የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በማልማት ለሀገራዊ እምርታ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ

የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፀጋዎችን በማልማት ለሀገራዊ እምርታ መጠቀም እንደሚገባ ተገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሀገራዊ የብልጽግና ፓርቲ የመካከለኛ አመራር ሁለተኛ ዙር ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ የአመራር አካላት ሰው ሰራሽ የኦሞ ወንዝ ሐይቅን ጨምሮ በልዩ ወረዳው የሚገኙ የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ሀብታሙ በላይነህ በመስክ ምልከታው ወቅት እንደገለፁት፤ የመስክ ምልከታው አመራሮች በስልጠና ያገኙትን እውቀት ወደ መሬት በማውረድ ለሀገራዊ የኢኮ-ቱሪዝም ልማት ዘርፍ እድገት ማዋል እንዲችሉ ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው ነው።

በልዩ ወረዳው የሚገኙ የተለያዩ ፀጋዎችን በጋራ በማልማት ለተሻለ ሀገራዊ እምርታ ለማዋል እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ሁሉም በቅንጅት በመስራት የቱሪስት መዳረሻዎቹን በማስተዋወቁ ረገድ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በፌደራል መንገዶች አስተዳደር እየተገነባ የሚገኘው ከወልዴሃኔ ዱርጊ የፌዴራል መንገድ እየተፋጠና እንደሚገኝ ጠቁመው፤ መንገዱ ሲጠናቀቅ ለልዩ ወረዳውም ሆነ ለአጎራባች አካባቢዎች ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።

በማህበር የተደራጁ ወጣቶች በሐይቁ ዓሳ በማምረት የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተቋዳሽ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የልዩ ወረዳው የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መኮንን ወጮሬ፤ ስልጠናው በግብርናና ገጠር ልማት ትራንስፎርሜሽን፣ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን፣ የከተማ ልማት ዘርፍ ትራንስፎርሜሽንና እንዱስትሪ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመው አመራሩን በእነዚህ ዘርፎች የተሻለ ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

በልዩ ወረዳው ከዱርጊ ወልዴሃኔ የሚሰራው የፌደራል መንገድ የቱሪስት መዳረሻውን ለመጎብኘት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ክልሎች በማገናኘት የህዝቦችን አንድነት ከማጎልበት አንፃር ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

አንድነትን ከሚነጣጥሉ ነጠላ ትርክቶች ይልቅ ገዢ የወል ትርክቶችን በህዝቡ ውስጥ በማስረጽ እንደ ሀገርም ህዝባዊ አንድነትን ማጎልበት ትኩረት የሚሰጥበት ነው ብለዋል።

በመስክ ምልከታው ወቅት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልሃፊዝ ሁሴን፤ የአመራር ስልጠናው ዋናው ዓላማ ሁሉም አመራሮች የጋራ ሀገራዊ አመለካከቶችን በማንገብ በሁሉም ዘርፎች ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ ነው ብለዋል።

በቀጣይም በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎችንም በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ፀጋዎችን በማጎልበት የቱሪስት መዳረሻ የማድረግ ስራዎች ትኩረት የሚሰጥባቸው መሆናቸውን አመላክተዋል።

በመስክ ምልከታው የኦሞ ወንዝ ሰው ሰራሽ ሐይቅ፣ የላሞ ፏፏቴ፣ የላሞ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ደን፣ በግብርና ዘርፍ የለሙ የተለያዩ የልማት ስራዎችና ሌሎችም ተጎብኝተዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን