የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 መከበሩ የእርስ በርስ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን በ20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ የተሳተፉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ልዑካን አባላት ተናገሩ

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 መከበሩ የእርስ በርስ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን በ20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ የተሳተፉ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ልዑካን አባላት ተናገሩ

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ላደረገላቸው ደመቅ አቀባበልና የሀዲያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ላደረገላቸው የእራት ግብዣም ምስጋና አቅርበዋል።

“ዲሞክራሲያዊ መግባባት፤ ለኅብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለ20ኛ ጊዜ በተከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ የታደሙ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የመጡ ልዑካን አባላት እንዳሉት፤ በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ ኢትዮጵያዊያን የእርስ በእርስ አንድነታችንን እንድናጠናክር የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የጥንት አያቶቻችን በአድዋ ድል ያደረጉበት ዋነኛ ምስጢር በጋራ በጠላት ላይ መዝመታቸዉ መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የአሁኑ ትዉልድም በህዳሴ ግድብ ላይ አንድነቱን ማሳያቱን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ይፋ ማድረጓን ጠቁመው፤ ይህ የሚሳካው ግን ኢትዮጵያዊያን የሚለያዩ ጉዳዮችን በመተው ለሀገር ብልጽግና በጋራ ርብርብ ስናደርግ ነው ብለዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የልማት ፍላጎት ለማሟላት የባህር በር ጉዳይ ወሳኝ በመሆኑ መንግስት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተናግረዋል።

በዓሉ በሚከበርበት አካባቢዎች ላይ የመሠረተ ልማት ስራዎች እንዲስፋፉ እያደረገ መሆኑንና ይህም ለቱሪዝም ዘርፍ ያለዉ አበርክቶ ከፍተኛ እንደሆነም የልዑካን አባላቱ ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምንም እንኳ ክልል ሆኖ ከተደራጀ አጭር ጊዜ ቢሆንም ለእንግዶች አቀባበል ባደረገው ዝግጅት መደነቃቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የተደረገላቸው አቀባበል እና የሀዲያ ዞንና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ያደረገላቸው የእራት ግብዣም እጅግ አስደሳች መሆኑን ገልጸው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።

21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በኦሮሚያ ክልል በጅማ ከተማ የሚከበር ይሆናል፡፡

ዘጋቢ፡ ተሻለ ከበደ – ከሆሣዕና ጣቢያችን