“የቤተሰቦቼ ፍቅር ለስኬት አብቅቶኛል” – መምህር አንዱዓለም አያሌው

“የቤተሰቦቼ ፍቅር ለስኬት አብቅቶኛል” – መምህር አንዱዓለም አያሌው

በሙናጃ ጃቢር

አካል ጉዳተኞች በተለያዩ  ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ ሲወድቁ ይታያል፡፡ እንደ አካል ጉዳታቸው የተለያዩ መሰናክሎች ይገጥማቸዋል፡፡ ስለሆነም እነዚህን   ችግሮቻቸውን የሚጋራቸው ቤተሰብ ያሻቸዋል፡፡

የተለየ የቤተሰብ እገዛ ያላቸው አካል ጉዳተኞች የሚደርሱባቸውን  ተግዳሮቶች ተቋቁመው  ከማህበረሰቡ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ ልጅ ያላቸው ቤተሰቦች ልጃቸውን ፍቅር ሰጥተው ካሰቡበት ግብ የማድረስ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በልጅነታቸው  አካል ጉዳት ከገጠማቸው  ቤተሰብ ሕይወታቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው የተለያዩ የስነ ልቦና መፅሐፍቶችን በማንበብ ሊያስገነዝቧቸው ግድ ይላል፡፡ ከልጅነት ጀምሮ ግንዛቤው ካላቸው  የስነልቦና ችግር አይገጥማቸውም፡፡ ቢገጥማቸውም  በቀላሉ መቋቋም ይችላሉ፡፡

ቤተሰብ ተገቢውን እርዳታ ካላደረጉላቸው ግን ከባድ ችግር ሊደርስባቸው ይችላል፤ የደረሰባቸውም በርካቶች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለልጆቻቸው መሰዋትዕነት ከፍለው ፍቅርን በተግባር ያሳዩ ወላጆች ደግሞ ብዙዎች ናቸው። የዛሬ ችያለው አምድ ባለተሞክሯችንም  “ቤተሰቦቼ  ፍቅርን በተግባር ያሳዩኝ” ናቸው ሲል ያሞግሳቸዋል።

እንደመታደል ሆኖ ተገቢውን  የቤተሠብ ድጋፍ ስላገኘ ዛሬ ላይ ለደረሰበት ስኬት አብቅቶታል፡፡ ቤተሰቦቹ ከራሳቸው አልፈው ለልጃቸው በጣም  ይጨነቁ  ነበር፡፡ ጉዳቱ ለህይወቱ የሚያሰጋ ቢሆን ቤተሰቦቹ ጥሩ ህክምና እንዲያገኝ ስላደረጉት ከሞት ታድገውታል፡፡

መምህር አንዱዓለም አያሌው ይባላል። ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ኮተቤ ተብሎ በሚጠራ ሰፈር ነው፡፡ አሁን ላይ ሀላባ ቁሊቶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የሀላባ ዞን የእጅ እና የእግር ጉዳት ያለባቸው አካል ጉዳተኞች ማህበር ሰብሳቢ እና አጠቃላይ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት ፀሀፊ ነው፡፡ 

ትምህርቱን ከ1ኛ እሰከ 12ኛ ክፍል በአዲስ አበባ ኮከበፅባህ ትምህርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ከዚያም ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ውጤት አምጥቶ ጅማ ዩኒቨርስቲ በታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል በድግሪ ፕሮግራም የተከታተለ ሲሆን በተመሳሳይ ከጅማ ዩኒቨርስቲ በታሪክ እና ቅርስ አሰተዳደር ትምህርት ክፍል 2ኛ ድግሪውን ይዟል፡፡ 

አካል ጉዳት የገጠመው የ2ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ነበር፡፡ ድንገት ከልጆች ጋር ሲጫወት ወድቆ ግራ እግሩ ላይ ጉዳት ደረሰበት፡፡ ጉዳቱ በወቅቱ በህይወት የመቆየት እና ያለመቆየት ጉዳይ ቢሆንም በቤተሰቦቹ  ጥረት  ጥሩ ህክምና አግኝቶ ለውጥ እንዳመጣ  ቤተሰብ የነገረውን አጫውቶናል፡፡

 “ከሌሎቹ  አካል ጉዳተኞች  አንፃር ሲታይ አሁን ላይ  የኔ  ጉዳት  ቀላል ነው፡፡ ዕድሜ ለወላጆቼ  በህክምና ባልረዳ ኖሮ ጉዳቱ ከዚህ የከፋ ይሆንብኝ ነበር” ሲል  የቤተሰቦቹን ጥንካሬ እና ለእርሱ ስኬት ዋጋ መክፈላቸው ነበር የገለፀልን፡፡ 

ለረዥም ጊዜ በህመም ተሰቃይቶ እንዳሳለፈ ነግሮናል፡፡ በዚህ የተነሳ ለ1ዓመት ያክል ትምህርቱን ለማቋረጥ መገደዱን ነው የሚናገረው፡፡

“ልጅ ስለነበርኩ የስነልቦና ጫናውን በውል  አልተረዳሁም ነበር፡፡  አድጌ ስረዳው  ቤተሰቦቼ ግን ለእኔ ሲሉ  ብዙ ዋጋ ከፍለዋል።

“በትምህርቴ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ጎበዝ የመሆኔ ሚስጥር ደግሞ ቤተሰቦቼ ናቸው፡፡ ትምህርቴ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር በብዙ መልኩ ይረዱኝ ነበር፡፡

“በእድሜ ከፍ እያልኩ ስመጣ  በስነልቦና እንዳልጎዳ የተለያዩ የስነልቦና መጽሐፍቶችን እንዳነብ ያግዙኝ ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዳደርግ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ አስገብተውኝም ነበር።  የእችላለሁን ስሜት እንዳዳብር ቤተሰቦቼ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡

“የኔ ተሞክሮ ለብዙ አካል ጉዳተኞች አስተማሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ተፅኖ ሲደርስባቸው አያለሁ፡፡ እንደመታደል ሆኖ ከቤተሰቦቼ ልዩ እንክብካቤ ስለነበረኝ ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ አብዛኛው አካል ጉዳተኛ በተለይ ገጠሩ ክፍል ያለው ማህበረሰብ ለአካል ጉዳተኛ የሚሰጠው አመለካከት ዝቅተኛ ነው፡፡ ምንም አይነት እንክብካቤ ድጋፍ አይደረግላቸውም፡፡ በደረሰባቸው ጉዳት ታክመው በቀላሉ መዳን ሲችሉ ለከፋ ጉዳት ሲጋለጡ ይታያል፡፡

“አካል ጉዳተኛ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን  በርግጥ መፈተኑ የማይቀር ነው ለምን አሜሪካ ውስጥ አይኖሩም፡፡ ግን ግንዛቤው ያላቸው አካል ጉዳተኞች ለከፋ ችግር አይጋለጡም፡፡

“ሌሎች አካል ጉዳተኞች ያለፉ ታሪኮቻቸውን ስሰማ በጣም አዝናለሁ፡፡ በክፋት ወይም ደግሞ ባለማወቅ ከሚመጣው ተፅኖ የቤተሰብ እገዛ ስላልተለየኝ ነፃ  የሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ቤተሰቦቼ አድጌ ተጽዕኖ እንዳይደርስብኝ ራሴን እንዳዘጋጅ ረድቶኛል።

“የሚሰማኝን በልበ ሙሉነት የምናገር  ሰው ነኝ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች እኔን ለማሸማቀቅ ሲፈለጉ አካል ጉዳተኝነቴን ጠቅሰው ነው፡፡ እኔ ግን ከቤተሰብ የወረስኩት ማንነት ስላለ አንገቴን አያስደፉኝም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ቤተሰቦቼን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡ አንገቴን ቀና እድርጌ እንድሄድ ስላደረጉኝ፡፡  በስራ ወይም  በሀሳብ እኔን መብለጥ ስላማይችሉ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ አካል ጉዳተኝነቴን ጠቅሰው ሊያሸማቅቁኝ ይሞክራሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሰዎች የአዕምሮ ጉዳተኛ እንደሆኑ ነው የሚሰማኝ፡፡

“የማህበረሰቡ አመለካከት ሰዎች ካሰቡበት ዓላማ እንዳይደርሱ፤ የጀመሩትን ውጥን እንዳያሳኩ  እንቅፋት የመሆን በቂ ሀይል አለው፡፡ ብዙዎች ተሸማቀዋል፣ አልቅሰዋል፣ አንገት ደፍተዋል እና ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡

“እኔ ላይ ተፅዕኖ አልፈጠረም ማለት ብዙዎች ላይ አልፈጠረም ማለት አይደለም።እኔ ያለኝን ልምድ እንጂ የምናገረው የማህበረሰቡ አመለካከት ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ቢጠና ሞራል የሚነካ ነው፡፡

“መልካም አመለካከት ያላቸው ሰዎችን ደግሞ ፈጣሪ አያሳጣም፡፡ የሥራ ባልደረቦቼ አንዳንድ የማደርገውን ነገር ሲያዩ በጣም ይደነቃሉ፡፡ የተለየ ችሎታ እንዳለኝ አድርገው የሚያዩኝ ሰዎች አሉ፡፡ ይሄ አመለካከት የተፈጠረው በልጅነቴ የቤተሰብ ፍቅር ስንቅ ሆኖኝ ነው ለዚህ የበቃሁት” ብሏል፡፡ 

ሥራ የጀመረው በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤት ለ1 ዓመት አስተምሯል። በመቀጠል ወደ ሀላባ ቁሊቶ ከተማ መጥቶ ሀላባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የታሪክ መምህር ሆኖ ለ16 ዓመታት አገልግሏል፡፡

በአጠቃላይ በታሪክ መምህርነት ወደ 20 ዓመታት አገልግሏል፡፡ በቆይታው ብዙ ዶክተሮችን፣ ፓይለቶችን፣ መምህራንን እና ዳኞችን አፍርቷል፡፡

“ለስኬት የበቁ ተማሪዎቼን  በስም እንኳን ጠቅሼ መጨረስ አልችልም ለፍሬ በቅተዋል በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ ምንም እንኳን አንድ ክፍለ ጊዜ ብቻ የማስተምራቸው ቢሆንም በጥቂቱም አሻራዬን አሳርፌያለሁ ብዬ አስባለው፡፡

“እድሉን ካገኘሁ ወደፊት ፒኤችዲ የመማር ዕቅድ አለኝ፡፡ ብዙ ጊዜ ወደ ጥበቡ አደላላሁ እሱንም አጠናክሬ መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ በተጨማሪም ወጎችን፣ ግጥሞችን እና አጫጭር መነባነቦችን የመፃፍ ህልም አለኝ” ብሏል፡፡

“ለሌሎች አካል ጉዳተኞች የማስተላልፈው መልክት፡- አካል ጉዳተኞች ይነስም ይብዛም  ህልማቸውን በጭንቅላታቸው በግልፅ ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ ላስቀመጡት ራዕይ ደግሞ እንዴት ማሳካት እንዳለባቸው ያስቡ፣ ይመራመሩ፣ አዋቂ ሰዎችን ያማክሩ እና ያንብቡ ከዚያም ለሚገጥማቸው ለየትኛውም መሰናክል በልበ ሙሉነት ምላሽ መስጠት አለባቸው፡፡ በፍፁም አልቃሻ መሆን የለባቸውም፡፡ የሰዎች የተዛባ አመለካከት የሚፈጠረው ከአለማወቅ እንደሆነ ተረድተው ከአላማቸው ምንም ወደ ኋላ እንዳይሉ እመክራቸዋለሁ” ብሏል፡፡

እዚህ ደረጃ እንድደርስ ለረዱኝ ቤተሰቦቼ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳቸው፡፡ ቀጥሎ በኔ አመል አሁን ላለሁበት ሰብአዊ ማንነት  በቆይታዬ ውስጥ ሳስከፋቸው ተረድተውኝ ዝም ላሉኝ አካላት ሁሉ ምስጋናዬ ባሉበት ይድረሳቸው ሲል መልካም የዋሉለትን ሰዎች አመስግኗል፡፡