ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀንን በማስመልከት በተጨማሪ አገልግሎቶች ህብረተሰቡን ማገልገልና ማገዝ መቻል ስኬትም ድልም ጭምር መሆኑን ነዋሪዎቹ ገለጹ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀንን በማስመልከት በተጨማሪ አገልግሎቶች ህብረተሰብን ማገልገልና ማገዝ መቻል ስኬትም ድልም ጭምር መሆኑን የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

በአገልጋይነት መንፈስ ውስጥ ሀገራቸውን በማገልገል እራሳቸውም ተጠቃሚ መሆናቸዉን የገለፁት አስተያየታቸዉን የሰጡት የከተማ ዉበትና ፅዳት አገልግሎት ሰጭ የማህበረሰብ ክፍሎች እስከዛሬ ከሚሰጧቸው አገልግሎት በተጨማሪ የዛሬዉን ዕለት በተለየ መልኩ ተጨማሪ አገልግሎት በመስጠታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ የትራፊክ ፖሊስና ፍሰት ቁጥጥር ባለሙያዎች በተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫ ተሰማርተው ነፃ አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው እንደገለፁት፤ ጳጉሜን 1 የአገልጋይነት ቀንን በማስመልከት በተጨማሪ አገልግሎቶች ህብረተሰብን ማገልገልና ማገዝ መቻል ስኬትም ድልም ጭምር ነው።

ከትራፊክ አደጋ የፀዳ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር የተጠናከረ የቁጥጥር አገልገሎት ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ በወላይታ ከተማ መርካቶ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ፍሰት ክፍል አስተባባሪ ዋና ሳጅን ዝናቡ ገዛኸኝ ገልጸዋል።

በከተማዋ የተለያዩ አራት አካባቢዎች ላይ በመገኘት የወላይታ ዩኒቨርስቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም ዕለቱን በማስመልከት ለማህበረሰቡ ነጻ የምርመራና ሀክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በተመሳሳይ የወላይታ ሶዶ ከተማ ጤና ጣቢያዎችም ለሚመጡ ታካሚዎች ነጻ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የተለያዩ የንግድ ቦታዎች እንዲሁም በወላይታ የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲስትሪክቶች ተጨማሪ አገልግሎት ለደንበኞቻቸዉ በመስጠት አገልግሎታቸዉን እያከናወኑ እንደሚገኙ ስራተኞቹ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ብዙነሽ ዘውዱ