በጤናው አገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሰራር ግድፈቶችን በማረም የሆስፒታሉን ደረጃ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አስታወቀ
የ2016 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ የልዩ ወረዳው ጤና ጽ/ቤት እና የሆስፒታሉ አመራሮችና ሰራተኞች ለህሙማን ማዕድ የማጋራት መርሃግብር አካሂደዋል።
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት እና የሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አመራርና ሠራተኞች የ2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሙዱላ መጀመሪያ ደረጀ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በመገኘት በህመም ምክንያት በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማሳለፍ ያልቻሉትን ህሙማን የመጎብኘትና ማዕድ የማጋራት መርሃግብር አካሂደዋል።
በመርሃግብሩ ተገኝተው የተቸገሩትን የመርዳትና የመደጋገፍ እሴት የሆነውን የጠምባሮ ብሔረሰብ ባህል ለማጉላትና በተለያዩ የጤና እክል ታመው በሆስፒታሉ የሚገኙትን ህሙማን ለመድረስ ያለመ ይህ በጎ ተግባር ተጠናክሮ እንድቀጥል በትኩረት እንደሚሠራ የተናገሩት የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደግነት አለንቦ ናቸው።
በጎ ተግባሩ በአዲስ ዓመት፤ በአዲስ መንፈስ በጤናው ዘርፍ የታቀዱ ተግባራትን ከግብ ለማድረስ በቅንጅት የመስራት ባህል ያነገበ ነው ያሉት አቶ ደግነት በአዲሱ ዓመት የሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሁለት የህክምና እስፔሻሊቲ አገልግሎቶችን በመጨመር የሆስፒታሉን አገለግሎት አሰጣጥ ይበልጥ በማሻሻልና በማዘመን የተገልጋዩን ማህብረሰብ እርካታ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በሆስፒታሉ የነበሩ የውስጥ አሠራር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የእርምት እርምጃ ስለመወሰዱ የሚናገሩት ኃላፊው አሁን ላይ የሪፎርም ስራዎች ተሠርተው በአዲሱ ዓመት ባለሙያውን በአዲስ መንፈስ በተሻለ አገልግሎት የማሰነቅ ሥራዎች ስለመጀመራቸው ጠቁመዋል።
“በጎነት ለራስ ነው” በሚል መንፈስ ለህሙማን በተደረገው የማዕድ ማጋራት መርሃግብር ላይ የተገኙት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ተከስተ ሰሙኤል በበሽታ ምክንያት የታመሙ ወገኖችን መድረስና የማዕድ የማጋራት ጅምር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የተቸገሩትን የመርዳት በጎ ተግባራት ባህል እንዲሆኑ ከዚህ ተሞክሮ በመውሰድ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማረም በተወሰደው የእርምት እርምጃ አሁን ላይ የጥራት ችግሮችን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት አቶ ተከስተ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሆስፒታሉን የሪፎርም ሥራዎች በማገዝና ከሆስፒታሉ ጋር በቅርበት በመስራት የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር መስፍን ወ/መስቀል በበኩላቸው የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገው የማዕድ ማጋራት መርሃግብር አብሮነትንና መደጋገፍን ከማሳየት ባሻገር በቀጣይ የሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሁለንተናዊ አገልግሎት ለማሳለጥ በጎ ጅምር ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ በሆስፒታሉ የሪፎርም ስራዎችን ለማደናቀፍ እኩይ ዓላማ ያነገቡ የውስጥና የውጭ አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው ሆስፒታሉ የቆመለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ሁሉም የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ዶ/ር መስፍን ጠቁመዋል።
በዕለቱ ድጋፍ የተደረገላቸው አካላት በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልፀው ድጋፍ ላበረከቱ አካላት ምስጋና ቸረዋል።
ዘጋቢ፡ ጡሚሶ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በመድሀኒት ረገድ የሚታየውን ህገ-ወጥነትና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ መከላከል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋን ለመፍጠር በጤናው ዘርፍ በየዓመቱ አዳዲስ የጤና አጠባበቅ ስልቶችን በመንደፍ ዘርፉን ማዘመን እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ባለፉት ሶስት አመታት በወባ ወረርሺኝ ሳቢያ ተደጋጋሚ ጉዳት በማስተናገዳቸው ለከፍተኛ የጤናና የኢኮኖሚ ችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ