝም አሊያም አልችልም ለሚሉ ሴቶች ለብዙዎች አስተማሪ ነውና እራሳቸውን በስራ በመለወጥ ከተጽእኖ ሊላቀቁ ይገባል የሚለው የዝግጅት ክፍላችን መልዕክት ነው፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው