“ወባ በጣም ቀላል እና መከላከል የምንችለው በሽታ ቢሆንም ዋጋ አስከፍሎናል” – አቶ ፍሰሀ ለመዕንጎ
በገነት ደጉ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ፍሰሀ ለዕመንጎ ይባላሉ፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ በጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ለ17 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ በክልሉ የወባ ጫና፣ የህብረተሰቡ ግንዛቤ፣ የመድሀኒትና አጎበር አቅርቦትና ስርጭት በሚሉ ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡– ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!
አቶ ፍሰሀ፡– እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ!
ንጋት፡– ከልጅነት ጀምሮ ያለው የትምህርት ዓለም ጉዞዎን በማንሳት እንጀምር?
አቶ ፍሰሀ፡– ትውልድና እድገቴ በገጠር አካባቢ ሲሆን በከምባታ ዞን ዶዮ ገና ወረዳ ነው፡፡ ዕድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ ወደ ትምህርት ቤት ገብቼ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ዶዮ ገና 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ እዛው ዶዮ ገና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትዬ አጠናቅቄያለሁ፡፡
የመጀመሪያ ድግሪዬን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ድግሪዬን በ2003 ዓ.ም ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በህብረተሰብ ጤና ተከታትዬ ተመርቄያለሁ፡፡
በኋላም ከዶዮ ገና ወረዳ እስከ ክልል ድረስ ባለው ከባለሙያነት እስከ ኃላፊነት ባሉት መዋቅሮች አገልግያለሁ፡፡
በመጀመሪያም ዶዮ ገና ወረዳ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን ለሶስት ዓመታት ያህል ያገለገልኩ ሲሆን እዛው ዶዮ ገና የወረዳ አስተዳዳሪ በመሆን፣ በዱራሜ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ በመሆን ለአንድ ዓመት፣ ለሶስት ዓመታት የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሊጅ ዲን፣ በቀድሞው ደቡብ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት የላብራቶሪ የስራ ሂደት ባለቤት፣ እዛው ጤና ቢሮ ፖሊሲ ጥናት የጤና ፖሊሲ ፕላን የስራ ሂደት ባለቤት በኋላም የቢሮው ኃላፊ አማካሪ በመሆን፣ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲዩት ምርምር ዳይሬክቶሬት ላይ የበሽታ መካላከል ዳይሬክተር በመሆን ያገለገልኩ ሲሆን አሁን ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልለ ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን እያገለገልጉ ነው፡፡ በአጠቃላይ ለ17 ዓመታት ያህል አገልግያለሁ፡፡
ንጋት፡– በክልሉ የወባ በሽታ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ፍሰሀ፡– የወባ በሽታ አሁንም በዓለማችን የማህበረሰብ የጤና ስጋት ሆኖ የቀጠለ በሽታ ነው። በገዳይነቱ አሁንም ብዙ ሰዎችን እየገደለ ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት በ2024 የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በዓመት ወደ 263 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ እንደሚያዙ ያሳያል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 557 ሺ ሞት እንደተመዘገበ ነው ያመላከተው፡፡
ይህም ማለት አሁንም ወባ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ነው ማለት ነው፡፡ ወባ በቀላሉ ልንከላከለው የምንችለው በሽታ ነው፡፡ በሽታው በወባ ትንኝ አማካይነት ነው የሚተላለፈው፡፡ ስለዚህም ወባን አራት ዋና አስተላላፊዎች አሉ፡፡
የመጀመሪያው ፋልስፋረስ፣ ሁለተኛው ቫዮቫክስ፣ ሶስተኛው ኦቫሌ እና ማላሪያ ሲሆኑ በሀገራችን በዋናኛት ያሉት ፋልስፋረምና ቫዮቫክስ ሲሆኑ ሌሎች ሁለቱ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር በእኛ ሀገር ጫና የላቸውም። አልፎ አልፎ ወደ ምስራቅ የሀገራችን አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡
ስለዚህ በቀላሉ መከላከል የምንችልባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ያም ማለት ትንኟ እንዳትራባ ማድረግ ነው፡፡ ትንኟ የምትራባው በጉበት ውስጥ ነው፡፡ ከጉበት ፈንድታ ስትወጣ ወደ ቀይ የደም ሴሎች ትገባና ቀይ የደም ሴሎችን እየተመገበች ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ ዕድል ታገኛለች ማለት ነው፡፡
ስለዚህም ይህንን መከላከል የምንችለው መጀመሪያ ቨክተሯን ወይንም ተዋሲያን ተሸካሚዋን ትንኝ በማጥፋት ነው፡፡ ትንኟን ማጥፋት የሚቻለው የአካባቢ ቁጥጥር ስራ በመስራት ነው፡፡
በተለይም እኛ የማንጠብቃቸው በሸክላ ስባሪና በጎማ ላይ የተጠራቀመ ውሃ፣ በእንሰት ኮባ ውስጥ ያለ ውሃ እነዚህ ውሀዎች በቀላሉ በአንዴ ብዙ እንዲፈለፈሉ ምቹ ዕድል ይሰጣሉ፡፡
ከዚህም ሰፋ እያለ ሲሄድ ያቆሩ ውሃዎች ማለትም ለተለያዩ አግልግሎቶች የምንጠቀማቸው ውሃዎች በዋናነት ለትንኟ መራቢያነት እንደ መነሻነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር ለመስኖ የምንጠቀማቸው በአንድ ቦታ ረግተው የሚቆዩ ውሃዎች ጠርገው ስለማይሄዱ ለወባ ችግር አላቸው፡፡ እነዚህን በደንብ ከሰራን ውሃዎች ለበሽታው መስፋፋት መንስኤ ናቸው፡፡
ሌላው በወባ በሽታ ከተያዝን ደግሞ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ነው፡፡ በወባ በሽታ ተይዘን ወደ ህክምና ተቋም ካልሄድን ህይወታችንን ልናጣ እንችላለን፡፡
እንደ ሀገራችን ባሳለፍነው ዓመት ከ9 ሚሊየን ያላነሱ ሰዎች በወባ የታመሙ ሲሆን ወደ ክልላችን ስንመጣ ከ5ሺ 160 የሚሆኑ ሰዎች ወባ የተያዙ ሲሆን ከ 44 ያላነሱ ሞቶች ተመዝግበዋል፡፡
ይህም ማለት አሁንም የወባ በሽታ ገዳይ ስለሆነ ከመከላከል በተጨማሪ ከተያዝን ወደ ህክምና ተቋማት መሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን ቀድመን የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ከዚያ ባሻገር የአጎበር አጠቃቀም ማስተካከል አለብን፡፡ ምክንያቱም ትንኟ በሽታ ከማስተላለፏ በፊት ህይወት ኡደት ደረጃዎች አሏት፡፡ የወባ ትንኝ የዕድገት ደረጃዋን መቁረጥ ያስፈልጋል፡፡ በአካባቢ ጥበቃ ስራ የራሷን የዕድገት ደረጃ ጨርሳ ከመብረሯ በፊት ዕድገቷን ማቋረጥ ይቻላል፡፡
ነገር ግን መብረር ከጀመረች ማድረግ ያለብን የአልጋ አጎበር መጠቀም፣ በቤት ውስጥ ርጭት ማካሄድ ነው፡፡ በዚህም በራ እንኳን ብትመጣ የመቆየት እና የማስተላለፍ ዕድሏ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡
የወባ በሽታ ገዳይ ነው ስንል ከያዘ ዝም ብሎ የሚገድል አይደለም፡፡ የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስ በጊዜ ከታከምን ሊድን የሚችል በሽታ ነው፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ በዚህ መልኩ ቢያየው ወባን በቀላሉ መከላከል የምንችለው በሽታ ነው፡፡
ንጋት፡– የሰውነት ወባ እና የጭንቅላት ወባ ልዩነታቸው ምን ይሆን አስተላላፊዋስ ትለይ ይሆን?
አቶ ፍሰሀ፡– አስተላላፊዋ የወባ ትንኝ ናት፡፡ የምታስተላልፈው ሴቷ ወባ ትንኝ ናት፡፡ ወባ ሰውነት ላይ ምልክት ሳያሳይ ከ10 እስከ 15 ቀናት ሊቆይ ይችላል፡፡ በተለይም በተደጋጋሚ በወባ በሽታ የሚጠቁ ሰዎች የበሽታውን ምልክቶችን የማሳየት እድላቸው ጠባብ ነው፡፡
ምክንያቱም ብዙ ጊዜ በወባ የሚያዙ ሰዎች ሰውነታቸው እየለመደ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም ጉበት ላይ ሲሆን ቀይ የደም ሴሎችን እየበላ ሲሄድ ከሰውነታችን ደም እየጠጣች ነው የምትሄደው፡፡ ይህም ሰዎች ለደም ማነስ በሽታ እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡
በተለይም ህፃናትና ነፍሰጡር እናቶች በሂደት ከሰውነት እየወጣ ወደ ጭንቅላት ይሄድና የማድከም፣ እራስን መሳት ሊታይባቸው ስለሚችሉ ሲሰራጭ ነው የጭንቅላት ወባ የምንለው፡፡ እንጂ የሰውነትና ወይንም የጭንቅላት ወባ ተብሎ የተለየ የለም፡፡
ህክምናቸው ግን ሊለያይ ይችላል፡፡ ፋልሲ ፋረም በቀላሉ በኳርተም የሚድን በሽታ ነው፡፡ ነገር ግን ተደጋጋሚ በወባ እየታመሙ የሚመላለስ ሰው ካለ መድሀኒቱ ለየት ብሎ ነው የሚታዘዘው፡፡ እንደ የሰውዬው ጉዳት ዓይነት የመድሀኒት አሰጣጡ ሊለያይ ይችላል፡፡
ንጋት፡- እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አሁናዊ የወባ ጫና እንዴት ይገለፃል?
አቶ ፍሰሀ፡- በክልሉ ባሳለፍነው ዓመት ከፍተኛ የወባ ጫና ነበረው፡፡ ከግማሽ ሚሊየን ሰዎች በላይ ህዝብ ነበር በወባ ታሞ የነበረው፡፡ ይህንን ለመመከት እንደ ክልል ከፍተኛ ርብርብ ተደርጓል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ የተለያዩ የአካባቢ ቁጥጥር እና ህብረተሰቡን የማንቃት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም ዓምና ክረምት ላይ የነበረው የወባ ጫና እና ዘንድሮ ከዓምናው የቀነሰ እና የተሻለ ነው፡፡
ባሳለፍነው አመት በመስከረም ወር ላይ የነበረው ጫና በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ለአብነትም ዓምና በአንድ ሳምንት እስከ 20 ሺ የህብረተሰብ ክፍል በወባ ይያዝ ነበር፡፡ ዘንድሮ በጣም ዝቅተኛው ከ6 አስከ 7ሺ ነው፡፡ ይህም ማለት በተሰሩ ስራዎች ጫናው ሊቀነስ የቻለ ነበር፡፡ በተለይም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ መደበኛ የዝናብ ወቅት ሲሆን ወባ ተጠርጎ የሚሄድበት ሲሆን የትንኟን የመራባት ኡደቷን ያጠፋዋል፡፡
ወባ ከክረምት ወደ በጋ መሸጋገሪያ እስከሚሆን ይጠብቃል፡፡ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር የረጋ ውሃ እና ወዲያውኑ ፀሐይ ሲገኝ ከሶስት እስከ አምስት ባሉት ቀናት ውስጥ መብረር ወይም መውጣት ጀምራል፡፡ ስለዚህ ስርጭቱ በዚያ መልኩ እንዳይሄድ ማድረግ ነው፡፡
በዚህም መነሻ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተሰራው ስራ ደግሞ አመራሩ ቁርጠኛ በመሆን ሁሉም በዚህ ላይ በመረባረብ ህብረተሰቡም ያስተማርናቸውን ነገሮች ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ የመቀነስ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡
ቀንሷል ስንል መጠነኛ ወባ የሚተላለፍባቸውና ከፍተኛ የወባ ጫና የሚኖርባቸው ጊዜያት ያሳለፍነው ክረምት እስከ ሰኔ ባለው ሚያዚያን ጨምሮ ነበር፡፡
ከዚያም ክረምት ላይ ዝናብ ይሆንና ከመስከረም ጀምሮ አራት ወራት ማለትም እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ከፍተኛ የወባ ጫና ይኖራል ተብሎ የሚታሰብበት ወቅት ነው፡፡
አሁን ላይ ስናየው መስከረም ላይ ያለው ጫና ጥሩ ነው፡፡ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ከፍተኛ የወባ ጫና የሚኖርበት ወቅት ነው፡፡ ለዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጀምሮ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ባለሙያዎችም ህብረተሰቡን በማስተማር ታችኛው መዋቅር ላይ ናቸው፡፡
ንጋት፡– ህብረተሰቡ ስለወባና አጐበር አጠቃቀም ያለው ግንዛቤ ምን ይመስላል?
አቶ ፍሰሀ፡– ወባ ከእኛ ጋር አብሮ የኖረ በሽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በህብረተሰቡ ዘንድን የከፋ ግንዛቤ ይኖራል ብለን አናስብም፡፡ ባየናቸው በተለያዩ ድጋፋዊ ክትትሎችም እንዳረጋገጥነው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለ ወባ በሽታ ግንዛቤ አለው፡፡
ከዚህ ቀደም ሲል ደጋ አካባቢዎች ላይ ወባ በብዛት አይታይም ነበር፡፡ አሁን ላይ አልፎ አልፎ በደጋማ አካባቢዎችም የወባ ጫና አለ፡፡
ከዚህ በፊት ወባማ ባልሆኑ አካባቢዎች እንዴት ነው የሚራባው ስንል ከሽንት ቤት ጋር ያገናኛሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ክፍተት ባለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤው አላቸው፡፡ የቅድመ መከላከል ስራዎችንም በጋራ እየተሰሩ ነው፡፡
አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ የምንረዳው የግንዛቤ ክፍተት ብዙም የለም፡፡ ነገር ግን የግንዛቤ ክፍተት የለም ብለን ስናበቃ የምናየው ነገር የአጎበር አጠቃቀም ላይ ችግሮች አሉ፡፡
የተሰራጨውን አጎበር ሁሉም ሰው ለታለመለት አላማ ያውላል ማለት አይቻልም፡፡ ከ50 አስከ 70 በመቶ ሲጠቀሙ ስናይ የግንዛቤ ክፍተት አሁንም አለ ወደሚል ድምዳሜ እንደርሳለን፡፡
የአካባቢ ቁጥጥር ማለትም የማፋሰስና የማዳፈን ስራው ከወባ በሽታ ይልቅ ለእርሻው ስራ እና ለከብቶች ቅድሚያ መስጠት ነገሮች በስፋት ይታያሉ፡፡ ያቆሩ ውሃዎች ብናፋስስ ከብቶቻችን በጋ ሲሆን ምን ይጠጣሉ በማለት ያስባሉ፡፡ ማለት ወባ ሊያሳድር የሚችለውን ከፍተኛ ተጽዕኖ የተገነዘበው ደግሞ ያንን መተባበርና መስራት ይጠበቃል፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች አሉ፡፡ ሁሉም አካባቢ እንደዚህ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
በተለይ በ2011 እና በ2012 ዓ.ም የወባ ጫና ዜሮ የደረሰበት ነበር፡፡ ያም ማለት ህብረተሰቡ ወባ ጠፍቷል ወደሚለው እሳቤ በመግባት የመዘናጋት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
በዚያን ጊዜ ነው ወባ እንደገና ማንሰራራት የጀመረው፡፡ በኋላም ከ2015 ዓ.ም በኋላ እየጨመረ መጥቶ በ2016 ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በ2017 በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ስጋት የሆነበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ይህም ሲታሰብ በወቅቱ የተሰራጨ የአልጋ አጎበር እና በቤት ውስጥ የተደረገ ኬሚካል ርጭት እንዲሁም ያቆሩ ቦታዎችም ላይ ኬሚካሎችን የመርጨት ስራዎች እየተሰሩ የወባ መጨመር ሁኔታዎች ታይተዋል፡፡
ህብረተሰቡም ከወባ ይልቅ ትኩረቱን ወደ ሌላ ጉዳዮች አድርጎ ነበር፡፡ በሽታውም የመስፋፋት አጋጣሚውን አግኝቷል፡፡
ወባ በጣም ቀላል እና መከላከል የምንችለው በሽታ ቢሆንም ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ የህብረተሰቡ መዘናጋት ወባ እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ሳይሰራ ቀርቶ ሳይሆን እየተሰራም መዘናጋቶች ተፈጥረው ነበር፡፡
አሁን ላይ ከዓምናውና ከዓቻምናው አንፃር ህብረተሰቡ ተምሮ አጎበር እና ርጭት አድርጉልን ነው የሚለው፡፡ ይህም መፍትሔ አይሆንም፡፡ በቀላሉ መከላከል ስንችል ግን ብዙ ተግዳሮቶችን እናስተናግዳለን፡፡
ህብረተሰቡ ወባ እንዳይራባ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ከሰራ ማጥፋት እንችላለን፡፡ ርጭት ኬሚካል ሲሆን በሂደትም የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረዋል፡፡ በርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ክልላችን ከዓምና መነሻ ተደርጎ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በዋናነት አሁን ላይ የወባ ጫና ባለባቸው ስድስት ወረዳዎች ላይ አጎበር ሙሉ በሙሉ እያሰራጨን ነው፡፡ አስራ አራት የገጠር ወረዳዎች ላይ ደግሞ የቤት ውስጥ ርጭት ስልጠና አልቆ ወደ ተግባር እየገቡ ያሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ቀጣይም በሁለተኛ ዙር የአስራ ሁለት ወረዳዎች የአልጋ አጎበር የሚሰራጭባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡
የወባ በሽታ ከፍተኛ ጫና ያለበት አሁን ከፊታችን ያሉ ሶስት ወራቶች ናቸው፡፡ በእነዚህ ወራት ተግባራትን እንደ አምና እና ካቻአምናው ያለመዘናጋት በእጃችን ያለውን አጎበር ላላስፈላጊ ነገር ከመጠቀም ይልቅ በተገቢው እና በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ከዚህም ውጪ ጥሩ አማራጭ ብለን እንደ ሀገር ሆነ እንደ ክልል ሀላባ ከተማ ላይ የወባ ጫና ያለበት ከመሆኑም ጋር ተያይዞ የህፃናት ክትባት ተጀምሯል፡፡ ክትባቱም በመደበኛ ክትባት ላይ ተካቶ እንዲሰጥ ፓይሌት ተደርጎ ተጀምሯል፡፡ በቀጣይ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋት ስራዎች ይሰራሉ፡፡
ክትባቱ ከአምስት ዓመት በታች ላሉት ህፃናት የሚሰጥ ሲሆን ህፃናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ስለሆኑ ዛሬ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ተብሎ የመጀመሪያ ዙር በተሳካ ሁኔታ ክትባቱ ተሰጥቷል፡፡
ንጋት፡– የአጎበር አቅርቦት እና የአገልግሎት ዘመንስ እንዴት ይገለፃል?
አቶ ፍሰሀ፡– የአጎበር ችግር የለም የምንለው አይደለም፡፡ ችግሩ አለ፡፡ የአጎበር ችግር ባይኖር ይሄኔ ተሰራጭቶ ህብረተሰቡ የሚጠቀምበት ጊዜ ነበር፡፡ ርጭትም ቢሆን አሁን አይደለም የሚረጨው፡፡ በተለይም ከመስከረም ወር በፊት ተረጭቶ በያዝነው ወር ቢያንስ ሊከላከል በሚችል ሁኔታ መሆን ነበረበት፡፡
አንድ አጎበር እስከ አምስት ዓመት መጠቀም ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከአምስት ዓመት ካለፈ አገልግሎት አይሰጥም፡፡
በተለይም ችግሩ ጎልቶ የወጣው ጤናውን ሴክተር የሚደግፉ (ዶነሮች) ለጋሶች በተለይም ግሎባል ፈንድ ዓለም ላይ ከተፈጠረው ሁኔታ አንፃር ጫናው ቀላል አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረውን ያህል አሁን ላይ አቅርቦት የለም፡፡
ከዚህ በፊት ርጭት ተደርጎ አጎበር ይሰጥ ነበር አሁን ላይ ግን ከውጤት አንፃር ኪሳራው ብዙ በመሆኑ አጎበሩን በትክክል ከተጠቀሙ መከላከል ይቻላል፡፡ በትክክል ከተረጨ አጎበር ባይጠቀሙም መከላከል ስለሚቻል ህብረተሰቡም ይህንን ተረድቶ አጐበሩንም ርጭቱን መጠየቅ የለበትም፡፡
በዋናነት አሁን ላይ የቁጥጥር ስራ ነው መስራት ያለበት፡፡ የወባ ትንኝ ከየትም የመጣች አይደለችም እንቁላል ጥላ ነው የምትራባው፡፡
ለወባ መራባት ምቹ ነገሮችን የፈጠርነው እኛው እራሳችን ነን፡፡ ትንሿ ቢምቢ ይህን ያህል ዋጋ እያስከፈለችን ነው፡፡ ህብረተሰቡም ችግሩ ምንድነው ብሎ ማየት አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ የሀብትና የግብዓት እጥረት ይገጥማል፡፡
ህብረተሰባችን ከጤናው በፊት የሚያስቀድማቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለማንኛውም ጤና ይቀድማልና ገንዘብ ያላቸውም የሚሰጠውን አጎበር ከመጠበቅ ይልቅ በገንዘባቸው የተሻሉ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቁ አጎበሮች በገበያ ላይ ስላሉ አቅም ከሌላቸው ሰዎች ጋር እኩል እራሳቸውን ባያዩ እና መንግስትን ባይጠብቁ መልካም ነው፡፡
ንጋት፡– የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከወባ በሽታ ተጽዕኖ ነፃ ነው ማለት ይቻል ይሆን?
አቶ ፍሰሀ፡– አይቻልም፡፡ በርግጥ ዓምና ከነበረው ጫና ወጥቷል፡፡ ሀገራችንም ከወባ ነፃ አይደለችም፡፡
እንደ መንግስትም በ2030 ሁሉንም አካባቢዎች ነፃ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ሲሆን ሀገርም እንደ ሀገር ከችግሩ አልተሻገረችም፡፡ ገና ብዙ መስራትን ይጠይቃል፡፡ ግን አሁን የተፈጠሩ መዘናጋቶች እና ከግንዛቤ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮች የወባ ስርጭትን ነፃ ማድረግ አልተቻለም፡፡
ንጋት፡– ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ፍሰሀ፡– ከቅንጅታዊ ስራዎች አንፃር የጤና ቢሮ ውስጥ በራሱ የሚሰራቸው ቅንጅታዊ ስራዎች አሉ፡፡ ውጪ ላይ ደግሞ ከሌሎች ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር የሚሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡
በዋናነት ቢሮው ከህብረተሰብ ጤና ኢኒስትዩት እና የክልሉ ጤና ቢሮ ጋር ከሶስት እና አራት ዘርፎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ግብረመልስም እየተሰጠው ተግባሩን ይመራል፡፡
በወባ በሽታ የፊት አመራሮች፣ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች እንዲሁም የጉዳዩ ባለቤት ከሆነው ህብረተሰቡ ጋር በጋራ ርብርብ ተደርጓል፡፡ ትልቁ ሀብታችን ህብረተሰቡ በመሆኑ በንቅናቄ መልክ እየተሰራ ነው፡፡
ዓምና ላይ በርዕሰ መስተዳድሮችና በምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች እየተመራ በየሳምንቱ አጀንዳ ተደርጎ ነው ይሰራ የነበረው፡፡ ዘንድሮም በተመሳሳይ በካብኔ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ ከቅንጅት አንፃር ጉድለቶች የሉም፡፡
ንጋት፡– ከብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ አገልግሎትና ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ጋር የሚሰሩ ስራዎች እንዴት ይገለፃሉ?
አቶ ፍሰሀ፡– የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ትንበያ እና የአካባቢ ጥበቃ ስራ እንዲሁም አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በየጊዜው መረጃዎችን ሊከሰቱ የሚችሉ ችገሮች መነሻውን ትንበያ አድርጎ በትኩረት ይሰራል፡፡
በዚህም የወባ በሽታ ብቻ ሳይሆን ምግብ እጥረት፣ ኮሌራ የመሳሰሉትን ቀድመን የተነበይናቸው ናቸው፡፡ ለዚህም ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየትና በማስተማር ረገድ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ጤና ቢሮ እንደ ቢሮ እየሰራ ያላቸው ስራዎች ስላሉ በተለይም ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ጋር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
የክረምት ወራት የዝናብ ጫና አሁን ላይ በመሆኑ ወባ ብቻ ሳይሆን ሌላም ወረርሽኞች ሊኖሩ ስለሚችሉ ባለድርሻ አካላትም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡
ንጋት፡– ለህብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
አቶ ፍሰሀ፡– በተለይም እንደ ክልል ከገጠሩ ይልቅ ከፍተኛ ጫና ያለው ከተሞች ላይ በመሆኑ ከቤቱ እና ከየአካባቢው የሚወጡ ቆሻሻዎች እንዲሁም በተለያዩ ዕቃዎች ትንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ረግተው የሚቆዩ ውሃዎች ለወባ መራቢያ ምቹ ናቸውና እንደ ቀላል ባናያቸው መልካም ነው፡፡
በከተሞች አሁን ላይ የኮሪደር ልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታችን ስለፈጠረ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመልካም መጠቀም ይቻላል፡፡
በመጨረሻም የወባ ትንኝ ከሶስት እስከ አምስት ቀናት ውስጥ መፈልፈል የምትችል በመሆኑ ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ትኩረት በመስጠት ከጫናው እንውጣ መልዕክቴ ነው፡፡
ንጋት፡– ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ፍሰሀ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

More Stories
“ሥራን ማክበርና የሰውን ችግር መረዳት ልዩ ባህሪዬ ነው” – አቶ አወቀ ሲራክ አበጋዝ
“የማባክነው ገንዘብና ጊዜ የለም” – ወይዘሮ ጽዮን አበራ
ሲምቡ ÷ ሌላኛው የአፍሪካ ኩራት