ጉባኤው ለአፍሪካ

ጉባኤው ለአፍሪካ

በፈረኦን ደበበ

ሰሞኑን የቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ በእንግዶች አሸብርቃ ከርማለች፡፡ ታዳሚዎች ከሁሉም የዓለም ክፍሎች የተሰበሰቡ ሲሆን ዓላማውም በሀገሪቱ በሥራ ላይ ስላለው “ቤልት ኤንድ ሮድ” ስለተሰኘው የመንገድ ልማት ፕሮጀክት ለመነጋገር ነው፡፡ ብዙ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታ ያለው ፕሮጀክት በሀገሪቱ ይፋ ከተደረገበት 10 ዓመታት ያለፉ ሲሆን ከአሜሪካ ጋር ቻይና ለገባችበት ፉክክርም እንደ አንድ ማጠንጠኛ ይታያል፡፡

በተለይ ምዕራባዊያን ፕሮጀክቱን በከፍተኛ ጥርጣሬና ነቀፌታ ስለሚመለከቱት፡፡ በተወሳሰበው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ ሲል የቆየው ይህ በእንግሊዝኛው “ቤልት ኤንድ ሮድ” የተባለው ፕሮጀክት ሰሞኑን 10ኛ ዓመት የመመስረቻ በዓሉ በርካታ እንግዶች በተገኙበት ተከብሮለታል፡፡ ታዳሚዎችም አብዛኛው የአፍሪካ እና ታዳጊ ሀገራት መሪዎች መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሀገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን ጨምሮ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶና እስከ 150 የሚሆኑ መሪዎች 30 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችን እንዲሁም ተሳትፈውበታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 የተጸነሰው ፕሮጀክቱ ኤሲያ፣ አፍሪካና አውሮፓ አህጉራትን በንግድና በመሠረተ-ልማት ለማገናኘት ተብሎ ሲሆን አጋጣሚውም ለአፍሪካዊያን ታላቅ ዕድል ነው ብዙዎች ልማትን በማስፋፋት ለህዝቦቻቸው አመቺ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር ስለሚፈልጉ፡፡ ስያሜውን ቀድሞ በአካባቢው በሚታወቁ የንግድ ዕቃዎችና መንገዶች ላይ አድርጎ የተነሳው ፕሮጀክት 10ኛ ዓመት መመሥረቻ በዓሉን ዘንድሮ ያከበረ ሲሆን ዝግጅቱም በአንድ በኩል ቻይና ከአሜሪካ ጋር የገባችበትን የንግድ ውድድር ያሳብቃል ምክንያቱም በርካታ የዓለም ሀገራት በአሁኑ ጊዜ በንግድ ወይም በፖለቲካ ጎራ ክፍፍል ውስጥ፤ ስለገቡ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደቦች፣ የኃይል ማመንጫዎችና ከፍተኛ የባቡር ሀዲዶች ግንባታ ላይ ትኩረት የሚያደርገው ፕሮጀክት በቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ሽፒንግ የበላይ ጠባቂነት የሚመራና ለግንባታዎች የሚሆነውን ገንዘብም ያቀርባል፡፡ ምንም እንኳን ምዕራባዊያን ፕሮጀክቱ በታዳጊ ሀገራት ላይ የዕዳ ጫና ያደርሳል በማለት እያብጠለጠሉት ቢሆንም፡፡ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም በተመለከተም አፍሪካ ኒውስ የተባለው የዜና ምንጭ እንዳስታወቀው በተለይ እንደ ታይላንድና ካምቦዲያ በመሣሰሉ የምሥራቅ ኤሲያ ሀገራት የተገነባው ፍጥነት መንገድ ቀደም ሲል ረጅም ቀናት ይወስድ የነበረውን ጊዜ በማሳጠር ለህዝቡ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ምንም እንኳን ከግንባታ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ የፕሮጀክቶች በጊዜ ያለመጠናቀቅና ተያይዞ የሚመጣው የዕዳ ጫና አሳሳቢ ነው ቢባልም።

ሆኖም ከዚህ ጋር ተያይዞ አስተያየታቸውን የሰጡት የቻይና ሬንሚን ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ወንግ ይው ለየት ያለ ሀሳብ አላቸው፤ ፕሮጀክቱ ከደንበኞች ጋር ትብብራዊ አሠራርን እንደሚያጎለብትና ለዘመናዊነት ተመራጭ መሆኑን በማስታወቅ። ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ. በ2017 እና በ2019 የተካሄዱ ጉባኤዎችን ተከትሎ ዘንድሮ የተካሄደው ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን ከተመሠረተበት 10ኛ ዓመት ጋርም በአንድነት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ምክንያቱም ዓለም በከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ ስለምትገኝ፡፡ የጉባኤው ሌላው ባህሪ በቅርቡ ቡድን-77 የተባሉ ታዳጊ ሀገራትና ቻይና በጋራ ምክክር ባደረጉበት ማግሥት መከናወኑ ሲሆን በቅርቡ ቱርክዬ ካዘጋጀችው ከአፍሪካ-ቱርክ የውይይት መድረክ ጋርም ይያያዛል ሁለቱም ሀገራት ለአፍሪካ ወዳጅና የልማት አጋር እንደመሆናቸው፡፡

በጉባኤው ከተሳተፉ የአፍሪካ ሀገራት መካከል የሀገራችን ኢትዮጵያና ኬንያ መሪዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ ፍላጎቶቻቸውንም በግልጽ አሳይተዋል፡፡ ጊዜው ሀገራችን ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ ካደረገችው የልማት አጀንዳ ጋርም ሲታይ ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት የባህር በር ሳይኖራት ስለቆየች ካለው ሀገራዊ ገቢ አብዛኛውን ለወደብ ክፍያ በማዋል – ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገች በመሆኑ፡፡ ሀገራችንን ባለፉት ዓመታት ካጋጠሙ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች ጋርም ካገናኘነው ሁኔታው በግልጽ ይታያል፤ ምክንያቱም ብዙ መሰናክሎች ስላጋጠሙ። እነዚህ ችግሮች ተጨማሪ ጉዳት በማያደርሱበት አግባብ መፍትሄ ለመስጠት አስቦ መንግሥት የያዘው አቋም እጅግ የሚደነቅና ድጋፍም ሊደረግለት የሚገባ ነው።

ስለሆነም የወደብ አማራጮችን ለማግኘት መንግሥት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ምክክር በማድረግ መነሳቱ ለሀገራችን ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ በተለይ አሁን በጂቡቲ ላይ የተመሠረተው የወጪ ንግዳችን ወደ ሰሜን በኩል ብዙ የክልል አካባቢዎችን ማዳረስ ስለማይችል ወደ ቀይ ባህር መመልከታችን ለልማትም ሆነ ዘላቂ ለሆነ ሀገራዊ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከቻይናው አቻቸው ሊ ቋንግ ጋር የተናጠል ውይይት ያደረጉት፡፡ በዚህን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ኢትዮጵያና ቻይና የረጅም ጊዜ ወዳጅ ሀገራት ናቸው፡፡ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በልማትና በተለያዩ ዘርፎች ተባብረው ለመሥራት የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትርም በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሀገራቸው የረጅም ጊዜ ወዳጅ መሆኗን አውስተው ትብብሩን ማጠናከርም የመንግሥታቸው ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመረጃ ምንጫችን እንዳስታወቀው ከሆነ የኬንያ መንግሥት ልዑካንም ከጉባኤው ጎን ለጎን የተናጠል ውይይት በማድረግ ከስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን ያቀረቡት ጥያቄ ግን ከእኛ ይለያል በብድርና በዕዳ አመላለስ ላይ ትኩረት ስለሚያደርግ፡፡ በአንድ ወቅት የምሥራቅ አፍሪካ ምጣኔ ሀብት ማዕከል ተብላ የምትታወቀው ሀገር በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና ውስጥ ስትሆን ችግሩ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታየው የኃይል አቅርቦት፣ ምጣኔ ሀብትና አየር ንብረት ለውጥ ጋርም ሲታይ ውስብስብ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህንን ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ያለው የሀገሪቱ መንግሥት አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመንደፍ ሁሉ አልቻለም፡፡ ስለሆነም ችግሩን ለመቅረፍ ከዋና አበዳሪዋ ጋር ውይይት ለማድረግ ተገደዋል፤ ተጨማሪ ብድር ለማግኘትም ሆነ ያለውን የብድር አመላለስ ሁኔታውን ለማሻሻል፡፡

ዓለም በተለያዩ ፖለቲካዊ እሳቤዎችና ወታደራዊ ጎራዎች ተከፋፍላ ባለችበት በአሁኑ ሰዓት የተከፈው 10ኛው “የቤልት ኤንድ ሮድ” ጉባኤ ታሪካዊ ሚና የተጣለበት ነው ለማለት እንችላላን፤ ምክንያቱም ለብዙዎች ተስፋና ዕድል ማሳየት ስለቻለ፡፡ ሀገራት በመነጋገርና በመመካከር የጋራ ችግሮቻቸውን መቅረፍ የሚያስችል አጋጣሚም ስለፈጠረ፡፡

ሆኖም ከምዕራባዊያን ጋር የገባችውን እሰጥ አገባ ለማስቀረት ግን ቻይና በብድር ፖሊሲዋ ማሻሻል የሚገባት ነጥብ ሊኖር ይችላል ምክንያቱም ብዙ ወዳጆችን ለማግኘት የያዘቸው ዕቅድ በገንዘብ አቅርቦቷ መነሻ እንዳይስተጓጎል ለማድረግ፡፡ እየታዩ ያሉ የፕሮጀክት አፈጻፀም መጓተቶችን ሁሉ በማስቀረት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችላት::