“አራዳ” ማለት …

“አራዳ” ማለት …

በአንዱዓለም ሰለሞን

እንደምን ሰነበታችሁ በማለት ሠላምታዬን አድርሻለሁ፡፡ አሁን አሁን የሠላምታ አሰጣጣችን ሁኔታና ለሠላምታ የምንጠቀማቸው ቃላት ተቀየሩ እንጂ ሠላምታ መልካም ምኞታችንን የምንገልጽበት ብቻም ሳይሆን ፈጣሪን የምናመሰግንበት ጭምር ነበር፡፡

ምንም እንኳ በጊዜያችን አብዛኞቻችን “ ሀይ ” እና “ ፒስ ነው ? ” ብንባባልም እንደ ወግና ስርዓቱ ሠላምታ መሰጣጣቱ ልዩ ትርጉም ነበረው፡፡ የሠላምታን ነገር ሳነሳና የቃሉን አንደኛዋን ፊደል ስገድፍ ያገኘሁት ቃል (ሠላም) ሌላ ነገር አስታወሰኝ፡፡ ስለ ሠላም ሳስብ ደግሞ የሰሞኑ፣ ለዓለማችን ሠላም ስጋት እየሆነ ያለው ጦርነት ወደ አእምሮዬ መጣ፡፡ … እርግጥ ነው፤ የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት ለማንም እንግዳ ክስተት ያልሆነ ነገር ነው፡፡

ሁለቱ ከልጅነታችን ጀምሮ የውጪ ዜና ላይ የማይጠፉ ሀገራት ነበሩ ብዬ ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ቴዲ አፍሮ እንኳ ስለ እነሱ ሲዘፍን ዕድሜው ገና 20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ “የአይሁድ አትሆኝ ወይ የአራፋት የፍልስጤም እየሩሳሌም ከሰለሞን መቅደስ ትይዩ አላሳ ሁለት የአንድ ልጆች መልካቸው ሬሳ” እንግዲህ ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው በሁለት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ነው፡፡ ያም ሆኖ እዚህ እኛ ዘንድ ደግሞ ለአንዳንዶች ሌላ አንድምታ ፈጥሯል፡፡ ሰሞኑን ምን ገጠመኝ መሰላችሁ? ሁለት ሰዎች ጉንጭ አልፋ ሙግት ገጥመዋል፡፡ የሚጨቃጨቁት በእስራኤልና ፍልስጤም ጦርነት ዙሪያ ነበር፡፡ ችግሩ መጨቃጨቃቸው ሳይሆን ክርክራቸው “ባልሆነ ወገንተኝነት” መታጀቡ ነበር፡፡ አንደኛው የእስራኤል፣ ሌላኛው የፍልስጤም ደጋፊ ሆነው ነበር የሚነታረኩት፡፡ የገረመኝ ግን ደጋፊነታቸው ሳይሆን ምክንያታቸው ነበር፡፡ ለእስራኤል የሚደግፈው ሰው ምክንያቱ ሀገሪቱ “የክርስቲያን ሀገር” በመሆኗ የሚል ነው። ለፍልስጤም የደገፈው ደግሞ ሀገሪቱ “የሙሲሊሞች ሀገር” በመሆኗ የሚል ነው፡፡ ይህን የሁለቱን ሰዎች ምክንያት አፍታተን ስናየው ልክ ያልሆኑ ነገሮች አሉት፡፡

ለምሳሌ በእስራኤል የሚገኙ ክርስቲያኖች ብዛት በመላ ሀገሪቱ ከሚኖረው ህዝብ 1.9 ከመቶ የሚሆን ነው፡፡ ታዲያ ነገሩን ከዚህ አንጻርና በሰውዬው መመዘኛ መሰረት ካየነው እንዴት ሆኖ ነው እስራኤል “የክርስቲያን ሀገር” የምትሆነው? የፍልስጤምን ነገር በተመሳሳይ ካየነው ደግሞ በሀገሪቱ ከሚኖረው ህዝብ 2 በመቶ የሚሆነው ህዝብ የክርስትና ሀይማኖት ተከታይ ነው፡፡ ከዚህ እውነታ ተነስተን ነገሩን ስናየው ደግሞ በሁለቱም ሀገራት የሁለቱም ሀይማኖት ተከታይ ህዝቦች እንደሚኖሩ እንረዳለን፤ የቁጥር ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ከምንም በላይ ዋንኛ ጥያቄ ሊሆን የሚገባውን ነገር ስናየው ደግሞ ይህኛው ሀሳብ ጭራሽ እንደምክንያትም ሊጠቀስ የሚገባው አይሆንም፡፡

ከሀይማኖት በፊት ሠው መሆን ይቀድማልና፡፡ አዳም ሲፈጠር ሀይማኖቱ ምን ነበር ? … የዓለም ሀገራትና ፖለቲከኞች ጥቅማቸውን አስልተው የሚያራግቡትን ጦርነት እኛ እዚህ ተቀምጠንና የራሳችንን ስንት ችግር ትተን ባልሆነ ምክንያት መነታረካችን ያሳዝናል፡፡ እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ነገሩ የሆነው በታዳጊነቴ ጊዜ ነበር፡፡ ከጓደኞቼ እና ከሰፈር ልጆች ጋር ሆነን የኢትዮጵያንና የግብጽን የእግር ኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን እያየን ነበር፡፡ በመሀል ግብጾች ጎል አስቆጠሩ። ይህን ጊዜ የተወሰኑ ልጆች አጨበጨቡ። የጭብጨባው አንድምታ ግራ ቢያጋባንም ምናልባትም የብስጭት እንጂ የደስታ ስሜት መግለጫ ይሆናል ብለን አላሰብንም ነበር። (“ወደው አያጨበጭቡ” እንዲል አንድ አጨብጫቢ ወዳጄ ) ይህ እንዴት ይታሰባል ? እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር፡፡

ልጆቹ ያጨበጨቡት በእርግጥም ግብጾች ጎል በማግባታቸው ተደስተው ነበር። የሚገርመው ደግሞ ለዚህ ምክንያታቸው ሀይማኖት መሆኑ ነው፡፡ (እነሱ የእስልምና ሀይማኖት ተከታይ በመሆናቸውና ግብጽም “ የሙስሊሞች ሀገር ” ስለሆነች ማለት ነው) ክስተቱ ለማመን ቢከብድም በወቅቱ የገጠመኝና የታዘብኩት “ መራራ ዕውነት ” ነበር፡፡ “ገና ሀገር ማለት ትርጉሙ አልገባንም” ይሏል ለእንደዚህ ዓይነቱ ነገር ነው፡፡ እዚህ ጋ ልጆቹ ያልተረዱት ነገር ሀይማኖትንና ሀገርን ለያይቶ አለማየትን ብቻም አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከዚህ አንጻር በተለይም ደግሞ ሀገራችን “ኢትዮጵያን አትንኩ” በሚል በነብዩ መሀመድ የተገባላትን ቃል አለማጤናቸውን የሚያስገነዝበን ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ ለአንዳንዶች የአንዳንድ ነገር ትርጉምና ልክ አይገባቸውም፡፡ ችግሩ ግን እንዳልገባቸው ስለማይረዱ ነገሩን ተገቢ ባልሆነ መልኩ ይገልጹታል፡፡ እናም እነሱ በገባቸው ልክ ለሌሎች ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ያኔም አለመግባባት ይፈጠራል። ወግም አይደል የያዝኩት፤ እንግዲህ አንዱን እያነሳሁና ሌላኛውን እየጣልኩ መቀጠሌ የግድ ነው፡፡ እዚህ ጋ ትዝ ያለኝን አንድ ነገር ላንሳ፡፡ ነገሩ ከጓደኞቼና ከሌሎች ሰዎች ጋር ሰብሰብ ብለን እየተጨዋወትን ሳለ የተከሰተ ነው፡፡ በጨዋታችን መሀል ስለሆነ ሰው ተነሳ፡፡ አንደኛው እንግዳ ሰው ስለ ሰውዬው ማንነት አጠር አድርጎ ተረከልን። ሀብታም እንደሆነና ሀብቱን ያገኘውም ከሚሰራበት የመንግስት መስሪያ ቤት አጭበርብሮ እንደሆነ ከነገረን በኋላ “ አራዳ ነው ” ሲል ሰውዬውን አድንቆ ንግግሩን ቋጨ። ይህንን ጊዜ የሰውዬውን ንግግር በጥሞና ሲያደምጡ የነበሩት ወዳጃችን ፡-

“አራዳ ማለት ግን ምን ማለት ነው ?” ሲሉ ሰውዬውን ጠየቁት፡፡ ሰውዬም ፡- “ አራዳ ማለት … ” አለና ለአፍታ ነገሩን በእንጥልጥል ተወው፡፡ ሰውዬው አስቀድሞ ከተናገረው ነገር አንጻር፤ አራዳ ማለት አጭበርብሮ ሀብታም የሚሆን ሰው ነው ማለት ነበረበት፡፡ ይህን ለማለት ግን አልደፈረም፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ነገሩን ብሎታል፡፡ ሁኔታው “ አልሸሹም ዞር አሉ ” እንደማለት ነበር፡፡ እርግጥ ነው፤ ዛሬ ላይ ብዙ ሊኮነኑ የሚገባቸው መሰል ድርጊቶች “ አራዳ ” እያስባሉን ነው፡፡ መስረቅ “ እርድና ” ሆኗል። መዋሸትና ማስመሰልም እንዲሁ፡፡ ህዝብን የሚበድል፣ ሀገርን የሚጎዳ ድርጊት መፈጸም ሳይቀር እንደ “ አራዳነት ” እየተቆጠረ፣ ይህን የሚያደርገው ግለሰብም “ አራዳ ነው ” እየተባለ እየተሞካሸ ነው፡፡ … ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ፤ ለአራዳ ትርጉም አጥቶ ወይም ከተናገረው ነገር ጋር የሚሄድ ትርጉም መስጠት አፍሮ ነገሩን በእንጥልጥል የተወውን ሰው ላለማሳፈር ሲሉ ጋሼ ጨዋታውን ቀየሩት፡፡

ጋሼ የህይወት ልምድ ብዙ ያስተማራቸው አስተዋይ ሰው ናቸው፡፡ ( አራዳ ብላቸው ስህተት ይሆን ?) ጥያቄውን ወደ እኛ አዞሩትና ከእኔ ጀመሩ፡፡ እኔም ፡- “ አራዳ ራሱን ሲጠቅም ሰውን የማይጎዳ ነው ” አልኳቸው እንደዋዛ፡፡ ወደ ሌላኛው ጓደኛችን ተመለከቱ፤ አንተስ ለማለት፡- “ አራዳ ቤተሰቦቹን የሚረዳ ነው ” አላቸው፡፡ ሌላኛው ጓደኛችን ተከተለለ ፡- “አራዳ ማለት የራሱን ህይወት በአግባቡ የሚመራ ነው ” አለ፡፡ ሌላኛው ጓደኛችን ቀጠለ ፡- “ አራዳ ማለት ነገሮችን በዕውቀት፣ በምክንያትና በጥበብ የሚመዝን አስተዋይ ሰው ነው ” ጋሼ ወደ ሌላኛው ጓደኛችን ፊታቸውን አዞሩ፤ ምላሹን ሽተው፡፡ ጓደኛችን ፈገግ አለና አያቸው፡፡ ጋሼ አተኩረው እያዩ ጠበቁት፡፡ እሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- “ አራዳማ ቢራ ነው ! ” የጅምላ ሳቅ ! … “ ምን!? አራዳ የሚባልም ቢራ አለ እንዴ!? ” ጋሼ ጠየቁ፤ ፈገግ ብለው፡፡ “ ቆየ እኮ ! ” “ያሰላም፤ እሱን እኔ አላውቅልህም!” አሉ ጋሼ እየሳቁ፡፡ በዛው ሳቅና ጨዋታው ደራ፡፡ እኔ ግን ጨዋታውን እዚህ ላይ ገታ አድርጌ፤ አንደኛው ጓደኛችን “አራዳነትን” የተረጎመበትን መሰረት በማድረግ እንደመውጫ ከማህበራዊ ድረ ገጽ ያገኘሁትን አንድ ጽሁፍ ጀባ ብያችሁ እሰናበት ዘንድ ወደድኩ፡፡

ነገሮችን በዕውቀት፣ በምክንያትና በጥበብ መመዘን በእርግጥም ትልቅ ነገር ነው። ይህ ግን ዝም ብሎ የሚመጣ ነገር አይደለም፤ ከህይወት ልምድ የምንማረውና በንባብ የምናዳብረው እንጂ፡፡ አሁን ለመውጫ ወዳልኳችሁ ጽሁፍ ልለፍ ፡- ዳኛው የቀድሞውን የግብጽ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳትን የገደለውን ሰው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት ፡- “ሳዳትን ለምን ገደልከው ? ” ገዳዩም ፡- “ እርሱ ሴኩላር ነው ” ሲል መለሰ፡፡ ዳኛው ፡- “ ሴኩላር ማለት ምን ማለት ነው ? ” “ አላውቅም ! ” ነበር የገዳዩ መልስ፡፡ ደራሲ ነጂብ ማፉዝን ለመግደል በተደረገ ሙከራ ደራሲውን በስለት ያቆሰለውን ሰው ዳኛው ፡- “ ለምን ወጋኸው ? ” ሲሉ ጠየቁት፡፡ አሸባሪውም ሲመልስ፡- “የሰፈራችን ልጆች በተሰኘው ልቦለድ መጽሀፉ ምክንያት ነው ” አለ፡፡ “ ይህን ልቦለድ መጽሐፍ አንብበኸዋል? ” ወንጀለኛውም አለ፡- “ አላነበብኩትም ” አንድ ሌላ ዳኛ ደግሞ ግብጻዊውን ደራሲ ፋራጅ ፉአድን የገደለውን አሸባሪ ፡- “ ፋራጅ ፉአድን ለምን ገደለከው ? ” ሲሉ ጠየቁት ፡- “ እምነተ ቢስ ስለሆነ ” አሸባሪው መለሰ። “እምነተ ቢስ መሆኑን እንዴት አወቅክ? ” አሸባሪውም አለ ፡- “ ከጻፋቸው መጻሕፍት ” “ከየትኛው መጽሐፉ ነው እምነተ ቢስ መሆኑን የተረዳኸው ? ” “መጽሕፍቶቹን አላነበብኳቸውም ” “እንዴት ማለት? ለምን አላነበብካቸውም?” “ ምክንያቱም እኔ ማንበብ ሆነ መጻፍ አልችልም” ሲል መለሰ አሸባሪው !!! እንግዲህ ምን እንላለን፤ ከእንዲህ ዓይነቱ ነገር ይሰውረን ከማለት በስተቀር፡፡ ቸር ይግጠመን ብዬ ተሰናበትኳችሁ፤ ሠላም !!!