ፊርማዬ÷ ከቀዳሚዎቹ አንዷ
በይበልጣል ጫኔ
“ድንገተኛው ከዬ ነፍስ አውጪ መንጠቆ
የዘመኑ ጉጠት ካልጨረሰው ነጥቆ
ታዛቢ ካልታጣ ሁሉ ተሟጦ አልቆ
ፅፋለሁ ምናለ
ተርፎ አንባቢ ታለ”
ይኼ ግጥም የፊርማዬ አለሙ ነው። በ1989 ዓ.ም “ታዛቢ ካልታጣ” በሚል ርዕስ የቋጠረችው። ፊርማዬ አለሙ ማናት? ያላችሁ እንደሆነ÷ ቀጥሎ የምናነሳው ሃሳብ ስለሷ ነው። ከቀዳሚዎቿ መካከል ስለምትጠቀሰው÷ ከአፃፃፏ ባልተለየ መድረክ አያያዟ እና አቀራረቧ ስለሚመስጠው÷ ድንቅ ገጣሚ። ከዚያ በፊት ግን ጥቂት ስለ ግጥም …
“ስነ ግጥም በእጅጉ ጥንታዊነት እንዳለው የሚነገርለት የኪነ ጥበብ ዘር ነው። የሰው ልጆች ለብዙ ዘመናት ደስታና ሃዘናቸውን፣ ምኞት ፍላጎታቸውን፣ የአኗኗር ሁኔታቸውንና ልዩ ልዩ ገጠመኞቻቸውን በማንጎራጎር እና በማዜም ሲገልፁበት ኖረዋል”÷ ይኼ ሃሳብ የስነ ፅሁፍ መሰረታውያን ከሚለው የተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው መፅሐፍ የተቀነጨበ ነው።
ስነ ግጥም የተለየ ስጦታ ነው። በጥቂቱ ብዙ የሚሉበት። ለስሜት ቅርብ የሆነ። አንድም ውበትን የሚኩሉበት። ወዲህም በምስጢር የሚራቀቁበት። ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) በአንድ ወቅት ስለ ግጥም ሲናገር፦
“ግጥም መፃፍ እንባ ይፈልጋል። ጣር ይፈልጋል። ህመም ይፈልጋል። ከታመመው ጋር አብረህ የምትታመም ከሆነ፣ ከሚያለቅሰው ጋር አብረህ የምታረግድ ከሆነ፣ ከሚደሰተው ጋር አብረህ የምትደሰት ከሆነ … ህብረተሰቡን ህዝቡን በደንብ የምታውቀው ከሆነ ጥሩ ፀሐፊ ይወጣሃል” ብሎ ነበር።
ይኼ ስጦታ ለብዙዎች የታደለ አይደለም። አንዳንዶች ባለ ተሰጥኦ ቢሆኑ እንኳን÷ በዚህ ልክ የሰውን ህመም ታመው÷ አሊያም በሌሎች ደስታ ስቀው ብዕር የሚያነሱቱ÷ ከልባቸው ፅፈው ለልባችን የሚደርሱቱ ጥቂቶች ናቸው። ከነዚያ ጥቂቶቹ መካከል ደግሞ ፊርማዬ አለሙ አንዷ ናት።
ፊርማዬ የሚለው ስሟ÷ ወደዚህ ምድር ከመጣችበት መንገድ የተቀዳ ነው። ለድፍን 11 ዓመታት የዘለቀው የእናት እና አባቷ ትዳር÷ በልጅ እጦት ክፉኛ ተፈትኗል። ይኼ ሁነትም ለአባቷ እና በአባቷ በኩል ላሉት ቤተሰቦች ሁሉ አምነው የሚቀበሉት አልሆን አለ። በዚህም ምክንያት ቤታቸው በብስጭት እና ብሶት በመሞላቱ÷ ሽማግሌ ሰብስበው ሰማንያቸውን ቀደዱ።
ባልና ሚስቱ በየፈርጃቸው የህይወት መንገዳቸውን ከመጀመራቸው በፊት ግን÷ አንድ ሽማግሌ የተለየ ሃሳብ አቀረቡ። ወትሮም መለያየታቸው ያልተዋጠላቸው ሽማግሌ “ፊርማው ቢቀደድም ለተወሰነ ጊዜ አብራችሁ ቆዩ” አሏቸው።
ከብዙ ክርክር በኋላ የማይመስል ነገር ሆነ። ፊርማቸውን የቀደዱት ባልና ሚስት÷ ለተወሰኑ ጊዜያት አብረው ለመቀጠል ተስማሙ። እንዲህ በሆነ በሦስተኛው ሳምንት ላይ÷ እናቷ በማህፀናቸው አንዳች ህይወት እንደተቋጠረ ተሰማቸው። የተሰማቸውን ለባለቤታቸው ሲያማክሩ÷ ባል በጥርጣሬ መንፈስ አቅማሙ።
“ሽል ከሆነ ይገፋል …” እንዲሉ÷ ውሎ ሲያድር የእናቷ የመፀነስ ምልክት ታየ። ውሉ ከፈረሰ በኋላ ሴት ልጅ ተወለደች። የተቀደደው ፊርማ በልጅቱ መወለድ ፀንቷልና÷ ፊርማዬ አሏት። ፊርማዬ አለሙ የተወለደችው በሆሳዕና ከተማ÷ ልዩ ስሙ ዘበኛ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጥቅምት 27 ቀን1950 ዓ.ም ነበር።
በፍፁም ወልደማርያም በተሰናዳው “ያልተዘመረላቸው” መፅሐፍ ላይ የሰፈረው ታሪኳ እንደሚያስረዳው÷ ፊርማዬ አለሙ ዕድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ÷ ከአባቷ ጋር ወደ ግንቢቹ በመሄድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን መከታተል ጀመረች።
ግንቢቹ ከተማ ላይ ከስድስተኛ ክፍል በላይ ባለመኖሩም÷ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው ወደ ትውልድ ቀዬዋ ሆሳዕና ተመልሳ ነው። በ1966 ዓ.ም የ12ኛ ክፍልን ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈትና ጥሩ ውጤት በማምጣቷ÷ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመደበች። ዩኒቨርስቲ በተመደበችበት ዓመት የዕድገት በህብረት የዕውቀት እና የሥራ ዘመቻ ስለነበር÷ በዚህም ምክንያት ትምህርት በመቋረጡ ዩኒቨርስቲ መግባት አልቻለችም ነበር።
ፊርማዬ አለሙ የወቅቱን ሀገር አቀፍ ዘመቻ ተቀላቅላ የመጀመሪያ ዙር ዘማች በመሆን ወደ ሐረር ሄደች። የገጠማት ድንገተኛ ህመም ግን በዚያ እንድትቆይ አላስቻላትም። ስለሆነም ወደ ግንቢቹ ተመለሰች።
ፊርማዬ ወደ ግንቢቹ ስትመለስ ያላሰበችው ሆነ። የአባቷ ንብረት በመንግስት ተወርሶ ቤተሰቦቿ እየተጉላሉ ነበር። በዚህ ያዘነችው ፊርማዬ ቤተሰቦቿን ለመርዳት ወደ ስራው ዓለም ተቀላቀለች። በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ድርጅት ውስጥ በሂሳብ ሰራተኝነት ተቀጠረች።
ፊርማዬ የዚያን ዘመን ስሜቷን እና ህመሟን ለመግለፅ ይመስላል “ሁሉም ያልፋል” የሚል ግጥሟን የፃፈችው፦
“አላፊው ያልፍና አላፊ ሲተካ
ባላፊው ቀን ባህርይ አላፊ ሲለካ
አላፊ አይመስሌ ቀን ያልፋል ጓዙን ይዞ
ተጉዞ እንደመጣ ደግሞ ሊያልፍ ተጉዞ …”
የህይወት ታሪኳ እንደሚያስረዳው÷ ፊርማዬ እጇን ከወረቀት ጋር ማስማማት የጀመረችው÷ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለች ነበር። አባቷ የሀገሩ ባላባቶች በመሬት እና መሰል ጉዳዮች ይከራከሯቸው ስለነበር÷ የሚያቀርቡትን ሙግት እንድትጽፍ ያዟት ነበር። ይህ ሁኔታም ክርክር እንድትወድ እና ምንነቱን እንድታውቅ አድርጓታል።
“በተፈጥሮ ያገኘሁትን ነፃነት ሊጋፉ የሚሹ ሰዎች በበዙ ቁጥር÷ ይበልጥ እጠነክራለሁ። ሳቅን አፈቅራለሁ። እኔነቴን ከነስሜ ከሁሉም በላይ አደንቃለሁ” የምትለው ገጣሚ ፊርማዬ አለሙ÷ በሰው ልጅ ነጻነት፣ በፖለቲካ፣ በፍቅር እና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅፋለች።
የገጣሚ ስስ ነፍሷን ተከትላ የሰዎችን ስቃይ ተሰቃይታለች። ሰቀቀናቸውንም ተጋርታለች። በነበልባላዊ ብዕሯ ÷ ይኸው ህይወታችንን ተመልከቱ ለማለት በመድረክ እና በመገናኛ ብዙሃን ላይ ግጥሞቿን አቅርባለች። በእርግጥም ግጥም አንብባለች ከማለት ተውናለች ማለት መድረክ አያዟን ለመግለፅ የተሻለ ይሆናል።
ገጣሚዋ በርካታ የግጥም ስብስቦች ቢኖሯትም በግሏ አላሳተመችም። ነገር ግን ከሌሎች ደራሲያን ጋር በጋራ በ1990 ዓ.ም “እኛ የ170 ግጥሞች” በተሰኘ መድብል ውስጥ÷ 26 የግጥም ስራዎቿ ተካተው ታትመዋል።
ከዚህ በኋላ “የአፍሪካ ክራሞት” የተሰኘ ስብስብ ግጥሞቿን የያዘ መፅሐፍ አሰናድታ ነበር። በገንዘብ እጦት ምክንያት ሳይታተም ቀረ። ስራዎቿን ለአንባቢ ለማድረስ ካላት ፅኑ ፍላጎት የተነሳ÷ ይኼንኑ መጽሐፍ በኮምፒዩተር ፅፋ፣ በፎቶ ኮፒ በማባዛት እና ቆራርጣ በመጠረዝ÷ ከ60 ኮፒዎች በላይ ለአንባብያን አድርሳለች።
ፊርማዬ አለሙ እንደ እርሷ ሌሎች ሴት ደራሲያን ወደ መድረክ እንዲወጡ በብዙ ጥራለች። የኢትዮጵያ ሴት ደራሲን ማህበርን በምናነሳበት ጊዜም ከመስራቾቹ አንዷ ሆና እናገኛታለን። በ1987 ዓ.ም ባቋቋሙት በዚህ ማህበር ውስጥ÷ ፊርማዬ በፀሐፊነት እና በሊቀ መንበርነት አገልግላለች። በዚያ ወቅት ማህበሩ ቢሮ ስላልነበረው መኖሪያ ቤቷን እንደ ቢሮ ትጠቀምበት ነበር።
ይህቺ ብርቱ የጥበብ ሰው ጥር 27 ቀን 1993 ዓ.ም ነበር÷ የእረፍቷ ዜና የተሰማው። ፍፁም ባልተጠበቀው የመሞቷ ነገር÷ የሚወዷት በቅርብም በሩቅም የሚያውቋት ሁሉ ሃዘናቸው ከባድ ነበር።
ፊርማዬ አለሙ ከ1984 ዓ.ም ጀምራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተከታታይ ትምህርት ክፍል በዲፕሎማ ፕሮግራም ትምህርቷ ተከታትላለች። በ1988 ዓ.ም እንደገና ወደ ዩኒቨርስቲ በመመለስ÷ በማታው ክፍለ ጊዜ የዲግሪ መርሃ ግብር ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ወራት ሲቀራት ነበር÷ ሞት የቀደማት። “ክራር” የሚለው ግጥሟ÷ ለራሷ ስንብት፣ ለራሷ ትዝታ ቀድማ ከተበችው ይሆን?÷ እንጃ!
“ጭልጥ እንደ ውሃ ላጥ እንደመንገድ
አጠገቤ ሆና ሳላያት ስትሄድ
አንተ የክራር መንገድ እባክህ መልሳት
ትዝታ ክፉ ነው ያነዳል እንደ እሳት
በጣቷ ፈላልጋ ባወጣችው መንገድ
ታሳዝነኛለች ተቀምጣ ስትነጉድ
ባምስቱ ጣቶቿ ደርድራ ደርድራ
አጠገቤ እያለች ወጣች ተንደርድራ”

More Stories
“ትራንስፖርት በባህሪው ወሰን ተሻጋሪ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከጎናችን ሊሆን ይገባል” – አቶ ሰንበቶ አባባ
“የቤተሰቦቼ ፍቅር ለስኬት አብቅቶኛል” – መምህር አንዱዓለም አያሌው
አክሳሪው- ትርፍ!