የምርቃት በረከቶች

የምርቃት በረከቶች

በይበልጣል ጫኔ

ልጅ ሆነን ወይም አድገን እንደ ልጅ ለምናደርገው መታዘዝ÷ ምርቃትን ስናተርፍ ኖረናል። በሁሉም ቋንቋ እና ባህል ውስጥ ለሰዎች በጎ ምግባር መልካም መመኘት እና መመረቅ የተለመደ ነው። ይኼ ምርቃት እና ቡራኬም (እንደየእምነታችን) በብዙ ሲያግዘን እና ሲረዳን ኖሯል።

ደምስ መሸሻ የተባለ አጥኚ “የምርቃት ስርዓተ ከበራ ኃይል በሰሜን ወሎ ማህበረሰብ” በተሰኘ ጥናቱ ላይ እንዳሰፈረው÷ ምርቃት በስነ ቃል ዘውግ ውስጥ የሚካተት ሲሆን÷ ከማህበረሰብ ልቦና ጋር የተሳሰረ ነው። ተመራቂ አካላት የማህበረሰቡን ደንብ፣ መመሪያ፣ ባህልና ወግ ለማክበር እና ለማስከበር የሚያስችላቸውን አቅም የመፍጠር ኃይል እንዳለው ይታመናል።

ምርቃት በተሻጋሪነት ሰዎችን የላቀ ምግባር ባለቤት ለማድረግ እና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑ ይገለፃል። እንዲሁም እሴትን የመትከያ፣ የማስጠበቂያ እና ግብረገብነትን የማጠናከሪያ ብልሃት በመሆን የማገልገል ሚና አለው።

አጥኚው “በርንሃርት” የተባለን ፀሐፊ ጠቅሶ ÷ ምርቃት ተመራቂው ግለሰብ ወይም ቡድን በፈጣሪ ዘንድ የተወደደና የተመረጠ ሲሆን÷ ምርቃቱ የፈጣሪ በረከት መሆኑን አመላክቷል። ከዚህም ባሻገር ምርቃት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ረብ ያላቸው ባህላዊ ልማዶችን ማክበር፣ በህግ መተዳደር፣ ታማኝና ታዛዥ መሆን፣ ደካሞችን መርዳት እንዲሁም ሰዎችን አክብረው ሲገኙ ከአንደበት በሚወጡ ገንቢ ቃላት ወይም በመልካም ድርጊታዊ ምላሽ በጎ ሰሪዎች የሚወደሱበት ነው። ምርቃት ያገኙት ግለሰቦች እና ቡድኖች ባከናወኑት መልካም ተግባር የተበረከተልን ነው በማለት÷ በመልካም ተግባራቸው እንዲቀጥሉ የማነቃቃት ኃይል አለው።

የምርቃት ስርዓት በትውልዱ ጉዞ ውስጥ የሚኖር ማህበረሰባዊ ሃብት ነው። በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ በጎ ነገሮች ለምርቃት መከሰት ጉልህ ሚና አላቸው። መግባባት እና መስማማት መመረቅን ያስከትላል። ሰዎች ካላቸው ኃይማኖት፣ እምነት እንዲሁም ሚቶሎጂ ማህበረሰቡ አምኖ የተቀበላቸውን የተጻፉ እና ያልተጻፉ ደንቦችን ማክበር ምርቃትን እንደሚያስገኝ ይታመናል። ምርቃት ዕድሜ ጠገብ በሆኑና ቅቡልነት ባላቸው ሰዎች ሲከወን ይደርሳል ተብሎ ይታመናል።

በነገራችን ላይ÷ ምርቃት ከማህበራዊ ጉዳይነቱ ባለፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። የማህበረሰብን የአኗኗር ዘይቤ፣ ታሪክ፣ እምነት፣ ልማድ እና ስነልቦና ይገልፃል። ማህበራዊ መስተጋብርን ያጠነክራል። በተጨማሪ ማህበረሰብን ለልማት ያነሳሳል፤ በእሴቶች ላይ ተመርኩዞ ህይወትን የመምሪያ ይትባህል ያስገኛል። ግብረገብነትን ያዳብራል። የመከባበር እና የመቻቻል መርህን የማጠናከር ኃይል አለው።

ምርቃት አዎንታዊ ይዘት ያለው ሲሆን ሰዎች በሰዎች ላይ ዋስትና የማሳረፍ፣ በግብረገብነት የመገንባት፣ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ የማድረግ፣ ማህበራዊ መስተጋብርን መመስረት እንዲሁም ልቦናን በማጠናከር በኩል ሚናው የጎላ ነው። በዋናነትም ምርቃት እውነት ላይ ሲመሰረት በልዕለ ተፈጥሮአዊ ኃይል ቅቡል እንደሆነ እና ወደ ተመራቂው የመድረስ ኃይል እንዳለው ይታመናል።

ማህበረሰቡ በዕለት ተዕለት የህይወት መስተጋብሩ ውስጥ ምርቃትን ይገለገልበታል። እንደየአኗኗራችን ምርቃት በልዩ ልዩ አውዶች ውስጥ ይከወናል። ከነዚህ መካከልም÷ በሠርግ ላይ፣ ልጅ ሲወለድ፣ አዲስ ቤት ተሰርቶ ሲገባ፣ አዝመራ ሲሰበሰብ፣ ሰው በስራ ወይም በኑሮ የመኖሪያ ቀዬውን ለቆ ሲሄድ፣ ለአውደ ዓመት በጋራ ሰብሰብ ሲባል፣ ሰዎች ተጣልተው ሲታረቁ፣ በጋራ ቡና ሲጠጣ… ከብዙ በጥቂቱ ምርቃት የሚከወንባቸው አውዶች ናቸው።

ደምስ መሸሻ ከላይ በገለፅኩት ጥናቱ ላይ እንደተገለፀው÷ በአካባቢ እና ሀገር ላይ ጦርነት እንዳይከሰት፣ ድርቅ እንዳይሆን እና ጦርነት እንዳይመጣ፣ የታመሙ ሰዎች ከህመማቸው እንዲፈወሱ፣ ምጥ የተያዙ እናቶች በሰላም እንዲገላገሉ፣ የዘገየ ዝናብ ፈጥኖ እንዲመጣ፣ የግድያ እርቅ እንዳይፈርስ እና እንዲፀና … የምርቃት ስርዓት ይከወናል።

በልዩ ልዩ አውድ ውስጥ የሚከወነው የምርቃት ስርዓተ ከበራ÷ እንደ ልምድ ስለተያዘ እና ከአያት ቅድመአያቶቻችን ጀምሮ ሲወራረድ እኛ ጋ ስለደረሰ ብቻ የሚከወን አይደለም። ይልቁንም በየመልኩ የሚገለጡ ልዩ ልዩ ጠቀሜታዎች አሉት። ይኼንን የምርቃት ጠቀሜታ በጥናቱ ላይም በዝርዝር ሰፍሮ እናገኘዋለን።

ማህበራዊ ጠቀሜታውን ስንመለከት÷ የምርቃት ስርዓት ሲከወን ውህደታዊ ተግባራትን የሚሻ ሲሆን ከአካል ቅርርቦሽ ባሻገር የልቦና ትስስር የሚፈጥሩበት እንዲሁም በጋርዮሽ ተማፅኖ በረከት የሚሹበት ስርዓት በመሆኑ ማህበራዊ መስተጋብርን ያጠናክራል።

በሌላ መልኩም ምርቃት በየተራና በቅብብሎሽ የሚከወን ስርዓት ሲሆን አንድነትን እና አብሮነትን የሚገልፅ በመሆኑ ማህበራዊ ማንነትን የመገንባት ሚና አለው። የሰዎችን ልቦና ዘልቆ የመግባት ኃይል ያለው በመሆኑም ሰዎችን ወደ መልካምነት፣ ደግነት፣ አስተዋይነት፣ እንዲሁም ቅንነት የመለወጥ ኃይል አለው።

ምርቃት በተለያዩ ምክንያቶች ሲከወን የአከዋወን ስርዓቱ እና ሂደቱ ለተከታዩ ትውልድ እንዲተላለፍ እና ቀጣይነት እንዲኖረው መሆኑም ባህላዊ ጠቀሜታው ተደርጎ ይወሰዳል። በተለያዩ ምክንያት የሚተገበሩ ምርቃቶች ትኩረታቸው ምን ላይ እንደሆነ መለየት፣ ባህልን በማስተዋወቅ በኩልም ጠቀሜታ አለው።

የምርቃት አከዋወን ሂደት፣ የምርቃት ሰጪዎቹ ማንነት እንዲሁም የምርቃቱ ትኩረት÷ የማህበረሰብ ወግ፣ ደንብ፣ እሴት፣ የአኗኗር ዘይቤ እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብራቸውን የመግለፅ አቅም አለው። በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች እና አውዶች ምርቃት ሲከወን÷ የመራቂዎቹ እና የተመራቂዎቹ አካላዊ እንቅስቃሴቀዎች፣ ቃላዊ ምልልሶች፣ የእጅ መዳፍን እንዲሁም ጉልበትን የመሳም ተግባራት ባህላዊ መሰረት አላቸው።

እንደ ጥናቱ ሃሳብ ከሆነ÷ ምርቃት ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታም አለው። ምርቃት አዱኛዊ እርከንን በማሳደግ በኩል አበርክቶ ያለው ሲሆን የሰው ልጅ በተለያዩ መቅሰፍቶች የአልጋ ቁራኛ ከሆነ በቤተሰብና ሀገር ላይ ጫና ይፈጥራል። ማህበረሰብን ከሚያናጋ አሉታዊ ክስተት ለመሰወር “ጤና ይስጥህ ፣ ውለህ ግባ፣ ክፉ አያግኝህ …” በማለት መመረቃቸው÷ ሰው ከበሽታ እና ከመቅሰፍት ከተሰወረ÷ በተለያዩ ሙያዎች ላይ ስለሚሳተፍ ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እና ለሀገር ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትን ያመጣል።

ምርቃት የተለያዩ ትዕምርታዊ ፋይዳዎችም አሉት። በባህል ውስጥ ያሉ ትዕምርታዊ እሳቤዎች በቋንቋ እና በቁስ ተምሳሌታዊ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ። ትዕምርቶቹን በመተንተን የተለያዩ ሰብዓዊ ጉዳዮችን ማምረት ይቻላል።

አጥኚው በወሎ አካባቢ የሚከወነውን “እርፎ መረባ” እንደ አብነት ወስዶ ሲያስረዳ፦
“የእርፎ መረባ እናቶች ተቀምጠው ከወገባቸው በታች አንድ ነጭ ጋቢ በጋራ መልበሳቸው÷ አንድም ነጭ ጋቢ የብሩህ ተስፋ፣ የደስታ እና የስኬት ተምሳሌትነት ገላጭ ሆኖ ይቀርባል። አንድም አንድ ጋቢ በጋራ መልበሳቸው ማህበረሰቡ ያለውን አብሮነት፣ አንድነት እና ውህደት አመልካች ትዕምርት አለው” ብሏል።

ሌላኛው ሳይጠቀስ የማይታለፈው የምርቃት አስተዳደራዊ ጠቀሜታ ነው። በማህበረሰቡ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ እና እርቁም መሰረቱ የጸና እንዲሆን ምርቃት ሚና አለው። ልጆች ቤተሰቦቻቸውን፣ በዕድሜ የሚበልጧቸውን ወንድም እና እህቶቻቸውን … እንዲያከብሩ እንዲሁም በዕድሜ ለገፉ ሽማግሌዎች የመታዘዝ መንፈስን እንዲያዳብሩ ያስችላል። በተጨማሪም ሰላማዊ አካባቢ እንዲኖር እና አጎራባች አካባቢዎች የወንድማማችነትን መንፈስ እንዲገነቡ፣ ሰዎች ለሰዎች መልካም ተግባራትን በመፈፀም የተረጋጋ ማህበረሰብ እና ሀገር እንዲኖር የማስቻል ሚና አለው ተብሎ ይታመናል።

የተመረቁ ሰዎች ለህግ እና ለደንብ ተገዢ በመሆን ሀገራዊ ልማትን ያፋጥናሉ። እንዲሁም ደካሞችን የሚረዱ፣ ለሰዎች ቅን የሚያስቡ፣ ለቂም በቀልና ለአመፅ የማይነሳሱ ይልቁንም ለፍቅር እና ለአንድነት ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች እንዲኖሩ የማስቻል አቅም አለው።

ስለሆነም በመልካም ጠባያችን እና በመልካም ምግባራችን ከሚመረቁት ወገን እንድንሆን÷ በጎ ምግባርን ገንዘባችን ልናደርግ ይገባል።