ትዝታ ፥ ትዝታ

በአንዱዓለም ሰለሞን

(አጭር ልበ ወለድ)

የትምህርት ቤት ትዝታዎቼ ገፆች ሲገለጡ ከማስታውሳቸው ሰዎች አንዱ አበበ ነው። አበበ ማንያዘዋል የክፍል አለቃችን ነበር። ዕድሜው ከእኛ ይበልጣል፡፡ አስተሳሰቡ ግን ከአብዛኞቻችን የሚያንስ ይመስለኛል፡፡ በትምህርቱ ሰነፍ መሆኑን በጉልበቱ ሊያካክስ የሚሞክር፣ አምባገነን ወጣት ልትሉት ትችላላችሁ፡፡

አይ አቤ፤ አሁን የት ይሆን ያለው? ምንስ ሆኖ ይሆን? መቼም ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ከሆነ አምባገነን ካድሬ እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም፡፡

መምህር በማይኖረን ክፍለ ጊዜ የክፍል ሀላፊ መምህራችን አቤን፡-

“አንድ ሰው እንዳይረብሽ! የረበሸውን ስም ፅፈህ ትሰጠኛለህ!” በማለት አስጠንቅቀውት ይሄዳሉ፡፡ ይህ ለአቤ ደስታው ነው።

አጋጣሚውን ተጠቅሞ ያሻውን ያደርጋል። የፈለገውን ይቀጣል፡፡ …

አንድ ቀን እንደተለመደው የክፍል ሀላፊ መምህራችንን ትዕዛዝ በደስታ ተቀብሎ በመምጣት ብላክ ቦርዱ ፊት ለፊት ቆመና፡-

“የሂሳብ አስተማሪያችን የለም፡፡ አንድ ሰው ትንፍሽ እንዳይል! ዝም ብላችሁ ማንበብ ትችላላችሁ!” በማለት አስጠነቀቀን፡፡ እኔ ለሂሳብ ትምህርት ብዙም ፍቅር ስለሌለኝ መምህሩ በመቅረታቸው በውስጤ ደስ አለኝ። ትዝታ ደግሞ አበበ እልሁን የሚወጣበትን አጋጣሚ በማግኘቱ የሚከፋት ይመስለኛል፡፡

ትዝታ ከክፍላችን ቆንጆ ተማሪዎች አንዷ ነች፡፡ እኔ በዚህ ሀሳብ ባልስማማም አንዳንዶች እንደውም ከትምህርት ቤታችን ጭምር በማለት ውበቷን ያጎሉታል፡፡

ረጅም፣ ቀጭን፣ ልክ እንደ ሰንደቅ መስቀያ ዓይነት ቁመት ያላት፣ በቀይና በጠይም መካከል ያለ የፊት ገጽታዋ ላይ እንቁ የመሰሉ ዓይኖቿ ብርሀን የሚረጩ፣ በጥርሶቿ ውበት ፈገግታዋ ልክ የሀምሌን ደመና ሰንጥቃ ብቅ እንደምትል ጸሀይ የሚናፈቅ ቆንጅዬ ልጅ ነች፡፡ ጸጉሯ ዛሬ ላይ ቢሆን “ሂውማን ሄር” በመሸጥ ብቻ ለመተዳደር የሚያስችላት፣ ከትከሻዋ አልፎ ወገቧ ላይ የተኛ፣ እርግት ያለች፣ ጭምት ነች – ትዝታ፡፡

አበበ ትዝታን ይወዳታል፡፡ እሷ ግን አትወደውም፡፡ እናም አቤ ጠምዷታል። በወቅቱ ያልገባኝ፣ “ለአቅመ ፍቅር” ስደርስ የተረዳሁት ነገር አቤ ለትዝታ የፍቅር ደብዳቤ ጽፎላት (ይቅርታ አጽፎላት በሚለው ይታረም) እሷ ግን ዘግታዋለች፡፡ ይህ እንዳልኳችሁ ዘግይቼ የገባኝ ብቻም ሳይሆን የሆነ ጊዜ ጓደኞቿ ሲያሙ ሰማሁ ብሎ ጓደኛዬ የነገረኝ መረጃ ጭምር ነው፡፡

በዚህ የተነሳ አቤ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የክፍል አለቃነቱን ተጠቅሞ ትዝታ ላይ ቂሙን ይወጣባታል፡፡ የረባሽ ተማሪዎችን ስም ሲጽፍ የትዝታን ስም የዘለለበት ቀን ትዝ አይለኝም፡፡ ትዝታ፤ ምንም እንኳ ዝምተኛ ልጅ ብትሆንም ሰነፍ ከሚባሉት ተማሪዎች ውስጥ የምትመደብ በመሆኑ መምህራችንም የአቤን ኢ-ፍትሀዊነትና የትዝታን ብሶት እንዳያስተውሉት አድርጓቸዋል፡፡

አስር ደቂቃም ሳንቆይ አቤ ከተቀመጠበት ተነስቶ ከብላክቦርዱ ፊት ቆመና፡-

“ዝም በሉ ስላችሁ አልሰማ አላችሁ አይደል! ግድየለም እያንዳንድሽ ዋጋሽን ታገኛለሽ! ዝም ብዬ የተቀመጥኩ መስሎሻል። ስም እየፃፍኩ ነበር! ስንታየሁ፣ መነን፣ ትዝታ፣ መላኩ፣ ሜሮን፣ አንድነት፣ ሚሊዮን አሁን ስማችሁን የፃፍኳችሁ ናችሁ፡፡ ዝም ካላላችሁ ይቀጥላል!” ብሎ ወደ መቀመጫው ተመለሰ።

አቤ ይህን ያለን ትዝታን እያየ ነበር። የሌሎቻችንን ስም ሲጠራ እንኳ ዐይኖቹን እሷ ላይ ተክሎ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር የትዝታን ድምፅ ፈፅሞ ስላልሰማሁ ረባሽ መባሏ አስገርሞኛል፡፡ ለትዝታ ሲሆን የመረበሽ ትርጉሙ ሌላ ይሆናል፡፡ ይህ የአምባገነኑ የክፍላችን አለቃ፣ የአበበ ማን ያዘዋል ያልተፃፈ ህግ ነው፡፡

የሂሳብ ክፍለ ጊዜ ከመጠናቀቁ አምስት ደቂቃ አስቀድሞ የክፍል ሃላፊ መምህራችን መጡና አቤን፡-

“የረበሸ ተማሪ አለ!?” በማለት ጠየቁት።

“ብዙም የለም፡፡ እነዚህ ግን፤ በቃ ከአቅሜ በላይ ሆነዋል!” አለና የረባሽ ተማሪዎችን ስም የፃፈበትን ብጣሽ ወረቀት አቀበላቸው፡፡

መምህራችን የረባሽ ተማሪዎችን ስም ጠሩ፡፡ ስማቸው የተጠራ ተማሪዎችም ከተቀመጡበት ተነስተው ብላክ ቦርዱ ፊት ለፊት ቆሙ፡፡ ከዚያም መምህራችን እጃቸውን አዘርግተው አምስት አምስት ጊዜ በያዙት አርጩሜ ገረፏቸው፡፡

ከትዝታ በስተቀር ሁሉም ተማሪዎች እጃቸውን እያፈራረቁ ነበር የተገረፉት፡፡ ትዝታ ግን የቀኝ እጇን እንደዘረጋች ጥርሷን ነክሳ አበበን እያየች ተገረፈች፡፡ ስትገረፍ ፊቷ ቅጭም አይልም፡፡ ግን ደግሞ እልህና ንዴት ይነበብባታል፡፡

ይህ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል አብሬያቸው ከተማርኳቸው ተማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው የትዝታ ታሪክ ነው፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ስገባ ትዝታ ሚኒስትሪ ከወደቁት የክፍላችን ተማሪዎች መካከል ነበረች፡፡ ከዚያ በኋላ ስለ እሷ የሰማሁት ነገር አልነበረም፡፡ ተገናኝተንም አናውቅም፡፡

ከአስር ዓመታት በኋላ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብቼና ተመርቄ ሌላ ከተማ ስራ ይዤ እየኖርኩ ነበር። አንድ ቀን ድንገት መንገድ ላይ ከአንድ ሴት ጋር ተገጣጠምን፡፡ ሳያት የሆነ ነገር ተሰማኝ። ድንገት ከአፌ አንድ ቃል ወጣ፡-

“ ትዝታ !? ”

“አዎ ነኝ፡፡ አንተ ግን ማነህ?!” አለች ትክ ብላ እየተመለከተችኝ፡፡

“አላወቅሽኝም!?” አልኳት እኔም ትኩር ብዬ እያየኋት፡፡

የእሷ እኔን ካለማወቅ በላይ የእኔ እሷን አለመርሳት ያስገርማል፡፡ ፍፁም ተለውጣለች። ያቺ የመስከረም አደይ የመሰለች ልጅ የጠወለገ የመቃብር ላይ አበባ መስላለች፡፡ ፊቷ በማድያት ወይቦ፣ እንደ ሀር ፈትል ወገቧ ላይ ይዘናፈል የነበረው ፀጉሯ ለዛውን አጥቶ ፈፅሞ ሌላ ሰው መስላለች፡፡

“ወይኔ በእናትህ አላስታወስኩህም ይቅርታ”አለች ፈገግ ለማለት እየሞከረች። የውብ ፊቷ ድምቀት የነበረው ፈገግታዋ ደብዝዟል፡፡

ስሜን ነግሬ የት እንደምንተዋወቅ አስታወስኳት፡፡

“አንተ! በጣም ይገርማል! ምንድነው ይሄ ሁሉ ሽበት!?”አለች የጥጥ ማሳ የመሰለውን ፀጉሬን ትኩር ብላ እየተመለከተች፡፡

“ያው እንግዲህ ጊዜውም እኮ ሄዷል፣ ልጅም መጣ፣ የእኛ ልጅነትም አበቃ ማለት ነው” አልኳት እየሳቅሁ፡፡

“እንዴት አወከኝ ግን?” አለች፡፡ በደበዘዘ ፈገግታዋ ውስጥ የሆነ ስሜት ያስተዋልኩ መሰለኝ፡፡

“የልጅነት ነገሮቼን አልረሳም”አልኳት፡፡

“በጣም ተለውጫለሁ ብዬ ነው፤ ትንሽ ያመኝ ነበር”

“ምነው?”

“እዚህ ጋ ያበጠ ነገር አለ” አለች የቀኝ ጎኗን በእጇ እየነካች፡፡

“በህክምና ብዙም ለውጥ አላገኘሁም። እስኪ አሁን ደግሞ ፀበል እሞክራለሁ ብያለሁ፡፡ እግዚአብሔር ያውቃል! እሱ ምን ይሳነዋል!”

በእውነት በጣም ነው ውስጤ የተረበሸው፤ አሳዘነችኝ፡፡

 “ልክ ነሽ ለሱ የሚሳነው ነገር የለም፡፡ እሱን ተስፋ ማድረግ ነው” አልኳት፡፡ ምናለ፤ አንቺ ሴት እምነትሽ አድኖሻል … ቢላት ብዬ በውስጤ እየተመኘሁ፡፡

“እውነት ነው እሱ ያውቃል፡፡ ፀበል ለመሄድ አስቤ ነበር፡፡ ትንሽ እቤት የማስተካክላቸው ነገሮች ስላሉ ነው የቆየሁት። እ… ከባለቤቴ ጋር ትንሽ ጥሩ አይደለንም፡፡ ከመጀመሪያ ልጄ ጋር አይስማሙም፡፡ በቅርቡ እንደውም ተጣልተው ልጄ ከቤት ወጥቶ ነው ያለው፡፡ ከህመሜ በላይ የጨነቀኝ ይሄ ነገር ነው፡፡ እሱ ወደ ቤት ከተመለሰልኝ እሄዳለሁ” አለችኝ፡፡

ሁኔታዋ ልቤን ነካው፡፡ ያቺ ዝምተኛዋ፣ ያቺ የክፍላችን ቆንጆዋ ትዝታ ከዓመታት በኋላ እንዲህ ተጎሳቁላ አግኝቻት ብሶቷንና የቤቷን ገመና ስታወጋኝ ሳይ ከልብ አዘንኩኝ፡፡

“አይዞሽ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጊ። ሁሉም ነገር ይስተካላል” ከዚህ ውጪ የምለው አልነበረም፡፡

“እሺ፤ አመሰግናለሁ” አለችና እዚህ ነው የምትኖረው?” ስትል ጠየቀችኝ፡፡

“አዎ አንድ አስር ዓመት ሆነኝ፡፡”

“በቃ እንገናኛለን፤ ስልክ ግን ለጊዜው የለኝም፤ ጠፍቶብኛል፡፡ ያንተን ቁጥር ፅፈህ ስጠኝና እኔ እደውላለሁ”

ከኪሴ ስኪሪፕቶ እና ወረቀት አውጥቼ ቁጥሬን ፅፌ ሰጠኋት፡፡ ተሰነባብተን ተለያየን።

ምን ዐይነት ዕድል ነው? የአንዳንድ ሰው ዕጣ ፈንታ ግን ይገርማል፡፡ ተማሪ ሳለች አምባገነን የክፍል አለቃ ሲያሰቃያት ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ አምባገነን ባል ገጠማት፡፡

አምባገነኖች የክፍል አለቃ ሆኑ፣ ባል ሆኑ፣ በአጠቃላይ ውጤቱ አንድና አንድ ነው፡፡ የሰዎችን ተስፋ መንጠቅ፣ ውበትን ማጠውለግ፣ ህይወትን ለዛና ጣዕም ማሳጣት።

ስለ አበበ ማንያዘዋል ማሰብ ጀመርኩ። …