በገነት ደጉ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ ሰንበቶ አባባ ይባላሉ፡፡ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ እና ምክትል የቢሮ ኃላፊ ናቸው። ከባለሙያነት እስከ አመራርነት ለ12 ዓመታት ያህል አገልግለዋል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ፣ አገልግሎቱን ለማዘመን እና የህዝብ ቅሬታዎችን ለመመለስ በሚሰሩ ስራዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ንጋት፡– ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን!
አቶ ሰንበቶ፡– እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ!
ንጋት፡– ከትውውቅ እና ከስራ ድርሻዎ እንጀምር?
አቶ ሰንበቶ፡– ትምህርቴን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በገቨርናንስ ኤንድ ደቨሎፕመንት ስተዲ የትምህርት ክፍል ተከታትዬ ነው የጨረስኩት። የሁለተኛ ድግሪዬን እዛው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድምንስትሬሽን ነው ያጠናቀቅኩት፡፡
ከትምህርቴ በኋላ ለአንድ ዓመት ከግማሽ በከምባታ ዞን ዳምቦያ ወረዳ በባለሙያነት ካገለገልኩ በኋላ በቀድሞው አጠራር የወጣቶች ሊግ ኃላፊ ሆኜ ነበር ሹመት የተሰጠኝ፡፡
በኋላም በቀድሞው ከምባታና ጠምባሮ ዞን የወጣቶች ሊግ ኃላፊ በመሆን ለሶስት ዓመታት ያህል አገልግያለሁ፡፡ የከተማ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ በመሆን እያገለገልኩ በቀድሞው ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል መንግስት የክልሉ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ በመሆን በ2012 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ሹመት አግኝቼ ወደ ሀዋሳ ገባሁ፡፡
በዚሁ ዘርፍ እያገለገልኩ ክልሉ በህዝቦች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አራት ክልል ሆኖ ሲደራጅ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወጣቶች ሊግ ኃላፊ በመሆን ለአንድ ዓመት ያህል አገልግያለሁ፡፡
አሁን ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንገዶችና የትራንስፖርት ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ዘርፍ ኃላፊ በመሆን እያገለገልኩ ነው፡፡ አጠቃላይ ከባለሙያነት እስከ አመራርነት ለ12 ዓመታት ያህል አገልግያለሁ፡፡
ንጋት፡– እንደ ማዕከላዊ ኢትየጵያ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ምን ይመስላል?
አቶ ሰንበቶ፡– ትራንስፖርት ሴክተር በባህሪው አገልግሎት ሰጪ ተቋም ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ደግሞ ዘርፈ ብዙ ፍላጎቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ፍላጎቶች በአስተሳሰብም እንዲሁም በተግባር የሚገለፁ ናቸው፡፡
ከፍላጎቶቹ አንፃር አንዱ አገልግሎት መስጠት የምንጀምርበት ቦታ መናኸሪያ ነው። መናኸሪያዎቻችን የነበራቸው ስያሜ ብቻም ሳይሆን አጠቃላይ ይንፀባረቅ የነበረውን ስያሜውም በጣም ፀያፍ ነው የነበረው፡፡
አንድ ሰው እንኳን የመጨረሻ ስድብ ሊሰድብ ሲፈልግ የመናኸሪያ ልጅ እስከመባል ድረስ ነበር። መናኸሪያዎቻችንን በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥሩ እይታ አልነበረም፡፡ ስለዚህም አንዱ እና ማስተካከል የነበረብን የመናኸሪያ ሪፎርም ብለን ነበር፡፡ ለዚህም የመናኸሪያ ሪፎርም ምንድነው? የሚለውን ፓኬጅ የሆኑ ጉዳዮችን ለይተን ለሁሉም መናኸሪያዎች ስታንዳርዶችን አውርደን ማቅረብ ብቻም ሳይሆን የሚከታተል ግብረሃይል ኖሮት በየጊዜው እየተገመገመ እና እየታረመ እንዲሄድ የማድረግ ሰፋፊ ስራዎችን ሰርተናል፡፡
ይህን ለማድረግ የተገደድነው እዚያው አካባቢ ያሉት በአስተሳሰብም በተግባርም የሚገለፁ ችግሮች ስለነበሩ ነው፡፡ የእነዚህም ችግሮች ተዋኒያኖች አሉ፡፡ እነዚህን ተዋኒያኖችን እንዴት ነው ማረም ያለብን የሚለውን በመወያየት ወሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡ እነሱ ካልታረሙ ህዝቡ በመናኸሪያ ውስጥ ፍትሀዊ አገልግሎት ማግኘት አይችልም ነበር፡፡
ህብረተሰባችን ክብሩ ሳይነካ ተሳፋሪም የትም ይሂድ ከየትም ይምጣ ክብሩ ተጠብቆለት የሚፈልገውን አገልግሎት ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ማግኘት እንዲችል የሚያደርጉ አሰራሮች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡
በዚህም ችግሮችን መለየት በራሱ ግብ ስላልሆነ እንዴት እናርማቸው ብለን ወደ ታች ግብ ጥለን አውርደናል፡፡ በመናኸሪያ አካባቢ ሶስተኛ ወገን የምንለው ያለ ሲሆን ቀይ ለባሽ የሚባለው በጣም የትራንስፖርት ስርዓቱን የሚረብሽ፣ ተሳፋሪዎችን ለእንግልት የሚዳርግ አካል ነው፡፡
ስለዚህም ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለይም በ2017 ዓ.ም በስፋት የሄድንበት ጉዳይ እነዚህን የሚያውኩ አካላትን ማስወገድ ነው፡፡ ስለዚህም የመናኸሪያ ሪፎርም ላይ አገልግሎቱን የሚሰጡት በማህበር ተደራጅተው ተጠያቂ ለመሆን ኃላፊነትን የሚወሰድ አካል ኖሮት አገልግሎት የሚሰጡ ጫኚ እና አውራጆች እንዲቀጠሩ የማድረግ ስራ አንዱ ነበር፡፡
ከዚያ ውጪ ተሳፋሪዎቻችን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ወደ መናኸሪያ ሲገቡ የት ይሄዳሉ የሚለውን በግልጽ ማግኘት እንዲችሉ መነሻዎቻቸውን በታፔላ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ሌላው የስምሪት ባለሙያዎቻችን መናኸሪያ ውስጥ ቁጭ ብለው የስምሪት መስመሮችን ተከፋፍለው አገልግሎቱን እንዲያሳልጡ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ይህንንም በክላስተር ይዘው የሚያስተባብሩ ባለሙያዎች ከማሰማራት ጀምሮ መናኸሪያዎቻችን ተጠያቂነት ባላቸው ሰዎች ብቻ እንዲመሩ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡ በመናኸሪያ ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ከገንዘብ ንክኪ ነፃ እንዲሆን የማድረግ ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡
ተሳፋሪው እና በመናኸሪያ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች በካሽ ገንዘብ እንዳይገናኙ የማድረግ ስራዎች በስፋት ሰርተናል፡፡ በዚህም ጫኚና አውራጆች ገንዘብ ከተሳፋሪ እንዳይወስዱ እና ማህበራቸው እንዲከፍላቸው ተደርጓል፡፡
ህብረተሰቡም የያዙት ዕቃ ያስከፍላል ወይስ አያስከፍልም የሚለውን ሚዛን እንዲለዩ የማድረግ ስራ በሁሉም መናኸሪያዎቻችን የሚዛን አገልግሎት እንዲኖር የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በደመነፍስ የሚሰራ ስራ ህብረተሰቡን ዛሬም ለእንግልት እየዳረገ ነው፡፡ በዚህም መልክ አገልግሎቱ እንዲሰጥ እየተደረገ ነው፡፡
ሌላው ተሳፋሪ የሚያገኘው አገልግሎት የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም የተነሳ ተሽከርካሪዎች ላይ የቅድመ ስምሪት ምርመራ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ለስምሪት ብቁ ያልሆነ ተሽከርካሪ ሰርቪስ አግኝቶ ብቁ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ወደዚህ አሰራር የሚመጣበት ሲሆን ካልሆነ ግን ከስምሪት ታግዶ የሚቆይበት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡
በዚህም ራሱን ችሎ የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ዳይሬክቶሬት የስራ ክፍል አለው፡፡ ይህንንም ስራ በሁሉም መናኸሪያዎቻችን ተግባራት እንዲቀጥሉ የማድረግ ስራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ይህም ተሳፋሪው ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለው የትራንስፖርት ስምሪት ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ በመናኸሪያ ውስጥ አገልግሎቱን የሚሰጡ አካላት በሙሉ ራሳቸውን የሚገልጽ እና የየትኛው ስምሪት አካል እንደሆኑ የሚያሳይ ሽርጥ፣ ባጅ እንዲሁም ዩኒፎርም እንዲኖራቸው ማድረግ ደግሞ ሌላው ስራ ነው፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው ወደ መናኸሪያ ሲገባ በመናኸሪያ ውስጥ አገልግሎት ሰጪ መሆኑን አውቆ ነው የሚፈልገውን አገልግሎት ማግኘት ያለበት፡፡ ስለዚህም ስራው ሰላማዊ፣ ከእንግልት ነፃ እና ፍትሀዊ አገልግሎት የሚገኝበት እንዲሆንና ሰው ክብሩ ተጠብቆለት የስምሪት አገልግሎት የሚያገኝበት ቦታ ነው ማለት ነው፡፡
ንጋት፡- ከአጎራባች ክልሎች ጋር አብሮ የመስራት ልምዶች አሉ ይሆን?
አቶ ሰንበቶ፡- ከመንገድ ደህንነት ስራዎቻችን ውስጥ ትልቁ ትኩረት የምንሰጠው አደጋን መከላከል ነው፡፡ አደጋ እንዲቀንስ ከማድረግ አኳያ አንዱ ቁጥጥር ስራችን ነው፡፡ በዚህ ስራ የተሰማሩ ሰዎች ሁሉ የግንዛቤ ችግር ያለባቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ ሰልጥነው የወጡ ሰዎች ናቸው። የተፈቀዱ እና የተከለከሉ ነገሮችን የሚያውቁ ናቸው፡፡ ግን ስግብግብነት ያለበት ዘርፍ ነው። በተለይም አንድ ጉዞ በሰላም እገባለሁ ሳይሆን ስንቴ እመላለስበታለሁ የሚል ስግብግብነት የሚታይበት ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ቁጥጥራችን ጥብቅ እንዲሆን የሚያደርግ ነው፡፡
ይህም ስግብግብነት ከፍትሀዊነት ጋር አብሮ የሚገናኝ አይደለም፡፡ ስለዚህም የፍጥነት ወሰንን ጥሶ የተገኘው አካል በአግባቡ ተጠያቂ የሚሆንበት በተለይም ደንብ 557/2016 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የወረደ ደንብ በጣም አስተማሪ ስለሆነ ይህን ደንብ በክልላችን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የጋራ አድርገን ወጥ አቋም ይዘን ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን፡፡
ስራውንም በየጊዜው በጋራ እንገመግማለን። ክልል ላይ የጋራ ግብረ ሀይል አለን፡፡ ከፖሊስ ኮሚሽንና ከፀጥታ መዋቅር ጋር በመሆን በጋራ እንሰራለን፡፡ ጉድለቶችንም ለመሙላት ጥረቶች እያደረግን እንገኛለን፡፡
ሌላው ስግብግብነት ከመናኸሪያም ከወጡ በኋላም ትርፍ መጫንና ከታሪፍ በላይ ሌላ ጭማሪ ገንዘብ መጠየቅ ነው፡፡
ባለሀብቱም ማግኘት ያለበትን ጥቅም ብቻ ነው ማግኘት ያለበት፡፡ እንደ ተቋም የእኛ ስራ ሚዛናዊነትን እና አሰራርን ማስጠበቅ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ አሁንም ስግብግብ አሽከርካሪዎች አሉ፡፡ እነዚህን አሽከርካሪዎች መንገድ ላይ በምናደርገው ቁጥጥር ለማረም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በአብዛኛው ቀንሷል፡፡ ነገር ግን አሁንም በቀጣይ የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡
ይሄም መታረም ስላለበት እንደ ቢሮ አቋም ተወስዶ የቢሮ ባለሙያ ጭምር በአመራር የተመራ ቡድን እየወጣ መንገዶች ላይ ድንገተኛ እና መደበኛ ቁጥጥር በማድረግ በርካታ አሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡
ይህንንም የሚያግዝ ስራ እንደ ቢሮ ነፃ የስልክ መስመር ተከፍቷል፡፡ 8934 ነፃ የስልክ መስመራችን ነው፡፡ 24 ሰዓት አገልግሎት ይሰጣል። ከ12 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ነው፡፡ በዚህም ሰዓት ማንኛውም በትራንስፖርት ስራ ላይ የገጠማቸው ችግሮች ካሉ በነፃ የስልክ መስመር መደወል ይቻላል፡፡ ከአጎራባች ክልሎችም ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡
ለዚህም የሚያመች ፌደራል መንግስት ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሰራ ሲሆን ክልሎች ከክልሎች ጋር በጋራ የሚሰሩትንም ጉዳዮች ለይቶ ሰጥቶናል፡፡ በእነዚህ ጉዳች ዙሪያ ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ጋር ተቀናጅተን እየሰራን ሲሆን ግንኙነታችን በተለይም ከደቡብ ኢትዮጵያ እና ከኦሮሚያ ጋር ነው፡፡
ስለዚህም በሚያዋስኑን አካባቢዎች ባሉት ጉዳይ ላይ በጋራ እየሰራን ችግሮችን ለማረም ጥረት እያደረግን ነው ያለነው፡፡ ግን ደግሞ በቀጣይ የሚሰሩ ቀሪ ስራዎች አሉ፡፡ ገና ወደ ፍፁምነት እና ወደ ምንፈልገው ደረጃ አልመጣንም፤ አሁንም የህዝብ እሮሮ ቀጥሏል፡፡
ንጋት፡– የተሽከርካሪዎች ሙሉ ጤንነት፣ የታሪፍ እና የአሽከርካሪዎች ስነ–ምግባር ችግሮችን ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሰንበቶ፡– ተቆጣጣሪዎቻችን በተግባር የሚገለፁ ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ሲሆኑ ይህንንም ለመስበር በቅንጅት ሰፋፊ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ በዚህም ከ48 በላይ በሚሆኑ ባለሙያዎቻችን ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ከ200 በላይ በሆኑ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የገቡትን ባለፉት ወራት እርምጃ የመውሰድ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም ከስምሪት እስከማገድ ድረስ የተወሰዱ እርምጃዎች ነበሩ፡፡ በዚህም ደረጃ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
በክልሉ ወደ 27 የሚደርሱ መናኸሪያዎቻችንን የኢ-ትኬቲንግ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገናል። ስለዚህ የመንገድ ቁጥጥራችንም ላይ በኢ-ትኬቲንግ ነው የተሳፈረው፣ ከኢ-ትኬቲንግ ጣቢያ ውጪ ሌላ አካል ገንዘብ አልጠየቃቸውም የሚል የቁጥጥር ስራዎችን ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው፡፡
ከዚህም ሌላ በመንገድ ላይ የተሽከርካሪ ሙሉ ጤንነት፣ ቦሎ፣ ደረጃውን እንዲሁም ሶስተኛ ወገን የታደሰለት ስለመሆኑ በትኩረት ይሰራል። ከዚህም ውጪ መንገድ ላይ በአግባቡ ቀበቶ ማድረጋቸውን ቁጥጥር ይደረጋል፡፡ አደንዣዥ እጽ ወስደው የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠርም ከፍተኛ ጥረቶችን እያደረግን እንገኛለን፡፡ በእዚህ ላይ በተለይም በራዳር ጭምር መንገዶችን ታሳቢ ያደረገ ቁጥጥሮችን እንደ ክልል እያደረግን እንገኛለን፡፡
ንጋት፡– አደጋን ከመቀነስ አንፃር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችስ እንዴት ይገለፃሉ?
አቶ ሰንበቶ፡– አደጋን ከመቀነስ አንፃር የትምህርትና ስልጠና ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ከትምህርትና ስልጠና ስራዎቻችን አንፃር አንዱ ተቋማት ላይ ትኩረት አድርገን የምንሰራው ስራ አለ፡፡ በተለይ መንገድ ዳር ያሉ ትምህርት ቤቶች፣ በቀበሌያት ያለውን ስራ ከቀበሌ ኮሚቴ በትምህርት ቤት ክበባትን ከማዋቀር ጀምሮ የማጠናከር ስራዎችን በስፋት እየሄድንበት ነው፡፡
በትምህርት ቤቶች በሰንደቅ ዓላማ ስነስርዓት ወቅት ለሁሉም ተማሪዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች እንደዚሁም ክበባት ላይ ለክበባት አመራሮችና አባሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ሲመለሱም የመንገዱን ግራ ጠርዝ ይዘው እንዲመለሱ የማድረግ እና ዜብራ ብቻ እንዲያቋርጡ የማድረግ ትምህርትና ስልጠና ስራዎች እየሰጠን እንገኛለን፡፡
በተለይም የተለያዩ ሁነቶችን ምክንያት በማድረግ ለዓብነትም የተለያዩ ሀይማኖታዊ እና የዘመን መለወጫ በዓላት እንዲሁም የአደባባይ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የትራፊክ ፖሊሶች፣ የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎችና አመራሮቻች ጭምር ገብተው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚሰጥበት ሲሆን በገበያ ቀናት ከገጠር አካባቢ የሚመጡትን የመንገዱን ጠርዝ ይዘው እንዲሄዱ እና በዜብራ እንዲያቋርጡ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም በዘንድሮ ዓመት በ1ኛ ሩብ ዓመት ወደ 21 በመቶ አደጋ የቀነስን ሲሆን ይህም አደጋው ዜሮ እስካልሆነ ድረስ የለም ማለት አይቻልም። በዚህም ዘርፍ አንድ ሰው እንኳን መሞት የለበትም፡፡ ከዚህም አኳያ ቀሪ ስራዎች አሉ። ከቀሪ ስራዎቻችን አኳያ የቱ ጋር ነው ጉድለት ያለብን ብለን ለይተን እያረምን ነው፡፡
ሌላው የትራንስፖርት ሴክተር አገልግሎት የሚሰጥበት የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ላይ ነው። በተለይም በማሰልጠኛ አካባቢ ያለው መንጃ ፈቃድ አሰጣጥን በተመለከተ በክልላችን 35 የማሰልጠኛ ተቋማት ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ በአግባቡ ስታንዳርዱን ያሟላ፣ የተወሰነ ጉድለት ያለበት እንዲሁም ችግር ውስጥ ያለ ብለን ለይተን ማሰልጠኛ ተቋሞቻችንን በድጋፍ እያገዝን እንገኛለን፡፡
ባለፈው ዓመት አንዳንድ ተቋማት ከስታንዳርድ በታች በመሆናቸው ፈቃድ የመሰረዝ ስራዎች ተሰርቶ ችግሮቻቸውን አርመው ከተወሰነ ጊዜ ዕገዳ በኋላ ወደ ተግባር የተመለሱ ማሰልጠኛዎች አሉ፡፡ አደጋ አድራሽና ስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ሰዎች መነሻቸው ማሰልጠኛ ነው፡፡ ማሰልጠኛዎቻችን ሚናቸውን በአግባቡ ከመወጣት አንፃር በአዋጅ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው ነው፡፡
በዚህም በድጋፋችን እያረምን ነው የምንሄደው፡፡ ይህንን ማረም ብቻ ሳይሆን ወቅቱ የዲጂታል ዘመን ነው፡፡ አሁንም ማኗዋል በሆነ መንገድ እነዚህን ችግሮች ማረም አንችልም፡፡ ምክንያቱም ውስብስብ ስለሆነ ወደ ዲጂታል እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች እንደ ጅምር የተጀመሩ ሲሆን መንጃ ፈቃድ የማስተዳደር ስርዓትን ወደ ዲጂታል ለመቀየር እንደ ቢሮ ከአልሚ ተቋማት ጋር ውል ተፈራርመናል፡፡ በቀጣይም ወደ ተግባር የምንገባ ነው የሚሆነው። ሰልጣኞቻችን በአግባቡ ተከታትለው ነው የሚመረቁት የሚለውን በትኩረት እየሰራን ነው፡፡ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ሐሰተኛ የመሆን አካሄዶች አሉ፡፡
በመንጃ ፈቃድ ተቋማት ሰዎች ሳይማሩ የመንጃ ፈቃድ የሚወስዱበት አግባብ መኖር የለበትም፡፡ እሱን ማረም የሚችል ስራ እንደ ቢሮ እየሰራን ነው ያለነው፡፡ ሌላው በማሰልጠኛ በትክክል ተምሮ የወጣ ሰው ካለ አደጋዎች በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንሱ የሚችልበት ሁኔታዎች እንዳሉ ያሳያል፡፡ በዚህም ማሰልጠኛዎች በአግባቡ ሚናቸውን እንዲወጡ የማድረግ ስራዎችን እንሰራለን፡፡ ከዚያ ውጪ እንደ ቢሮ የምንሰጣቸው አገልግሎቶች አሉ፡፡
ንጋት፡- በተቋማችሁ መንጃ ፈቃድ ለመውሰድ እንግልት እና ምልልስ እንዳለ በስፋት ይወራል። ይህንንም ለመቀነስ ወይም ለማስተካከል ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሰንበቶ፡- በቢሮ ደረጃ የመንጃ ፈቃድ ህትመት የሚሰጠው በእኛ ቢሮ ነው። በዚህም የሰዎች ምልልስ እንዳይኖር ባሉበት ሆነው በቴክኖሎጂ ሁሉም ነገር ተጠናቆላቸው ለመውሰድ ብቻ የሚመጡበት አሰራር ለመዘርጋት ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡ ከዚያም ውጪ ታርጋ፣ ኢንተርናሽናል የመንጃ ፈቃድ አገልግሎት፣ እንዲሁም ስም ዝውውር አገልግሎቶች በአብዛኛው ወደታች ውክልና ተሰጥቶአቸው በዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ደረጃ እየተሰጡ ነው ያሉት፡፡
ወደ እኛ ተቋም ማንኛውም ሰው ከመጣ ከ10 እስከ 15 ደቂቃ የፈለገውን አገልግሎት አግኝቶ መመለስ አለበት የሚለውን ስታንዳርድ አስቀምጠን ነው እየሰራን ያለው፡፡ የመንጃ ፈቃድ ጥያቄ እኛ ጋር ሲቀርብ ሁሉም ነገር ተሟልቶለት ከመጣ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ አትመን እየሰጠን ነው፡፡
ስለዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋም እንደመሆኑ መጠን መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለይተን በተቋሙ ያሉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምንድናቸው? ብለን ለይተንና አቅደን እነዚህን ማን ምን ይስራ የሚለውን ለሚመለከተው አካል ስራ ቆጥረን ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ በአጠቃላይ ፍትሀዊ፣ ግልጽና ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ትልቁ ራዕያችን ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን እየሰራን ነው፡፡
ንጋት፡– ከትራፊክ ፖሊሶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ብልሹ አሰራሮችን እና ከመናኸሪያ በኋላ ተጨማሪ ገንዘብ ከሚጠይቁ አሽከርካሪዎች ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ሰንበቶ፡– ከኢ-ትኬቲንግ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር ወደ ድምጽ ቀይረናል፡፡ በሁሉም መናኸሪያዎቻችን ላይ በሚኒ ሚዲያ እንዲተላለፍ አድርገናል፡፡ አሽከርካሪ እና ተሳፋሪዎች መብትና ግዴታ፣ የስምሪት ባለሙያዎች ማድረግና አለማድረግ ያለባቸው፣ ረዳቶች ማድረግ ያለባቸው ምንድነው? የሚለውን የመናኸሪያ ማህበረሰብ የምንላቸው ደንቡ ላይ የተቀመጠውን ወደ ድምጽ ቀይረን ለሁሉም መናኸሪያዎች አሰራጭተናል፡፡ ይህንን ህገ-ወጥነት መከላከል የምንችለው በግንዛቤ ነው፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መተጋገዝ ሲችል ነውና በዚህም ደረጃ ስለምናምን ነው፡፡
ሌላው ኢ-ትኬቲንግ ስላስጀመርን ሁሉም ነገር ፍፁም ነው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን መጀመሩ ብዙ ለውጥ አምጥቷል፡፡ ግን አሁንም ስግብግቦች አሉ፡፡ እንደ ቢሮም ችግሩ እንዳለ ገምግመናል፡፡ በድንገተኛ ቁጥጥር ስምሪት የሚሰጠውን አካል መንገድ ላይ የሚቆጣጠረው አካል ችግር ፈቺ ቁጥጥር ያደርጋል ወይ? የህብረተሰቡን ችግር ያዳምጣል ወይ? መውጫ ከማንበብ ያለፈ ገባ ብሎ አስተማሪ እርምጃ እየወሰደ ህብረተሰቡን ከችግር እየታደገ ነው ወይ? የሚለውን ግምገማ ስናደርግ ቀሪ ነገሮች እንዳሉ ታዝበናል፡፡
የጀማመርናቸው ስራዎች አሉ፡፡ ማስደንገጥ ጀምረናል፡፡ እርምጃ የተወሰደባቸው ትራፊክ ፖሊሶች አሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ችግሮች ውስጥ ገብተው የተቀጡ የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎችም ጭምር አሉ፡፡ በኦፕሬሽን ስራዎች ሰርተን ያስጠየቅናቸው የትራፊክ ፖሊሶች አሉ። በተመሳሳይም የሚመሰገኑ የትራፊክ ፖሊሶች እና የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች አሉ፡፡ አንዳንዶችም ኪሳቸውን ብቻ ታሳቢ አድርገው የሚሰሩ አሉ፡፡ እነዚህንም በተለያየ መንገድ ህብረተሰቡ ሲያጋልጥ እኛም በመንገድ ደህንነት ኦፕሬሽን በሚሰሩ ስራዎች መረጃ የተሟላ ስናገኝ እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡
እንደ ከዚህ ቀደም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመቀየር ሳይሆን በትራፊክ ፖሊሶችና በመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ስራዎች የጀመርንበት አግባብ አለ፡፡ በዚህም ደረጃ በሚታይ መልኩ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አሉ፡፡ ህብረተሰቡም ህገ-ወጦችን በማጋለጥ ማገዝ አለበት፡፡ ትርፍ ከፍሎ ሲያበቃ አልከፈልኩም ይላል፡፡ ህገ-ወጥነትን በጋራ ነው መከላከል የምንችለው፡፡
ትራንስፖርት በባህሪው ወሰን ተሻጋሪ ስለሆነ ሰው ካልተጋገዘ ተዋኒያኑ ብዙ ስለሆነ ህብረተሰቡ ከጎናችን እንዲሆን ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ በእኛ ደረጃ ግን አሰራሮችን ተግባራዊ ባላደረገ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማራ አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ እጅግ በጣም ወጥ አቋም ይዘን ክትትልና ቁጥጥር እያደረግን እንገኛለን። ያልተሻገርነው ችግር ነው የሚለው ቢያዝ መልካም ነው፡፡
ሌላው በመናኸሪያ ውስጥም የሚተባበሩ አካላት አሉ፡፡ እነዚህም አካላት ከመናኸሪያ እንዲወገዱ የማድረግ እና ተመጣጣኝ እርምጃ የመውሰድ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ ሰዎች ባጠፉት ጥፋት ልክ እንዲታረሙ እያደረግን ነው፡፡ እኛ ቀንሷል ብለን ነው እንጂ የገመገምነው ችግሩ ግን አላለቀም፡፡ እኛ ችግሩ እልባት እንዲያገኝና ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ህብረተሰቡ እንዲያገኝ ቢሮው አሁንም ከፍተኛ የቤት ስራ አለበት። ይህንን የቤት ስራችንን ለመጨረስ በየጊዜው ክትትል እያደረግን እንገኛለን፡፡
ንጋት፡– ነፃ የስልክ መስመር በተሽከርካሪዎች ላይ ተለጥፏል፤ አገልግሎቱስ ፈጣን እና ህብረተሰቡ የሚያውቀው ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ሰንበቶ፡– ከነፃ ስልክ ተደራሽነት አንፃር በመናኸሪያዎች በሚኒ ሚዲያ ነው የሚነገረው። በኢ-ትኬቲንግ አገልግሎት ትኬት ላይ 8934 ነፃ የስልክ መስመር እንዲገባ ተደርጓል፡፡ የትኬቱ አንዱ አካል ነው፡፡
ሌላው በተሽከርካሪዎች እና በቢሮው በሚታይበት ቦታ እንዲለጠፍ ተደርጓል፡፡ ይህም ክትትል ማድረግን ይጠይቃል፡፡ ተሽከርካሪዎች በራሳቸው ላይ የሚመጣውን ነገር ለጥፈው መንቀሳቀስ ስለማይፈልጉ ክትትል ማድረግ ይጠይቃል፡፡ በተሰራው ስራ የሚመለከተው ባለሙያ ለአመራሮች መልእክት እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ እዛው ቀጥቶ ላለው ተቆጣጣሪ መረጃ ይሰጣል፡፡
በተጨማሪም የወሰደውን እርምጃ ጭምር ሪፖርት ይደርጋል ማለት ነው፡፡ አንዳንዱ ተሸከርካሪውን ጭምር ባለበት እስከማሰር ደርሰናል፡፡ ተሳፋሪ እንዳይቸገር በምትኩ ሌላ ተሽከርካሪ የመመደብ ስራዎች ይሰራሉ፡፡
በዚህም በቂ ሳይሆን በየጊዜው ምላሽ እና መፍትሔ የመስጠትና ቁጥጥር ማድረግን የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በየቀኑ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡
ንጋት፡– ለህብረተሰቡ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት?
አቶ ሰንበቶ፡– የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት ሰጪ ነው፡፡ ብዙ ተዋኒያን ያሉበት ስለሆነ አንዱም ተዋናይ ህብረተሰቡ ራሱ ስለሆነ ተሳፋሪው በክልላችን ባሉት በየትኛውም መናኸሪያዎች አገልግሎት ሲሰጥ መብቱን በአግባቡ መተግበር አለበት፡፡
ሌላው ህገ-ወጦች ሊገጥሙት ይችላሉ፡፡ ህገ-ወጦች ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉና ትርፍ የሚጭኑ ከገጠማቸው ለህግ አካል ማጋለጥና በነፃ ስልክ መስመራችን ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበረን፡፡ ህገ-ወጥነትን በጋራ መከላከል ያለብን ስለሆነ ማለት ነው፡፡
የመንገድ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ደህንነት ስለሆኑ በጋራ በቅንጅት በሚሰሩት ስራዎች በህግ የተሰጣቸውን ስራ በአግባቡ በማይወጣው ሀይል ላይ እርምጃ የመውሰድና የማጋለጥ ስራዎች ላይ እንዲሁም ለሚጠየቁ ጥያቄዎችም ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ቢተባበሩን መልካም ነው፡፡
ቀጥሎም ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላት ከማዕከል ጀምሮ የህዝብ አገልግሎት ስለሆነ የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ህዝባችንን ከእንግልት እንታደግ መልዕክቴ ነው፡፡
ንጋት፡– ስለነበረን ቆይታ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሰንበቶ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

More Stories
“የቤተሰቦቼ ፍቅር ለስኬት አብቅቶኛል” – መምህር አንዱዓለም አያሌው
አክሳሪው- ትርፍ!
የምርቃት በረከቶች